ቡርኪናፋሶ ውስጥ ታግተው የነበሩት አሜሪካዊት መነኩሴ ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, FBI
ታትሟል
ባለፈው ሚያዝያ ወር ቡርኪናፋሶ ውስጥ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አንድ አሜሪካዊት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መነኩሴ መለቀቃቸውን የሰሜን ምስራቅ ካያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አስታወቁ።
ጳጳሱ ቴዎፍሎስ ናሬ በሰጡት መግለጫ “እህት ሱሌን በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ጤንነት ብሎም ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ላይ ይገኛሉ’’ ሲሉ ተናግረዋል።
የ83 ዓመቷ ሱሌይን ቴንሰን የሚጠቀሙበትን መነፅር ብሎም ለደም ግፊት የሚወስዱትን መድሀኒት ሳይዙ እኩለ ሌሊት ላይ ነበር በአካባቢው ከሚኝ ደብር ታግተው የተወሰዱት።
አጋቾቹ ታጣቂዎች ከመሆናቸው ባሻገር እስካሁን ድረስ ማንነታቸው አልታወቀም። ነገር ግን በቡርኪናፋሶ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ጥቃትም ይፈጽማሉ።
ጳጳስ ናሬ መነኩሴዋ ሱሌን እንዲለቀቁ ያስቻለው ሁኔታ ምን እንደሆነ ምንም አይነት መረጃ የለኝም ብለዋል። ኤፍቢአይ ከእገታው በኋላ የመነኩሴዋን መጥፋት የሚገልጽ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር።
ከአልቃይዳ እና አይ ኤስ ጋር የሚተባበሩ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን በቡርኪናፋሶ እና በአጎራባች ሀገራት በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚጥቃት እና አፈና ሲፈጽሙ ይስተዋላል።
የአካባቢው መንግስታት በታጣቂ ቡድኖቹ ላይ ተደጋጋሚ የማጥቃት ዘመቻዎችን ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል።








