ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ታሊባን በሴቶች ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ አሳሰበ
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሴቶችና ልጃገረዶችን ኢላማ ያደረገውን የታሊባን መንግሥት ፖሊሲዎች አወገዘ።
ባለፈው ሳምንት ታሊባን ሴቶች ዩኒቨርሲቲ እንዳይገቡ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ እንዳይሰሩ አግዷል።
15 አባል አገራት ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት በአፍጋኒስታን እየጨመረ የመጣው በሴቶች ትምህርት ላይ የሚጣል እገዳ እንዳሳሰበው ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቅርቡ የተጣለው ገደብ መነሳት አለበት ብለዋል።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ በአፍጋኒስታን ያሉ ሴቶች ያልተገደበ፣ እኩልነት ያለበት እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጠይቋል።
መግለጫው ታሊባን ትምህርት ቤቶችን እንዲከፍት እና የሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነጻነቶችን የሚጋፉ ፖሊሲዎቹንና ተግባራቶቹን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ አሳስቧል።
በሴት የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ላይ የተጣለው ክልከላ የተባበሩት መንግሥታት የሚያካሂደውን ጨምሮ በአገሪቷ የሚካሄዱ ሰብዓዊ ተግባራት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብሏል መግለጫው።
ጉቴሬዝ በቅርቡ የተጣለው ክልከላ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል።
ሴቶችና ልጃገረዶችን ድምጽ ማፈን እና እንዳይሳተፉ ማድረግ ከፍተኛ ቀውስ የሚያስከትል ሲሆን የአፍጋኒስታን ሕዝብን አቅም ወደ ኋላ የሚመልስ ነው ሲሉም ጉቴሬዝ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በቅርቡ ሴቶች መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዳይሰሩ በታሊባን መንግሥት ከተከለከሉ በኋላ ቢያንስ አምስት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአፍጋኒስታን የሚያካሂዱትን ሥራ አቁመዋል።
ኬር ኢንተርናሽናል፣ ኖርዌጂያን ሬፊዩጂ ካውንስል እና ሴቭ ዘ ችልድረንም "ሴት ሠራተኞቻችን" በሌሉበት ሥራችንን መቀጠል አንችልም ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ሬስኩዩ ኮሚቴ በበኩሉ አገልግሎቱን ማቆሙን ያስታወቀ ሲሆን እስላሚክ ሪሊፍም አብዛኛውን ሥራውን ማቆሙን ገልጿል።
ታሊባን ባለፈው ሳምንት በአፍጋኒስታን ዋና መዲና ካቡል የሴቶች ትምህርት መታገዱን የሚቃወም ሰልፍ ላይ የተሳተፉ አምስት ሴቶችን አስሯል። ሦስት ጋዜጠኞችም እንዲሁ ታስረዋል።
ባለፈው ዓመት ታሊባን አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ ምንም እንኳን በ1990ዎቹ ዘመን ከነበረው በተሻለ ሕጋቸው ቀላል እንደሚሆን ቃል ቢገባም የሴቶችን መብቶችን ገድቧል።
በአብዛኛው የአገሪቷ ግዛቶች ልጃገረዶች የሚማሩባቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ሴቶች መናፈሻዎችና ጂምናዚየምን ጨምሮ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዳይገቡ ተከልክለዋል።