ሜሲ ወይስ ሞድሪች? ፈረንሳይ አሊያ ሞሮኮ? አዲስ ታሪክ የሚፃፍበት የዓለም ዋንጫ ወደየት ያመራ ይሆን?

እንግሊዝ ቅዳሜ ምሽት በፈረንሳይ ተረትታ በበነጋው አውሮፕላን ተሳፍራ ከዶሃ ወጥታለች።
አሁን አራት ብሔራዊ ቡድኖች ቀርተዋል - ፈረንሳይ፣ ሞሮኮ፣ ክሮሺያ እና አርጀንቲና። ከአራቱ አንዱ በሚቀጥለው እሑድ ወርቃማውን ዋንጫ ያነሳል።
እኚህ አራት ቡድኖች ለግማሽ ፍፃሜ ይደርሳሉ ብሎ የገመተ ጥቂት ነው። አራቱም ብሔራዊ ቡድኖች አዲስ ታሪክ ሊፅፉ ከጫፍ ደርሰዋል።
ሌዮኔል ሜሲ
አርጀንቲናዊው ኮከብ በእግር ኳስ ሕይወቱ የመጀመሪያው እና የመጨረሻውን የዓለም ዋንጫ ሊያነሳ ይችላል።
ሜሲ ለዋንጫ ብርቅ አይደለም። 10 የስፔን ላሊ ጋ ዋንጫ፣ አራት ጊዜ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ አንድ ጊዜ የፈረንሳይ ሊግ እንዲሁም ከአገሩ አርጀንቲና ጋር ኮፓ አሜሪካን አንስቷል።
ሜሲ የእግር ኳስ ከዋክብት ጉምቱው ሽልማት የሚባለውን ባሎን ዶር ሰባት ጊዜ በማንሳት ክብረ-ወሰን ጨብጧል።
ነገር ግን የ35 ዓመቱን የእግር ኳስ ተዓምረኛ ከማራዶና እና ከፔሌ የሚለየው የዓለም ዋንጫን አለማንሳቱ ነው።
አርጀንቲና በዲዬጎ ማራዶና እየተመራች የዓለም ዋንጫ ካነሳች 36 ዓመታት ተቆጥረዋል። ሜሲ ይህን ይደግመው ይሆን? የዓለም ዋንጫ ማንሳቱስ የዘመናችን ድንቁ ተጫዋች የተሰኘውን ስያሜ ያሰጠው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሞሮኮ
ሞሮኮ ከወዲሁ ታሪክ ሰርታ፤ እንዲሁም ጨምራ ሌላ ታሪክ እየፃፈች እዚህ ደርሳለች።
ሞሮኮ ከአህጉረ አፍሪካ፣ አልፎም ከአረቡ ዓለም ለግማሽ ፍፃሜው የደረሰች የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
ምንም እንኳ ሞሮኮ እንደ አሽራፍ ሐኪሚ እና ሐኪም ዚዬች ያሉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሯትም እዚህ ትደርሳለች ብለው የገመቱ ጥቂት ናቸው።
ክሮሺያ እና ቤልጂዬም የነበሩበትን ምድብ አልፋ፣ ኃያሏ ስፔንን አስወግዳ፣ ፖርቹጋልን አሰናብታ ነው እዚህ የደረሰችው።
የአትላስ አናብስት የጎል መስመራቸውን ሲከላከሉ ያለ እረፍት ነው። በኳታር የዓለም ዋንጫ ማንም የሞሮኮን መረብ አልደፈረም። ከአንድ ጎል በቀር። እሱም በራስ ላይ የተቆጠረ ነው።
ሞሮኮ የዓለም ዋንጫ ድምቀት ሆናለች። ደጋፊዎች ስታደየሙን ከጫፍ ጫፍ ሞልተው ያለማቋረጥ ቡድናቸውን ይደግፋሉ።
ሞሮኮ ረቡዕ ዕለት አዲስ ታሪክ ትፅፍ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳይ
ፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ በተከታታይ ሁለት ጊዜ ታነሳ ይሆን?
አውሮፓዊቷ አገር የዓለም ዋንጫውን በተከታታይ ሁለት ጊዜ እንዳታነሳ ታሪክ ሠሪዋ ሞሮኮ ልታግዳት ትችላለች።
'ሌ ብሉ' በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ፈረንሳዮች፣ ከስድሳ ዓመታት በኋላ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ይሞክራሉ።
ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ በተከታታይ የዓለም ዋንጫ ያነሳችው ብራዚል ስትሆን፣ ይህ ከሆነ 60 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ጣልያን፣ ስፔን፣ ጀመርን ባለፉት 12 ዓመታት ዋንጫ አንስተው በሚቀጥለው የዓለም ዋንጫ ውድድሩን በጊዜ የተሳነበቱ አገራት ናቸው።
ባለፈው ቅዳሜ እንግሊዝን የረታችው ፈረንሳይ ከብራዚል ቀጥላ ዋንጫ ባነሳች ተከታ የዓለም ዋንጫ ውድድር ለግማሽ ፍፃሜ የበቃች አገር ሆናለች።
አሠልጣኝ ዲዲዬ ዴሾ አሁን ትኩረታቸው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ሆናለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክሮሺያ
የ2018 ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታን ደግመን ልናየው እንችል ይሆናል።
ፈረንሳይ ሞሮኮን፤ ክሮሺያ ደግሞ አርጀንቲናን ካሰናበቱ በሩሲያ ያሳዩንን የፍፃሜ ጨዋታ በኳታር ምድር ይደግሙታል።
ክሮሺያ በዙር 16 ጃፓንን፤ በሩብ ፍፃሜው ደግሞ ብራዚልን በመርታት ነው ከመጨረሻዎቹ አራት ቡድኖች ተርታ መሰለፍ የቻለችው።
ክሮሺያ ለመጨረሻ ጊዜ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ በ90 ደቂቃ ተጫውታ ያለፈችው ከ24 ዓመታት በፊት ጀርመንን በረታች ወቅት ነው።
የክሮሺያ አምበል እና የመሃል መስመሩ ሞተር፤ ሉካ ሞድሪች ዕድሜው 37 ደርሷል። ነገር ግን 120 ደቂቃ ተጫውቶ አገሩን ለዚህ አብቅቷል።
ባለፈው የዓለም ዋንጫ በምድብ ጨዋታ በክሮሺያ 3 ለምንም የተረታችው አርጀንቲና ለሞድሪች ቡድን ንቀት እንደማታሳይ ይጠበቃል።
አርጀንቲና ከክሮሺያ ማክሰኞ ምሽት 4 ሰዓት ይገናኛሉ፤ ፈረንሳይ ከሞሮኮ ደግሞ ረቡዕ በተመሳሳይ ሰዓት ይፋለማሉ።
አዲስ ታሪክ ይመዘገብ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












