ኮሮናቫይረስ፡ የዓለም ጤና ድርጀት አፍሪካ የክትባት መሞከሪያ አትሆንም አለ

ታትሟል

በሁለት የፈረንሳይ ተመራማሪ ሐኪሞች የተሰጠውን የኮቪድ-19 ክትባት በአፍሪካ መሞከር አለበት የሚል ሃሳብ የዓለም ጤና ድርጅት ጄነራል ዳይሬክተር " ዘረኛ" ሲሉ ተቹ።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም " አፍሪካ ለማንኛውም ክትባት መሞከሪያ አትሆንም፣ መሆንም የለባትም" ብለዋል።

የሕክምና ባለሙያዎቹ ክትባቱ መሞከር ስላለበት ጉዳይ አስተያየት የሰጡት በቴሌቪዥን ይካሄድ በነበረ የቀጥታ ክርክር ወቅት ነው። ይህ የሐኪሞቹ አስተያየት ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን አፍሪካውያንንን " መሞከሪያ አይጥ" አድርጎ ማሰብ ነው ብሏቸዋል።

ከዚህ አስተያየት በኋላ አንዱ ህክምና ባለሙያ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ስለኮሮናቫይረስ መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት ስለጉዳዩ ሲጠየቁ መናደዳቸው ተስተውሏል።

ከዚያም " የቅኝ ግዛት አብሾ" አልለቀቃቸውም ሲሉ መልሰዋል።

" በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሳይንቲስት እንዲህ አይነት አስተያየት መስማት የተዋረደ፣ አሳፋሪ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገርን በማንኛውም ሁኔታ እናወግዛለን። እናም የማረጋግጥላችሁ ነገር ይህ በጭራሽ አይሆንም" ብለዋል።

ሁለቱ ተመራማሪ ሕክምና ባለሙያዎች በፈረንሳይ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተዘጋጀ የክርክር መድረክ ላይ ቀርበው በአውሮፓና በአውስትራሊያ ስለሚደረግ የክትባት ሙከራ እያወሩ ነበር።

ከዚያም ከተወያዮቹ መካከል አንዱ የሆኑት ዤን ፖል ሚራ " ይህንን ሙከራ ግን አፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም ሕክምና በሌለበት አፍሪካ ውስጥ ማካሄድ የለብንም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጡ።

አክለውም " ከዚህ በፊት ኤድስ ላይ እንደተደረገው ምርመራ፣ በወሲብ ንግድ የተሰማሩት የበለጠ ተጋላች በመሆናቸው እነሱ ላይ እንደተሞከረው ማለት ነው። ምክንያቱም ከፍተኛ ተጋላጭ ስለሆኑና ራሳቸውን መከላከል ስለማይችሉ ማለት ነው"

ከዚያም በጉዳዩ ላይ እየተወያዩ የነበሩት ዶ/ር ሎሼት በመስማማት አንገታቸውን ነቅንቀው" ልክ ብለሃል። በአፍሪካ በተመሳሳይ ወቅት ምርምር ለማድረግ እያሰብን ነው" ሲሉ ተናገሩ።

ዶ/ር ሚራ አስቀድሞ ምርምራቸው በአውሮፓና በአውስትራሊያ መስራቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልፀው ነበር። ለዚህም ምክንያት ያሉት የግል መከላከያ ስለሚጠቀሙ የሚል ነበር።

ይህ የሁለቱ ሕክምና ባለሙያዎች አስተያየት በበርካቶች ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን የቀድሞ እግርኳስ ተጫዋች ዲዲየር ድሮግባ " እጅግ ዘረኛ" በሚል ተችቶታል።

አክሎም " አፍሪካውያንን እንደ ቤተ ሙከራ አይጥ አትውሰዱን፤ በጣም አሳፋሪ ነው" ብሏል።

ሳሙዔል ኤቶም ዶክተሮቹን " ነፍሰ በላዎች" ብሏቸዋል።

ይህ የሕክምና ባለሙያዎቹ አስተያየት አፍሪካና አፍሪካውያን ለኮሮናቫይረስ ክትባት መሞከሪያ ይሆናሉ የሚለውን ስጋት አባብሶታል።