በስፔኗ ግዛት አልማሶራ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ተደርጎ እንዲውለበለብና የሶስት ቀናት ሐዘን ታውጇል። ምናልባት ስፔን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በኮሮና ቫይረስ ከመሞቱ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ሁኔታው እንደሱ አይደለም የብዙዎችን ልብ የሰበረው የካሪናን አሟሟት ለማሰብ ነው።
ካሪና ከሁለት ልጆቿ ፊት ለፊት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው በባለቤቷ አማካኝነት ነው። ከገደላትም በኋላ እጁን ለፖሊስ የሰጠ ሲሆን ወንጀሉንም ተናዟል።
ከኮሮና በፊት ቢሆን ሰው ተሰባስቦ የ35 አመት እድሜ ያላትን ጎረቤታቸውን ይዘክሯት ነበር። አሁን ግን በኮሮና ምክንያት ቤታቸው የዋሉ ግለሰቦች ግን በርቀት በሃዘን አስበዋታል።
ደወልም ተደወለ፣ ልብ የሚሰረስር ሙዚቃም በኦርኬስትራ ታጅቦ ቀረበ፤ የአካባቢው ህዝብ መውጣት ባይችልም በመስኮታቸው እንዲሁም የቻሉት ደግሞ ወደ በረንዳቸው ወጣ ብለው በፀሎት አስበዋታል።
አገራት የኮሮና መዛመትን ለመቆጣጠር ቤት የመቀመጥ ውሳኔ ማሳለፈቸውን ተከትሎ ሴቶች ከጥቃት አድራሾቻቸው ጋር በአንድ ቤት እንዲቆለፉ፣ እርዳታ ከሚለግሷቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት አለመኖር እንዲሁም ማምለጥ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ልጆችም ትምህርት ቤት ስለማይሄዱና ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ ስለሚያሳልፉ የነዚህ ጥቃቶች ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፤ ለማይሽር ስነልቦናዊ ጉዳቶችም እየተጋለጡ ነው።
ካሪና በስፔን ውስጥ በዚህ አመት ብቻ በትዳር አጋሮቻቸው ወይም በቀድሞ አጋሮቻቸው ከተገደሉ ሴቶች መካከል 17ኛዋ ናት። ኮሮናን ለመከላከል ውሳኔዎች ከተላለፉ በኋላ በትዳር አጋሯ የተገደለችው የመጀመሪያ ሴት ሆናለች።
እንደ ስፔን ጣልያንም በኮሮና ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ ናት። ከመቶ በላይ ዶክተሮች ኮሮናን ሲያክሙ ህይወታቸውን አጥተዋል።
የ27 አመቷ ሎሬና ኳራንታ ዶክተር ለመሆን የቀራት ጥቂት ጊዜ ነበር፤ ህይወቷ በአጭር ባይቀጭ። እንደ ሌሎች ዶክተሮች በኮሮና አይደለም የሞተችው የፍቅር ጓደኛዋ መግደሉንም ለፖሊስ ተናዟል።
አስከሬኗም ወደተወለደችበት ሲሲሊ ፋቫራ ከተማ ሲመለስም ብዙዎች በበረንዳቸው ላይ ነጭ አንሶላ ሰቅለው በኃዘን ተቀብለዋታል።
የነጩ አንሶላ ምልክትም ከንቲባ አና አልባ ይገልፁታል " የመንፈሷን ፅዳት እንዲሁም ለዘመናት ህልሟ የነበረው ዶክተር ስትሆን የምትለብሰውን ነጭ መለዮ ልብስ የሚያመላክት ነው።"