ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 92 ደረሰ
በዓለማችን ላይ ቢሊየኖች የኮቪድ-19ን እንቅስቃሴ ለመግታት ቤት ዘግተው ተቀምጠዋል። የዚህን ቫይረስ የስርጭት ሽክርክሪት ለመስበር ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ራስዎን ሰዎች ከሚበዙበት ስፍራ ማራቅ ነው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን ደጋግሞ በሳሙናና በውሃ መታጠብ ደግሞ ሌላው መከላከያ ነው። እናንተም ጤና እኛም ደህና ሆነን እንድንውል እየተመኘን ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ የቀጥታ ዘገባችንን ይከታተሉ ግብዣችን ነው።
የቀጥታ ሽፋን
ጂቡቲ በአንድ ቀን 156 ተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን አስታወቀች
ጂቡቲ በሃያ አራት ሰአት ውስጥ ባደረገችው ምርመራ 156 ተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን አስታውቃለች።
በአገሪቷ ውስጥ በአንድ ቀን ከተመዘገቡ ቁጥሮች ይህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
በአገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችንም ቁጥር 591 አድርሶታል።
የጂቡቲ የጤና ሚኒስትር መሃመድ ዋርሳሜ እንዳሳወቁት እስካሁን ድረስ ሁለት ህመምተኞች ህይወታቸው ሲያልፍ 73ቱ አገግመዋል። አክለውም ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ እንደተዛመተ ተናግረዋል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እስማይል ኦማር ገሌ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጂቡቲ ጥላቸው የነበሩ እገዳዎች ከ7-10 ቀናት መራዘማቸውንም በትናንትናው ዕለት አስታውቀዋል።
ለሁለት ሳምንታት ያህል አገሪቷ ኣሳልፋው የነበረው አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔም "ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ማህበረሰቡ ውስጥ እንዳይዛመት ረድቶናል" ብለዋል።
ከአንድ ሚሊዮን ያነሰ የህዝብ ቁጥር ያላት ጂቡቲ እስካሁን ባለው አምስት ሺ የኮሮና ምርመራዎችንም አከናውናለች።
የመጀመሪያዎቹ ህመምተኞች ከውጭ ሃገር የመጡ የህክምና ባለሙያዎች መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ኤቶ መቶ ሺ ካሜሮናውያንን ሊረዳ ነው
የቀድሞው የባርሴሎና አጥቂ ሳሙኤል ኤቶ በካሜሮን የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ለ100,000 ሰዎች የሚሆን የተለያዩ አቅርቦቶችን እንደሚረዳ ተናገረ።
ኤቶ በአገሩ በጎ አድራጎት ድርጅት ያለው ሲሆን "በአራት ከተሞች ለሚገኙ 50ሺህ አባወራዎች ሳሙና፣ ሳኒታይዘር፣ ምግብ ለማቅረብ ቃል ገብቷል"
በተጨማሪም 50 000 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ለታክሲ አሽከርካሪዎች እንደሚያከፋፍል ቃል ገብቷል።
"ይህ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ነው ስለዚህ በአግባቡ ንጽህናችንን በመጠበቅ እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን በማቅረብ የቫይረሱን ስርጭት መቀልበስ እንችላለን" ብሏል ሳሙኤል ኤቶ በበጎ አድራጎቱ በኩል ባወጣው መግለጫ።
በካሜሮን የወደብ ከተሞች እንቅስቃሴ የተከለከለባቸው ሲሆኑ ማንኛውም ዓይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴም ታግዷል።
በካሜሮን 850 ሰዎች ኮቪድ-19 የተያዙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 17 ሰዎች ሞተዋል።
በናይጄሪያ ፖሊስ ከኮሮና በላይ መግደሉ ይፋ ሆነ
የናይጄሪያ የጸጥታ ኃይሎች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከቤት ያለመውጣት ትዕዛዝ ከተላለፈ ጊዜ አንስቶ ከኮቪድ-19 በላይ ሰዎች መግደሉን የብሄራዊ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን አስታወቀ።
በናይጄሪያ እስካሁን ድረስ 12 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሲሞቱ ፖሊስ የቤት መቀመጡን መመሪያ ለማስፈፀም በወሰደው እርምጃ ግን 18 ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ እንዳለው እስካሁን ድረስ ከ100 በላይ ቅሬታዎች ከ24 ግዛቶች እንደቀረቡለት ገልጾ፣ ቅሬታ የቀረበባቸው ግዛቶች መካከል ሌጎስ፣ ኦጉን እና አቡጃ እንደሚገኙበት አስታውቋል።
በናይጄሪያ ለሁለት ሳምንት ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ በቅርቡ መራዘሙ ይታወሳል።
ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ እንዳለው በስልክ መስመራቸው በመደወልና የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መላካቸውን ገልፀዋል።
የናይጄሪያ አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት 200 ሚሊዮን ሲሆን እስከ አሁን ድረስ 407 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል።
በማላዊ ነርሶች የስራ ማቆም አድማ መቱ
በማላዊ የሚገኙ ነርሶች መንግሥት ተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎችን መቅጠር ባለመቻሉ የስራ ማቆም አድማ መቱ።
መንግሥት ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት 2000 የጤና ባለሙያዎች እንደሚቀጥር አስታውቆ ነበር ተብሏል።
በማላዊ ነርሶች ዝቅተኛ ክፍያ፣ የአካል መከላከያ አለመኖርና ረዥም ሰዓት መስራትን በማንሳት ቅሬታ አቅርበው ነበር።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ነርሶች በክዊን ኤልዛቤጥ ሴንተራል ሆስፒታል ስራ አንገባም ብለው ተቃውሞ ሲያሰሙ የሚያሳይ የትዊተር መልዕክት አጋርቷል።
የማላዊ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት ለ21 ቀን እንቅስቃሴን ያገደ ሲሆን እስካሁን ድረስ 16 ሰዎች በቫይረሱ መያዛችን ተረጋግጧል።
የኮሮናን ህግ ተላልፈዋል የተባሉት ህንዳዊው ምሁርና ሰባኪ "በግድያ" ወንጀል ተከሰሱ
300ሺህ አፍሪካውያን በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ-የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን
በአሜሪካ ፖሊስ በእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ የ17 ሰዎች አስከሬን አገኘ
በአሜሪካ ኒው ጀርሲ ግዛት በሚገኝ በአንድ የአዛውንቶች የእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ የ17 ሰዎች አስክሬን መገኘቱ ተገለፀ።
ፖሊሶቹ በማገገሚያ ማዕከል ውስጥ የሞቱ ሰዎች መኖሯቸው ከተነገረው በኋላ በስፍራው ሲደርስ አራት ሰው የመያዝ አቅም ባለው አስክሬን ማቆያ ውስጥ 17 ሰዎች ማግኘቱ ተነግሯል።
"ተቋሙ ምናልባት በቂ ሰራተኛ የሌለውና ከፍተኛ ሕሙማን ያስተናገደ ይመስለናል" ብለዋል የፖሊስ አዛዡ ኤሪክ ዳኒልሰን ለሲኤንኤን።
እንደ ኒዮርክ ታይምስ ዘገባ ከሆነ ይህ የማገገሚያ ማዕከል ሁለት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ከዚህ ቀደም በሌላኛው ቅርንጫፉ ሁለት ነርሶችን ጨምሮ 68 ሰዎች መሞታቸውን ዘግቧል።
ከሟቾቹ መካከል 26 የኮሮናቫይረስ ሲገኝባቸው የቀሪዎቹ የ42 የሞት መንስዔ ግን አልታወቀም።
ባለፈው መጋቢት ወር ድርጅቱ በሜዲኬር ቅኝት የተደረገበት ሲሆን ማገገሚያ ማዕከሉ ከደረጃ በታች መሆኑ ተገልጾ ነበር።
በዓለም ላይ የእንክብካቤ ማዕከሎች ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በርካታ ሞቶች ገጥሟቸዋል።
ኤሊዬን አንሸራሽራለሁ ያሉ ጣሊያናዊ ቅጣት ተከናነቡ
ኮቪድ-19 በመላው ዓለም ከተከሰተ ወዲህ መንግሥታት ካስተላለፏቸው መመሪያዎች መካከል አንዱ ለአስፈላጊ ነገር ካልሆነ በቀር ከቤት አትውጡ የሚል ነው።
ቤታቸው የተቀመጡ ደግሞ ውሻቸውን እንዲያንሸራሽሩ የፈቀዱ የተወሰኑ አገራት አሉ።
ጣሊያን ውስጥ ታዲያ የሮም ፖሊስ የ60 ዓመቷ አዛውንት ኤሊያቸውን ሲያናፍሱ አግኝቷቸው 206 ዩሮ ቀጥቷቸዋል።
እኚህ አዛውንት ለማዳ ኤሊያቸው ቤት ውስጥ ታፍና ቢያይዋት አየር ትቀበል ብለው መወሰናቸውን ይናገራሉ።
ፖሊስ ግን በኤሊ መንቀራፈፍ በአዛውንቷ እርምጃ መካከል ያስተዋልነው የበጋውን ፀሀይ ለመሞቅ የተሴረች ሴራ መሆኗን ነው ብሏል።
ጣሊያናውያን ከቤት በሚወጡበት ሰዓት መሙላትና መያዝ ያለባቸው ቅፅ አለ። ይህንን የሞሉትን ቅጽ ታዲያ በመንገድ ላይ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለሚያገኛቸው ፖሊስ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
ጣሊያን በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጎዱ አገራት መካከል ስትሆን በቫይረሱ ምክንያት 21645 ሰዎች ሞተዋል።
ባለፈው ሳምንት ፈረንጆቹ ባከበሩት ፋሲካ ሰሞን 14ሺህ ሰዎች ቤት ውስጥ መቀመጡን በመጣስ ቅጣት ተከናንበዋል።
በአሜሪካ በኮሮና ምክንያት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስራቸውን አጡ
በኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ እየተመታች ባለችው አሜሪካ በባለፉት አራት ሳምንታት ብቻ 21 ሚሊዮን ሰዎች ስራቸውን እንዳጡ ተዘግቧል።
በአገሪቷም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ስራ ያጡበት ወቅትም ነው ተብሏል።
ከሰራተኞች ጉዳይ መምሪያ በተገኘው አሃዝ መሰረት በባለፈው ሳምንት ብቻ አዲስ 5.25 ሚሊዮን ተመዝጋቢዎች የመጡ ሲሆን ከዛ በፊት በነበረው ሳምንትም 6.6 ሚሊዮን ሰዎች ስራችንን አጥተናል ብለው አመልክተዋል።
የወረርሸኙን መስፋፋት ተከትሎ በብዙ ግዛቶች አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔ ተላልፏል፤ ይህም ሁኔታ የአሜሪካን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ቀጥ አድርጎታል። የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም ሆኑ ተቋማትም ሰራተኞቻቸውን በማሰናበትም ላይ ናቸው።
ከስራ የሚሰናበቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም እንደሚጨምር የተገመተ ሲሆን በጎርጎሳውያኑም የወር መጨረሻ 20 በመቶ ይደርሳልም ተብሎ ይጠበቃል።
በአሜሪካ ውስጥ 640 ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 30ሺ 985 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
"አብረን ነን" ሚሊንዳ ጌትስ
" ኮቪድ-19 በማንኛውም ስፍራ ካለ ኮቪድ-19 በየትኛውም ስፍራ አለማለት ነው" ይህንን ሚሊንዳ ጌትስ ለዓለም አቀፍ ትብብር ጥሪ ባቀረቡበት ቃለምልልሳቸው ወቅት ያሉት ነው።
እኚህ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና አንቀሳቃሽ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚያደርጉትን ድጋፍ ማቋረጣቸውን ካሳወቁ በኋላ ቢቢሲ ሬዲዮ 5 ላይቭ ላይ ቀርበው ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅትን ድጋፍ ማቋረጥ " ስሜት አይሰጥም" ሲሉም ገልፀዋል።
ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ የዓለም ጤና ድርጅት ሁለተኛው ትልቁ ድጋፍ አድራጊ ሲሆን ኮቪድ-19ን ለመዋጋት ተጨማሪ 150 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብቷል።
ሚሊንዳ ጌትስ በዚህ ቃለመጠይቃቸው ላይ ከ18 ወራት በፊት ክትባት ዝግጁ ይሆናል ብለው ተስፋ እንደማያደርጉ ገልፀዋል።
ጌትስ አክለውም ቤተሰባቸው ወረርሽኙን መተንበዩን የተናገሩ ሲሆን ቀድመው ምግብ ማስቀመጣቸውን ገልፀዋል። ነገር ግን "በኛ ዘመን ይደርሳል ብለን አልጠበቅንም ነበር" ብለዋል።
ሚሊንዳና ባለቤታቸው ቢል የዉሃንን መረጃ በሚመለከቱበት ወቅት " ፈጣሪ ሆይ ወረርሽኙ እየተከሰተ ነው" ማለታቸውን ያስታውሳሉ።
ሚሊንዳ አክለውም "ምንም ልናደርገው የምንችለው የተለየ ነገር የለም፤ ሁለችንም በጋራ ያለንበት በሽታ ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 92 ደረሰ
ናይጄሪያዊው ዶክተር በኮሮና ህይወታቸው አለፈ
በግል ክሊኒካቸው ውስጥ በኮሮና የተጠቃን ግለሰብ ሲያክሙ የነበሩት ናይጄሪያዊው ዶክተር በኮሮና ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
ዶክተሩ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁት ባለፈው ሳምንት በኮሮና ህይወቱ ያለፈ ግለሰብ ሲያክሙ ተላልፎባቸው ነው ተብሏል።
ሰኞ ዕለት ወደ ናይጄሪያ የማስተማሪያ ሆስፒታል ተወስደው የነበረ ቢሆንም በትናንትናው ዕለት ህይወታቸው ማለፉን የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ክሪስ ቦዴ ገልፀዋል።
ዳይሬክተሩ አክለው እንደገለፁትም ሆስፒታሉ ሲደርሱ በፀና ታመው እንደነበር ነው።
ሟቹ ዶክተር ቹግቦ ኤሜካ የአስም ህመምተኛ እንደነበሩና ዕድሜያቸው 51 መሆኑን ቫንጋርድ ጋዜጣ የናይጄሪያ የሐኪሞች ማህበርን ጠቅሶ ዘግቧል።
ማህበሩ ከዚህ ቀደም መንግሥት ለጤና ባለሙያዎች አስፈላጊውን መከላከያ እንዲያቀርብ ጠይቆ ነበር።
ማህበሩ በተጨማሪ ወደ ጤና ማዕከላት የሚመጡ ህሙማን የጉዞ ታሪካቸውን፣ ከዚህ ቀደም ኮሮና ከታመመ ሰው ጋር ንክኪ መኖር አለመኖሩን ለዶክተሮቻቸው እንዲያሳውቁና ኮሮና መሆን አለመሆኑም በፍጥነት እንዲለይ ያደርጋል በማለት መልዕክት አስተላልፏል።
ኮሮናቫይረስ ያጠላበት የዛሬው ፀሎተ ሐሙስ እንዴት እየተከበረ ነው?
የኮሮናቫይረስ ፅኑ ህሙማን እንዴት ያገግማሉ?
አራት ሚሊዮን ሩዋንዳውያንን ስለኮሮና ለማስተማር የወጠነው የሬዲዮ ድራማ
" ልጆቻችንን ልቀቋቸው" የባርሴሎና ከንቲባ
ስፔን ዜጎቿ ወዲያ ወዲህ እንዳይሉ በሚል ካዘዘችና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገች ወር ሞላት። ነገር ግን ከሌሎች አውሮፓዊ ጎረቤቶቿ ተለይታ ልጆችም ቢሆኑ ውልፊት ማለት አይችሉም ብላለች።
በስፔን ልጆች በምንም ምክንያት ቢሆን ከቤቱ ደጃፍ ዝር ማለት አልተፈቀደለትም።
አዳ ኮላኡ የባርሴሎና ከንቲባ ናቸው። መንግሥታቸውን " ልጆቻችንን ልቀቋቸው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከንቲባዋ በፌስቡክ ሰሌዳቸው ላይ ለጥፈው ባስነበቡት ጽሁፍ በርካታ ወላጆች የልጆቻቸው " የስነልቦናና አካላዊ ጤና " ስጋት ገብቷቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።
"እኛ የሰለቸን ነገር እርስ በእርሳችን እንዴት መረዳዳት እንዳለብንና እንዴት ህይወታችንን መምራት እንዳለብን ከመንገር ይልቅ 'ይህ ጦርነት ነው እናንተ ደግሞ ወታደሮቹ ናችሁ' መባል ነው" ብለዋል በምሬት።
በስፔን የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣዮቹ አስር ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።
በስፔን እስካሁን ድረስ 182,816 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
የመጠጥ አምራቹ አልኮል መጠጣት ቫይረሱን አይከላከልም አለ
የሄኔሲ ኮኛክ አምራች ኬንያውያንን አልኮል መጠጣት ከኮሮናቫይረስ ያድናል ብላችሁ እንዳትታለሉ ሲል አስጠነቀቀ።
አልኮል መጠጣት ኮቪድ-19ን ይከላከላል የሚለው ሃሳብ የተሰማው ከኬንያ መዲና ናይሮቢ ገዢ ማይክል ሶንኮ ነበር።
የናይሮቢ ገዢው ለምንዱባኖች ከሚሰጡት የምግብ እርዳታ ጋር አንድ ጠርሙስ አልኮል መጠጥ በመስጠት የቫይረሱን ስርጭት አንደሚከላከሉም ተናግረዋል።
" ሄኔሲ የኛንም ምርት ሆነ ሌላ ማንኛውንም የአልኮል መጠጥ መውሰድ ከቫይረሱ አይከላከልም" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የናይሮቢ ገዢ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው ላይ የዓለም ጤና ድርጅት የአልኮል መጠጥ ኮቪድ-19ን ይከለከላል ብሏል ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከዚህ ቀደም የዓለም ጤና ድርጅት አልኮል መጠጥ መውሰድ ከኮሮናቫይረስ አይከላከልም ሲል አስታውቆ ነበር። ነገር ግን አልኮል ያለው የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር እጅን ለማጽዳት መጠቀም ጀርሞችን እንደሚገል አስታውቋል።
" መጠጥ መጠጣት ቫይረሱን አያጠፋውም፤ አንድ ሰው መጠጥ የሚጠጣ ከሆነና በቫይረሱ ከተያዘ ተጎጂነቱ ይበልጥ ይጨምራል" ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት።
መጠጥ አዘውትረው የሚጠቀሙ ሰዎች በሽታን የመከላከል አቅማቸው እየደከመ እንደሚሄድ ይታወቃል።
ባለፈው መጋቢት ወር በኢራን ኮቪድ-19ን ለመከላከል አልኮል መጠጣት ፈዋሽ ነው የሚል ሀሰተኛ ወሬ ተሰራጭቶ ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል።
በኮቪድ-19 ከሞቱት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የቀደመ የጤና እክል ነበረባቸው ተባለ
በኢንግላንድ እና ዌልስ በኮቪድ-19 ሳቢያ ከሞቱት 90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የቀደመ የጤና እክል የነበረባቸው ናቸው ተባለ።
ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ እንዳለው በፈረንጆቹ ወር በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ 4ሺህ ሰዎች የጤና ሁኔታን ተመልክቷል።
ቢሮው ደረስኩበት እንዳለው፤ በኮቪድ ከሞቱት መካከል 91 በመቶ የቀደመ የጤና ችግር አለባቸው።
የልብ ሕመም፣ የመርሳት በሽታ እና የመተንፈሻ አካል ሕመም ደግሞ አብዛኞቹ ሟቾች የሚጋሯቸው የበሽታ አይነቶች ናቸው።
የኮሮናን ህግ ተላልፈው መጠጥ የገዙት የሌሶቶው ሚኒስትር ክስ ሊመሰረትባቸው ነው
የሌሶቶ ፖሊስ አስገዳጁን የቤት መቀመጥ ሕግ ተላልፈው መጠጥ ሲገዙ በካሜራ ይዣቸዋለሁ ያላቸውን ሚኒስትር ለፍርድ እንደሚያቀርብ አሳውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ያለችው ሌሶቶ እንደ ጎረቤቷ ደቡብ አፍሪካ የአልኮል መጠጦች ሽያጭንም አግዳለች።
ቪዲዮው ሌህሎኖሎ ሞራሞትሴ የተባሉት የፖሊስና የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ሁለት ሳጥን መጠጥ ሲገዙ የሚያሳይ ሲሆን ብዙዎችም ቪዲዮውን ተጋርተውታል።
በሚኒስትሩ ላይ የተደረገው ምርመራ እንደተጠናቀቀና ፖሊስ ክስ ለመመስረትም ጫፍ መድረሱን የሃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።
በሌሴቶ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የሌለ ሲሆን አጎራባቿ ደቡብ አፍሪካ ግን ከአፍሪካ ከፍተኛ የሚባለው አሃዝ ተመዝግቦባታል።
እስካሁንም ባለው መረጃ 2ሺ 500 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።