"አገሪቷን ብንዘጋት ህዝቡ ምን ይበላል?" ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን ተከትሎ አገራት ህዝቦቻው ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ እግድ በመጣል ከተሞቻቸውን ቢዘጉም የኬንያው ፕሬዚዳንት ቤት የመቀመጥ ውሳኔ "ህዝባችንን ምግብ አልባ ያደርገዋል" ብለዋል።
የተለያዩ መመሪያዎችን እያወጣች ያለችው ኬንያ ሙሉ በሙሉ አገሪቷን መዝጋትና ቤት የመቀመጥ ውሳኔ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ኬንያውያን የተላለፉትን ህጎች ማክበር ሳይችሉ ሲቀሩ ነው። የመጨረሻም አማራጭ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
መዲናዋን ናይሮቢን ጨምሮ ቫይረሱ ተከስቶባቸዋል በተባሉ ሶስት ግዛቶችም ላይ የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ በትናንትናው ዕለት የነበረውን መግለጫ አስመልክቶ ቃለ መጠይቅ በዛሬው ዕለት የተደረገላቸው ሲሆን እነዚህ መመሪያዎች አገሪቷን ሙሉ በሙሉ ከመዝጋት የሚታደጉ ናቸው ካሉ በኋላ፤" አገሪቷን ብንዘጋት፣ ቤት ተቀመጡ ብንል፤ ህዝቡ ምን ይበላል" ብለዋል።
እስካሁንም ባለው መረጃ በኬንያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 158 ሲሆን ስድስት ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።