በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ሦስቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ሠራተኞች ናቸው ተባለ

የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት አገራት በርካታ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው። በኢትዮጵያም የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት የሚረዱ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ እንሰማለን። ማንኛውም መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ግን በዜጎች ፈፃሚነት ካልታገዘ መጪውን ጊዜ ፈታኝ ያደርገዋል። ሁሉም በጤና እንዲኖርና ያሰበውን እንዲያሳካ፣ እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ አለመጨባበጥን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። እነዚህን መከላከያ መንገዶችን እየተገበርን በጤና እንኑር! በኮቪድ-19 ዙሪያ የምንሰበስበውን አበይት መረጃ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ዘገባችን እናቀርብላችኋለን።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በአሜሪካ በ24 ሰዓት ብቻ 1736 ሰዎች ሞቱ

    ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ በየትኛውም አገር በአንድ ቀን ይህን ያህል ሰው ሞቶ አያውቅም፡፡

    አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት ብቻ በ24 ሰዓት 1ሺህ 736 ሰዎች ሞተውባታል፡፡

    ይህም እስካሁን በአሜሪካ ምድር የሟቾችን ቁጥር 12ሺህ 722 ያደርሰዋል፡፡

    በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 400 መቶ ሺ ለመድረስ 2ሺ ሰዎች ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 1 ሚሊዮን 400ሺ እያለፈ ይገኛል፡፡

  2. ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አሁንም ከጽኑ ሕሙማን ክፍል አልወጡም

    የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለ2ኛ ቀን በጽኑ ሕሙማን ክፍል አሳልፈዋል፡፡

    በመካከለኛው ሎንዶን ቅዱስ ቶማስ ሆስፒታል እጅግ በረቀቁ መሣሪያዎችና አሉ በሚባሉ ሐኪሞች የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙት ቦሪስ ጤንነታቸው ለክፉ የሚሰጥ አይደለም እየተባለ ነው፡፡

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በሰጠው መግለጫ ‹‹መሪያችን ቦሪስ የኦክሲጂን እርዳታ እያገኙ ነው፤ ነገር ግን ቬንትሌተር ወደ መጠቀም ደረጃ የሚያደርስ ችግር አልገጠማቸውም፤ መልካም በሚባል ሁኔታ ነው የሚገኙት ብሏል፡፡

    ቦሪስን ተክተው አገሪቱን ለጊዜው እየመሩ ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶምኒክ ራብ ‹‹ቦሪስ በአሸናፊነት ከህመማቸው ተፈውሰው እንደማይ ይቺን ታክል አልጠራጠርም›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ወደ ሆስፒታል የገቡት ዕሑድ ከሰዓት ህመሙ እየባሰባቸውና ሳሉ እየጸናባቸው በመምጣቱ ነበር፡፡

  3. የውሃን ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት ሆነች

    የተቀረው ዓለም ቀስ በቀስ በሩን እየከረቸመ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ተወልዶባታል የምትባለው ዉሃን ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ ለእንቅስቃሴ በሯን ሙሉ በሙሉ ከፍታለች፡፡

    ጤናማነታቸው የተረጋገጠና ይህንኑ የሚመሰክር አረንጓዴ ኩፖን ምልክትት (በስልክ መተግበሪያ ላይ የሚገኝ) የያዙ ነዋሪዎቿ አሁን ወደየትም አገር መጓዝ ይችላሉ፡፡

    የባቡር መንገዶቿ፤ የመኪና አውራ ጎዳናዎቿም ለመጀመርያ ጊዜ በሙሉ ኃይል ክፍት ሆነዋል፡፡ የ11 ሚሊዮን ቻይናዊያን መኖርያ የሆነችው ውሃን ለ11 ሳምንታት ሙሉ በሙሉ ተዘግታ፤ እንቅስቃሴዋ ታግዶ ከርማ ነበር፡፡

    በቻይና ወረርሽኙ ከተነሳ ወዲህ 3300 ሰዎች ብቻ የሞቱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የሚበዙቱ የዚች ከተማ ነዋሪዎች ነበሩ፡፡

  4. እንደምን አደራችሁ

    በትናንትናው ዕለት የዘጠኝ ወር ህፃንን ጨምሮ ስምንት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    እነዚህ ስምንት ሰዎችም የተገኙትም ለ264 ሰዎች በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ነው።

    የኮሮና ቫይረስ መዛመት ከጀመረበት ጀምሮ ለተጠርጣሪዎች ምርመራ እያደረገቸው ባለችው ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 2271 ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል

    ከነዚህም ውስጥ 52ቱ በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ፣ አራቱ ከህመሙ አገግመዋል፣ ሁለቱ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል፣ ሁለቱ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

    አንደኛው በፅኑ ህክምና ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አርባ አራቱ ደግሞ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች ለይቶ ማቆያ ይገኛሉ።

    ብዙዎቹ ህመምተኞች ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ቢሆኑም፣ ምንም አይነት የውጭ ጉዞ ታሪክ የሌላቸው ግለሰቦች በበሽታው መያዛቸውም አሳሳቢ ሆኗል።

    በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እንድትመረምር ብዙዎች እየጠየቁ ሲሆን ጤና ሚኒስቴርም ምርመራ እንደሚጨምር አሳውቋል። ቢቢሲ አማርኛ በቫይረሱ ህይወታቸው ላጡ ዘመዶችና ቤተሰቦች መፅናናትን እንዲሁም በህክምና ላይ ለሚገኙት መዳንን ይመኛል።

    በቫይረሱ ላይ እየተደረጉ ስላሉ ሳይንሳዊ ምርምሮች፣ አገራት ስላሉባቸው ሁኔታዎች፣ አገራት እየወሰዱት ስላሉት እርምጃዎች እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን በቀጥታ ዘገገባችን ማግኘት ይችላሉ።

    መልካም ቀን እንዲሆንላችሁ ተመኘን

  5. በኒው ዮርክ የሟቾች ቁጥር 5 ሺህ 489 ደረሰ

    አሜሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተመታችው ኒው ዮርክ ከፍተኛ ሞት እያስተናገደች እንደሆነ የግዛቷ አስተዳዳሪ አንድሪው ኮሞ ገልጹ።

    በግዛቲቱ ትናንት በአንድ ቀን ውስጥ 731 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ይህም ከፍተኛው የሞት ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።

    በአሜሪካ በአጠቃላይ እስካሁን 38 ሺህ 836 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በኒው ዮርክ ብቻ 5 ሺህ 489 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

    ጎረቤቷ ኒው ጀርሲይ ደግሞ የሟቾች ቁጥር ከ1 ሺህ መብለጡን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

    አስተዳዳሪው አክለውም ከተማዋ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን በሆስፒታሎች ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ አዲስ በተዘጋጁ ድንገተኛ ሆስፒታሎች 3 ሺህ የሚሆኑ አልጋዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

  6. ሰበር, በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ሦስቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ሠራተኞች ናቸው

    በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠው ሰዎች መካከል ሦስቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ሠራተኞች መሆናቸው ተገለጸ።

    የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ከሠራተኞቻቸው መካከል ሦስቱ የኮቪድ-19 ቫይረስ እንደተገኘባቸው ተናግረዋል።

    ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የታመሙት ሠራተኞች ጤንነት በደህና ሁኔታ ላይ ይገኛል።

    ድርጅቱ አሁን በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ይፋ ያደረጋቸው ሠራተኞቹ በበሽታው በምን ሁኔታ ሊያዙ እንደቻሉ የተባለ ነገር የለም።

    ሮይትረስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ደግሞ አየር መንገዱ ከፈረንጆቹ ጥር እስከ ሚያዚያ ድረስ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ሳቢያ ካለው አቅም 10 በመቶውን ብቻ እየሰራ 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አጥቷል።

    ወረርሽኙ ቻይና ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በተስፋፋበት ጊዜ በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ቢያቋርጡም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ይበር እንደነበር ይታወሳል።

    በዚህም ሳቢያ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች፣ አየር መንገዱ በረራውን እንዲያቋርጥ ግፊት ቢደረግበትም እንደማያቋርጥ ተናግሮ ነበር።

    በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፉ የበረራ ኢንዱስትሪ ላይ ባደረሰው ከባድ ጫና ሳቢያ አብዛኛውን በረራዎቹን አቁሟል።

    እስካሁን በኢትዮጵያ 52 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንድ ግለሰብ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

    አራት ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው የተገለጸ ሲሆን ሁለት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

  7. ስለኮሮናቫይረስ ምርመራ ሐሰተኛ መልዕክት ያስተላለፈው ፍርድ ቤት ቀረበ

    ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሐሰተኛ ዜናን በማሰራጨት የተከሰሰው ግለሰብ በኬፕ ታውን ከተማ ፍርድ ቤት ቀረበ።

    በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለሦስት ሳምንታት እንቅስቃሴን ያገደችው ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ወረርሽኙን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያጋሩ ሰዎችን አስከ 6 ወር በሚደርስ እስር፣ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም የሚያስቀጣ ጥፋት መሆኑን አውጃለች።

    ስቴፈን ቢርች የተባለው የ55 ዓመት ዕድሜ ያለው ግለሰብ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያው በሽታን ያስተላልፋል በማለት በቪዲዮ አስተላልፏል ተብሎ ነው የተከሰሰው።

    በስፋት የተሰራጨው ቪዲዮ የመመርመሪያ መሳሪያው "ቫይረሱን የሚያስተላልፍ" በመሆኑ ሰዎች ቤት ለቤት በመሄድ ምርመራ የሚያደርጉትን ባለሙያዎች እንዳይቀበሏቸው ይመክራል። .

    ደቡብ አፍሪካ በዚህ ሳምንት ሰፊ የምርመራ ዘመቻ የጀመረች ሲሆን፤ እስከ ሚያዚያ ማብቂያ ድረስ በየቀኑ 30 ሺህ ሰዎችን ለመመርመር አቅዳለች።

    ነገር ግን ባለስልጣንት በግለሰቡ የተሰራጨው የቪዲዮ መልዕክት በሥራቸው ላይ እንቅፋት ሳይፈጥር እንደማይቀር ስጋታቸውን ገልጸዋል።

  8. ሰበር, በእንግሊዝ ሌሎች 758 ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸው ተነገረ

    በእንግሊዝ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ህክምና ሲደረግላቸው የነበሩ ተጨማሪ 758 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቷ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት አስታወቀ።

    ይህም በእንግሊዝ እስካሁን በሆስፒታል በክትትል ላይ ሳሉ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 5 ሺህ 655 አድርሶታል።

    ትናንት አጠቃላይ የሟቾቹ ቁጥር 4 ሺህ 897 የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ግን ቁጥሩ ጨምሯል፡፡

  9. በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሚጠቁ ጥቁሮች አሃዝ ከነጮች ይበልጣል እየተባለ ነው

    ኮሮናቫይረስ ዘር፣ ቀለም፣ ሃብት፣ ጾታና ሃይማኖት አይለይም ይባላል። ታዲያ በአሜሪካ ከነጮች ይልቅ በጥቁሮች ላይ ምነው ክንዱ በረታ?

    በቅርብ ከወደ አሜሪካ የወጡ መረጃዎች አስገራሚ ሆነዋል።

    ይህ ዘገባ ሲጠናቀር በአሜሪካ 370 ሺህ ሰዎች በወረርሽኙ ተጠቅተዋል። 11ሺህ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። ከዚህ አሐዝ የጥቁሮች ድርሻ ከፍተኛ ነው።

    ለምሳሌ ቺካጎን እንመልከት።

    በቺካጎ ከጠቅላላው ነዋሪ የጥቁሮች ብዛት 30 ከመቶ ብቻ ነው። ወደ ኮሮናቫይረስ ስንመጣ ግን በቺካጎ ከሞቱት ሰዎች 70 ከመቶ ጥቁሮች ናቸው። በቫይረሱ ከተያዙት ደግሞ ግማሹ ጥቁሮች ናቸው።

    ከኤፕሪል 5 ወዲህ ያለውን ቁጥር እንኳ ብንመለከት በቺካጎ 4ሺህ 680 ሰዎች ቫይረሱ ይዟቸዋል፡፡ 1824ቱ ጥቁሮች፣ 847ቱ ነጮች፣ 478 ሂስፓኒክ እና 126 ኢሲያዊ ዝርያ ያላቸው ናቸው።

    ወደ ኢሊኖይ ግዛት እንሂድ። ተመሳሳይ ነገር እናገኛለን።

    እዚያ የጥቁሮች ብዛት 14 ከመቶ ብቻ ነው። 41 ከመቶ ሟቾች ግን ጥቁሮች ሆነው ተገኝተዋል። ተጨማሪ አንብቡ፡ ኮሮናቫይረስ በአሜሪካ ከነጮች ይልቅ በጥቁሮች ላይ ለምን ጨከነ?

  10. በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የሰዎች አማራ ክልል ድጋፍ እያደረገ ነው

    የአማራ ክልል መንግሥት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት እንቅስቃሴዎችን ባገደባት ባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ ችግረኞች የምግብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

    የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እገዳውን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎችን የማገዝ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

    "በዕለታዊ ገቢ የሚኖሩትን ከሰኞ ጀምሮ ቤት ለቤት በመሄድ በነፍስ ወከፍ ስሌት የዱቄት እድላ እየተደረገ ነው። በተጨማሪም በከተማው ከንቲባ በኩል አቅርቦቱ እንደቀጠለ ነው" ብለዋል።

    በተጨማሪም የጎዳና ተዳዳሪዎችንና በቤተ እምነት አካባቢዎች የሚገኙ ችግረኛ ሰዎች በመሰብሰብ መስተዳደሩ በመመገብ ላይ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

    በእንቅስቃሴ እገዳው ወቅት ቀረው ነዋሪ የአቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው መግዛት ለሚችለው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሰፈር ለሰፈር የሽንኩርት፣ ድንችና የአትክልት ምርቶች እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑንና ሌሎችም መሰረታዊ ሸቀጦች ለማሰራጨት እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ገልጸዋል። ዝርዝሩን ያንብቡ፡ በእንቅስቃሴ ላይ በተጣለው ገደብ ለችግር ለተጋለጡ የአማራ ክልል ድጋፍ እያደረገ ነው

  11. ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ 600 ኢራናዊያን በአልኮል ተመርዘው ሞቱ

    ኢራን ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ በአልኮል መጠጥ መመረዝ ምክንያት ከ600 ሰዎች በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቷ የፍትህ ቃል አቀባይ አስታወቁ።

    ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች 3 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችም በህመም ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

    ግለሰቦቹ ከኮሮናቫይረስ ይጠብቀናል በሚል የተሳሳተ አመለካከት ደህንነቱ ያልተጠበቀ አልኮል ይጠጡ ነበር ተብሏል።

    በሕገ ወጥ መንገድ አልኮል ሲያመርቱ የነበሩ በርካታ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    በኢራን እስካሁን ከ62 ሺህ 500 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እየቀነሰ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

  12. በኮሮናቫይረስ ጥርጣሬ ግለሰቡ ፍቅረኛውንና እራሱን አጠፋ

    በኢሊኖይ ግዛት ነዋሪ የሆኑት ፍቅረኛሞች ሁለቱም ላይመለሱ አሸልበዋል። ለሁለቱም ሞት ምክንያቱ ኮሮናቫይረስ እንደሆነ ፖሊስ ጠርጥሯል።

    ቼሪል የፓትሪክ ፍቅረኛው ናት።

    ባለፈው ሐሙስ ፓትሪክ ፍቅረኛው ቼሪልን ከጀርባዋ በጥይት ደብድቦ ገድሏታል። እሷን ከገደለ በኋላ ታዲያ ለራሱም አልሳሳም።

    ፓትሪክ የ54 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ቼሪል 59 ዓመቷ ነው።

    ሬሳቸው በሎክቶፕ ታውንሺፕ አካባቢ በሚገኘው ቤታቸው በተለያየ ክፍል ውስጥ ተገኝቷል።

    ሽጉጡ ከፓርትሪክ እጅ አጠገብ የተገኘ ሲሆን የመጀመርያ ዙር ምርመራ ያመላከተው እሱ እሷን ስለመግደሉ ነው።

    የፓትሪክ ቤተሰቦች ልጃችን ከደወለ ቆየ፤ በሚል ሪፖርት በማድረጋቸው ነው አስከሬኖቹ ሊገኙ የቻሉት።

    የእርሱ ቤተሰቦች ኋላ ላይ በሰጡት ቃል እሱና ፍቅረኛው በኮሮናቫይረስ ሳንያዝ አንቀርም በሚል ስጋት ውስጥ እንደነበሩ መስክረዋል።

  13. የኮሮናቫይረስ ታማሚዋ በለይቶ ማከሚያ ውስጥ ወለደች

    በካሜሩን መዲና ያውንዴ፤ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆና የህክምና ክትትል እየተደረገላት የምትገኝ እናት ሴት ልጅ መገላገሏን አንድ የሆስፒታሉ ሐኪም ለቢቢሲ ገለጹ።

    ይህች የ19 ዓመቷ እናት በሰላም ከወለደች በኋላ ከልጇ ጋር እንዲለያዩ ተደርጓል።

    ማሪ የተባለችው ታማሚ ምጥ የጀመራት ለመተንፈስ የሚረዳት ኦክስጅን እየተሠጣት ሳለ ነበር።

    በያውንዴ ሆስፒታል የማህጸን ሃኪም የሆኑት ዶ/ር ያኔው ጋሃ ቦንጃ “የተለየ ክፍል አዘጋጀንላትና ኦክስጅን እንደተገጠመላት አልጋዋ ላይ በሰላም ተገላገለች” ሲሉ ተናግረዋል።

    ህጻኗ ያለ ጊዜዋ የተወለደች ሲሆን ስትወለድ 2.1 ኪሎ ግራም ትመዝን ነበር። በዚህመ ምክንያት በማሞቂያ ክፍል እንድትቆ ተደርጓል።

    ምርመራ እየተካሄደላት በመሆኑ እስካሁን ህጻኗ በቫይረሱ መያዝ አለመያዟ አልታወቀም። ነገር ግን የእናቷን ጡት እንድትጠባ ተደርጓል።

    ዶ/ር ያኔው እንዳሉት እናት ህክምናዋን እየተከታተለች ቢሆንም ቤተሰቦቿ ወደ ለይቶ ማከሚያው ክፍል ስለማይገቡ ብቸኝነት ተሰምቷታል።

    “ማሪ በተፈጥሯዊ መንገድ በመውለዷ እድለኞች ነን፤ በምጥ ባትወልድ ኖሮ በጣም በፍጥነት በቀዶ ሕክምና ማዋለድ ይጠበቅብን ነበር” ብለዋል- ዶክተሩ።

    በቫይረሱ የተያዙ ነፍሰጡር ሴቶች መደናገጥ እንደማገባቸው ዶክተሩ አሳስበዋል።

    በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ካሜሩን እስካሁን 658 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 6 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

  14. የስፔን ላ ሊጋ በግንቦት ወር ሊጀመር ይችላል ተባለ

    ያለው ሁኔታ በቅርቡ የሚስተካከል ከሆነ የስፔን የላ ሊጋ ውድድር በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ሊጀመር እንደሚችል የሊጉ ፕሬዝዳንት ዣቪየር ቴባስ ተናገሩ።

    በመጋቢት ወር ላይ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሊቨርፑል ጋር አንፊልድ ላይ አድርጎት በአሸናፊነት ከወጣበት የእግር ኳስ ግጥሚያ ወዲህ የትኛውም የስፔን ቡድን ጨዋታ ሳያደርግ ቆይቷል።

    የላ ሊጋው ፕሬዝዳንት ቴባስ በኢንተርኔት አማካይነት ከዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ጋር በካሄዱት ወይይት ላይ እንደተናገሩት የዓመቱ ውድድር ተመልሶ የማይጀመር ከሆነ የሊጉ ቡድኖች 1 ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ኪሳራ ይገጥማቸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም:

    • ውድድሩ በግንቦት መጨረሻ ወይም በሠኔ መጀመሪያ ላይ ሊጀመር ይችላል።

    • ጨዋታዎች በዝግ ስታዲየምና በተወሰነ የተመልካች ብዛት ብቻ ሊካሄዱ ይችላሉ።

    • ላ ሊጋው ከስፖንሰርሽፕና ከትኬት ያገኝ የነበረውን 150 ሚሊዮን ዩሮ አጥቷል።

    • የስፔን እግር ኳስ ማኅበር ከአገሪቱ መንግሥት ምንም አይነት ገንዘብ አይጠይቅም።

    • በአንደኛና በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚገኙ ስምንት ቡድኖች ተጫዋቾችን ቀንሰዋል።

  15. ፓሪስ በቀን መሮጥን ከለከለች

    የፈረንሳይ ዋና መዲና ፓሪስ ባለሥልጣናት የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ከሰዎች ጋር የሚኖርን ንክኪ ለመቀነስ ቀን ቀን ለአካላዊ እንቅስቃሴ የሚደረግ ሩጫን መከልከሉን አስታወቁ።

    ፈረንሳይ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ብትጥልም፤ ዱብ ዱብ ለማለት ከቤት መውጣት ግን የተፈቀደ ነበር።

    ይሁን እንጅ በርካታ ሰዎች በቀን አካላዊ እርቀታቸውን ሳይጠብቁ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው የፓሪስ ሐኪሞች ላይ ስጋት ፈጥሯል።

    ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሰዎች በቀን ውስጥ የሚሰሩትን የአካል እንቅስቃሴ በማሳበብ ከቤት እንደሚወጡ ባለሥልጣናት ጥርጣሬ አድሮባቸዋል።

    በዚህም ምክንያት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ ለአካላዊ እንቅስቃሴ ከቤት ወጥቶ መሮጥ የሚከለክል እገዳ ጥሏል።

    በፓሪስ ባለፈው ሳምንት ጀምሮ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

  16. የኮቪድ-19 ምልክቶችና እራሳችንን የምንጠብቅበት መንገድ

    ኮሮናቫይረስ ሳንባን የሚያጠቃ በሽታ ነው። የበሽታው ዋነኛ ምልክቶች ደግሞ ትኩሳትና ደረቅ ሳል ሲሆኑ በአንዳንድ ሰዎች ላይ የመተንፈስ ችግርን ያስከትላሉ።

    የሰውነትዎ ትኩሳት ከ37.8 ሴሊሸስ በላይ ከሆነና አዲስ የጀመረዎ ሳል ደረቅና የማያቋርጥ ሊሆን ይችላል። ይህም ያለመቋረጥ ከአንድ ሰዓት በላይ ማሳል ወይም በ24 ሰዓታት ውስጥ ከሦስት ጊዜ በላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሳል የበሽታው ምልክት ነው።

    ታዲያ እራሳችንን ከወረርሽኙ እንዴት መጠበቅ እንችላልን? ዋነኛው መንገድ እጅን በውሃና በሳሙና በድንብ አድርጎ በተደጋጋሚ መታጠብ ነው።

    በሽታው ያለበት ሰው በሚያስልበት ጊዜ በሚወጡት ጥቃቅን ጠብታዎች አማካይነት ቫይረሱ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ይተላለፋል።

    ጥቃቅን ጠብታዎቹ ወደ ሌላ ሰው አፍና አፍንጫ በመግባት ወይም ያረፉበትን ቦታ ከነኩ በኋላ ዓይንን፣ አፍንጫንና አፍን በመንካት ለበሽታው ልንጋለጥ እንችላል።

  17. ኡጋንዳ የህዝብ እንቅስቃሴ ማገዷን ተከትሎ የቤት ውስጥ ጥቃቶች መጨመራቸው ተገለፀ

    ኡጋንዳ ለሁለት ሳምንት ያህል የደነገገችውን የቤት ውስጥ መቀመጥ እወጃዋን ተከትሎ የቤት ውስጥ ጥቃቶች መበራከታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

    የፖሊስ ቃል አቀባይ ፍሬድ ኤናንጋ እንደገለፁት አራት ግለሰቦች በግድያ ተጠርጥረው መያዛቸውን ገልፀዋል።

    በኡጋንዳ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራትም የቤት ውስጥ ጥቃቶች እየጨመሩ መሆናቸውም ሪፖርቶች ያሳያሉ።

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኮሮና ወረርሽኝ መዛመት ጋር በተያያዘ በአለም አቀፍ ሁኔታ የቤት ውስጥ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

    መንግሥታትም እነዚህን ጥቃቶች ችላ እንዳይሉና ጥቃት አድራሺዎቹንም ወደ ህግ እንዲያቀርቡ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ከሰሞኑም የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የወረርሽኙ መዛመትን ተከትሎ እየተበራከተ የመጣውን የቤት ውስጥ ጥቃት አሳዛኝ ብለውታል፤ " ለጥቃት ምንም ምክንያት የለውም ብለዋል።

  18. ሰበር, የዘጠኝ ወር ህፃንን ጨምሮ ተጨማሪ ስምንት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተያዙ

    በኢትዮጵያ የዘጠኝ ወር ህፃንን ጨምሮ ተጨማሪ ስምንት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት በባለፉት 24 ሰዓታት የላብራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 264 ሰዎች መካከል ስምንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ከእነዚህም መካከል አንደኛው የዘጠኝ ወር ህፃን ሲሆን በተደረገላቸው ምርመራ እሱም እናቱም ተገኝቶባቸዋል። ምርመራ ከተደረገላቸው መካከል አንዱ ኤርትራዊ ሲሆን ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

    ይህም በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 52 አድርሶታል ነው ያሉት ሚኒስትሯ። በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠ ስምንቱ ሰዎች መካከል አምስቱ ከዱባይ የመጡና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል ሲደረግላቸው የነበሩ ናቸው።

    ከእነዚህም ውስጥ አንድ የ25 ዓመት ሴት ኢትዮጵያዊት ከታይላንድ መጥታ በለይቶ ማቆያ ክትትል ስታደርግ የነበረች ሲሆን፤ አንድ የ19 ዓመት ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ጉዞ ታሪክ የሌለው ሲሆን የንክኪ ሁኔታውም በመጣራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

    ወጣቱ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳለው ተጠርጥሮ በለይቶ ማቆያ የነበረ ነው።

    ሌላኛዋ የ30 ዓመት ሴት ኤርትራዊት ስትሆን ከእንግሊዝ ለንደን መጥታ አዲስ አበባ ውስጥ በለይቶ ማቆያ ክትትል እያደረገች የምትገኝ ነበረች።

    በአዲስ አበባ እና በሌሎች የክልል ከተሞች የኮሮናቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ አቅም እየጨመረ መጣቱም ገልጸዋል።

    በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።

    አራት ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፤ ሁለት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል። ሌላ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ወደ ሀገራቸው ተሸኝተዋል።

  19. ጃፓን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች

    የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በቶኪዮ፣ በባህር ዳርቻዋ ከተማ ኦሳካ እንዲሁም በሌሎች አምስት ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገጉ።

    አዋጁ ከእሮብ ዕለት ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆን ሲሆን ለአንድ ወር ይቆያል ተብሏል።

    የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ትምህርት ቤቶችንና የንግድ ተቋማትን መዝጋት ይችላሉ የተባለ ቢሆንም ባለስልጣናቱ ግን ዜጎች ቤታቸው እንዲቀመጡ የማዘዝ ስልጣን የላቸውም ተብሏል።

    ነገር ግን አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ከዘገየ የተወሰደ ነው ሲሉ ተችተዋል።

    ጃፓን ከሌሎች አገራት አንጻር ሲነፃፀር አነስተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ ቢያዝም በሚቀጥሉት ሳምንታት ግን በቶኪዮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታማሚ ሊመዘገብ እንደሚችል ተገምቷል።

    እስካሁን ድረስ በጃፓን በኮቪድ-19 ምክንያት 85 ሰዎች ሲሞቱ በቶኪዮ ብቻ 1ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል።

    አሜሪካና ጀርመን፣ ጃፓን አካላዊ ርቀትን ማስፈፀም ባለመቻሏና በስፋት ምርመራ ባለማድረጓ አምርረው ሲተቿት ነበር።

    በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የቶኪዮ ኦሎምፒክ በአንድ ዓመት መተላለፉ ይታወቃል።

  20. በአፍሪካ 10 ሺህ ገደማ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል

    እስካሁን ድረስ 52 የአፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንደሚገኙባቸው ታውቋል። የአፍሪካ ሕብረት በሽታ መቆጣጠርያና መከላከያ ማዕከል እንዳስታወቀው በአፍሪካ 9,457 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በአፍሪካ እስካሁን ድረስ 442 ሰዎች ሲሞቱ 800 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

    በሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ ሶስት ሰዎች መያዛቸው ከታወቀ በኋላ፣ በአፍሪካ እስካሁን ድረስ አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱን ያላስመዘገቡ አገራት ኮሞሮስ፣ ሌሴቶ ብቻ ሆነዋል።

    የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት እንዳሉት ከሆነ አፍሪካ የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት 100 ቢሊየን ዶላር ትፈልጋለች።

    እኚህ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ከፍራንስ 24 ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ እንደገለፁት፣ አፍሪካ በማህበራዊና በምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮች በርካታ ጥረት ብታደርግም አሁንም ግን " አቅሟ ደካማ ነው" ብለዋል። ዝርዝሩን እዚህ ያገኙታል፡ በአህጉረ አፍሪካ 10 ሺህ ገደማ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል