ኔታንያሁ የጋዛ ጦርነት ተገቢነት ባስረዱበት የአሜሪካው ጉዟቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የሚያደርጉትን ጦርነት ድጋፍ ለማግኘት “ጠላቶቻችን ጠላቶቻችሁ ናቸው” ሲሉ ለአሜሪካ ምክር ቤት ንግግር ያደረጉ ሲሆን በካፒቶል ሂል እና በውጭ በርካቶች የተቃውሞ ሰልፎች አካሂደዋል።

"ኢራንን ስንዋጋ በጣም አክራሪ እና ገዳይ የሆነውን የዩናይትድ ስቴትስን ጠላት ነው የምንዋጋው" ብለዋል ኔታንያሁ።

“ትግላችን የናንተም ትግል ነው፤ ድላችንም የእናንተ ድል ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

የእስራኤሉ መሪ ለአራተኛ ጊዜ በኮንግረሱ የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ከአብዛኛዎቹ የሪፐብሊካን ፖለቲከኞች ደማቅ አቀባበል ተደረጎላቸው።

በጋዛ ጦርነት ምክንያት እየጨመረ ባለው የፖለቲካ ክፍፍል በርካታ የኮንግረሱ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ሆን ብለው በስብሰባው ያልተገኙ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በጎዳናዎች ላይ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ የተጠየቀውን የእስር ማዘዣ መነሻ በማድረግ የእስራኤሉን መሪ "ታዳኝ የጦር ወንጀለኛ" ብለው የሚገልጹ ጽሑፎችን የያዙትን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎች በካፒቶል ሂል ለተቃውሞ ወጥተዋል።

በካፒቶል ህንጻ ውስጥ የኔታንያሁን ንግግር ለማደናቀፍ የሞክሩ 5 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ኔታንያሁ ተቃዋሚዎችን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር “በይፋ የኢራን መጫወቻ ሆናችኋል” ብለዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራንን በተመለከተ ከሰጡት ብዙ ሃሳቦች በአንዱ አሜሪካን፣ እስራኤልን እና የአረቡን ዓለምን የሚያስፈራራ “የሸብር መረብ” ከማለት ባለፈ “በስልጣኔ እና አረመኔያዊነት መካከል የሚደረግ ግጭት” በማለት ገልጸዋል።

ቃሉ ኢራን የገለፀችውን "የትግል መረብ" በማለት የገለጸችውን እና የፍልስጤሙን ሃማስ፣ የሊባኖሱን ሂዝቦላህ እና በየመን የሚንቀሳቀሱትን ሁቲዎችን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ጥምረት የሚያሳይ ነው።

በኢራን የሚደገፉ ሃይሎች በአሜሪካን ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን እና "አሜሪካን ለመቃወም መጀመሪያ መካከለኛውን ምስራቅን ማሸነፍ እንደሚያስፈልግ" ኢራን ታምናለች ብለዋል።

በርካታ ሰዎች ለተቃውሞ ወጥተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኔታንያሁ ከአንድ ሰዓት በላይ በቆየው ንግግራቸው የእስራኤልን ትችት በመቃወም በጋዛ ላይ ያለው ጦርነት የአገራቸው የህልውና ትግል አድርገው በማቅረብ ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

ለአስርት ዓመታት “ለጋስ ለሆነው ወታደራዊ እርዳታዋ” አሜሪካንን አመስግነዋል፤ እስራኤል ደግሞ በምላሹ “የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያተረፈ” ወሳኝ የስለላ መረጃ ለአሜሪካ ሰጥታለች ብለዋል።

የጋዛን ጦርነት ፍጻሜ ስለሚያፋጥን እና ሰፊ ክልላዊ ጦርነት እንዳይፈጠር ይረዳል በማለትም የአሜሪካን ወታደራዊ እርዳታ “ፈጣን” እንዲሆን ጠይቀዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል ለአሜሪካ ህዝብ ያቀረቡትን ጥሪ በመጥቀስ “መሳሪያውን ስጡን ሥራውን እኛ እንጨርሰዋለን” ብለዋል።

እስራኤል ለእያንዳንዱ ሰው ሦስት ሺህ ካሎሪ የሚሆን በቂ የምግብ ዕርዳታ ታቀርባለች ከማለት በስተቀር በጋዛ ስላለው ሰብዓዊ ቀውስ በሰፊው አልተናገሩም። የጋዛ ነዋሪዎች ምግብ እያገኙ ካልሆነ "ሃማስ ስለሚሰርቀው" ነው ብለዋል።

ከጦርነቱ በኋላ በጋዛ ሰርጥ ስለሚኖረው ሁኔታ ሲገልጹም “ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ እና ከጽንፈኝነት የተላቀቀ” ግዛት ሆና በእስራኤል ጦር ስር ትቀጥላለች ሲሉ ተናግረዋል።

"ጋዛ እስራኤልን ለማጥፋት በማይፈልጉ ፍልስጤማውያን የሚተዳደር የሲቪል አስተዳደር ሊኖራት ይገባል:: ይህ ብዙም የሚያጠያይቅ አይደለም::" ብለዋል።

ኔታንያሁ ደማቅ አቀባባል ቢያገኙም ቢያንስ 39 የሕግ አውጭዎች አለመኖራቸውን ሊሸፍነው አልቻሉም።

ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ደግሞ ዴሞክራቶች ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት የቀድሞዋ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ጠቅላይ ሚንስትሩ መጎብኘታቸው “አግባብ አይደለም” ብለዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቷ ካማላ ሃሪስ ያልተገኙት ደግሞ በፕሮግራም መደራረብ ምክንያት መሆኑ ተዘግቧል።

በንግግራቸው ሁሉ የሚቺጋኗ ዲሞክራት ራሺዳ ጠላይብ (የመጀመሪያዋ ፍልስጤማዊት-አሜሪካዊት የኮንግረስ አባል ናቸው) "የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ" እና "የጦር ወንጀለኛ" የሚል ጽሁፍ ይዘው ታይተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ ሊመለሱ እንደሚችሉ የተረዱት ቤንያሚን ኔታንያሁ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የአሜሪካን ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም ስላዘዋወሩ እና እስራኤል በ1967 ከሶሪያ በወረራ የነጠቀችውን የጎላን ሃይትስን የእስራኤል ሉዓላዊነት ግዛት አካል አድርገው ዕውቅና በመስጠታቸው አመስግነዋቸዋል።

ሁለቱ መሪዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ ፍሎሪዳ ውስጥ ይገናኛሉ።

በእስራኤል የሚገኙ እና አሁንም በጋዛ የሚገኙ የታጋቾች ቤተሰቦች ንግግሩን በቀጥታ ሲተላለፍ ቴል አቪቭ በሚገኘው የታጋቾች አደባባይ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ ተሰባስበዋል።

የእስራኤልን ብሔራዊ መዝሙርን ከዘመሩ በኋላ ተበታትነዋል።

ንግግሩ እንደተጠናቀቀ የእስራኤል ጦር ማያ ጎረን እና ኦረን ጎልዲን የተባሉ ሁለት ታጋቾችን አስከሬን ከጋዛ ማግኘቱን አስታውቋል።

ዜናው ለወራት የዘለቀው የእገታ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ በመቆየቱ፤ ብዙ ቤተሰቦች ታጋቾችን እንደገና በህይወት የማየት ተስፋ ስለማመንመኑ አጉልቶ አሳይቷል።