“የዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ አዝጋሚ ነው፤ ፊልም አይደለም” ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ

ዩክሬን በሩስያ ወረራ የተያዙባትን ግዛቶች ለማስመለስ የምታደርገው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነና የዘገየ መሆኑን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አመኑ።
ዩክሬን በሩስያ ላይ የምታደርገው የመልሶ ማጥቃት ከተጀመረ ሳምንታትን አስቆጥሯል።
“አንዳንድ ሰዎች እያደረግነው ያለው ዘመቻ የሆሊውድ ፊልም ነው ብለው ያምናሉ። እናም ውጤቱን ወዲያውኑ ይጠብቃሉ። ይህ ፊልም አይደለም” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዚህ ጦርነት እየገበርን ያለነው የሰዎች ህይወት ነው” ብለዋል።
ዩክሬን ሳምንታት በፈጀው መልሶ ማጥቃት እስካሁን ድረስ በደቡብ ዛፖሪዝህዚህያ እና በምስራቅ ዶኔትስክ የሚገኙ ስምንት መንደሮችን ማስመለሷን ገልጻለች።
የሩስያ ኃይሎች በዩክሬን የተቋጠጠሯቸው ግዛቶች 200 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር መሬት የሚሸፍን መሆኑ ጋር ተያያይዞም ሩስያን መግፋቱ ቀላል እንዳልሆነም ነው ፕሬዚዳንቱ ያስረዱት።
“ አንዳንዶች የሚፈልጉት ምንም ይሁን ምን፣ በእኛ ላይ ጫና ለማሳደር የሚሞክሩትን ጨምሮ ከአክብሮት ጋር የጦር ሜዳ ግስግሴያችንን የምናካሂደው እንዳመቸን ነው” ብለዋል።
አገራቸው ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጸጥታ ዋስትና እንዲሰጣት የጠየቁት ፕሬዚዳንቱ የመጨረሻ ግባቸው ግን የመከላከያ ህብረቱ ኔቶ አባልነት መሆኑንም አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ በሚቀጥለው ወር በሊቱዌኒያ በሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ዩክሬንን ለመጋበዝ ምንም ዓይነት እቅድ እንደሌለ በዚህ ሳምንት በግልጽ ተናግረዋል።
"[ጄንስ] ስቶልተንበርግ አቋሜን ያውቀዋል። በተደጋጋሚ ነግረናቸዋል። እቅዳችንን አታበላሹት” ብለናቸዋል ሲሉም ዘለንስኪ አስረድተዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በድጋሜ አገራቸው አሜሪካን ሰራሹ ኤፍ 16 አውሮፕላን በጥብቅ እንደሚያስፈልጋት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ተዋጊ አብራሪዎቹ ነሐሴ ወር ስልጠና ሊጀምሩ እንደሚችሉ ጠቁመው የመጀመሪያዎቹ ጄቶች ከስድስት እና ከሰባት ወራት በኋላ ሊደርሱ እንደሚችሉም ተናግረዋል።.
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት በለንደን የተደረገ ጉባኤን ለመካፈል በመጡበት ወቅት ነው።
የግሉ ሴክተር ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት የሚጫወተው ሚናን በተመለከተም ጉባኤው መክሯል። በለንደን ቆይታቸውም ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ጋር ተወያይተዋል።
የዩክሬን ምጣኔ ኃብት በባለፈው ዓመት 29.2 በመቶ መቀነስ ያሳየ ሲሆን አገሪቱን መልሶ ለመገንባት እና ለማገገም 411 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም የዓለም ባንክ ግምቱን አስቀምጧል።












