ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታሊባን ሴቶች መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዳይሠሩ ከለከለ
ታሊባን ሴቶች መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዳይሠሩ ማገዱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አወገዘ።
ተመድ ድርጊቱ መሠረታዊ መብቶችን የጣሰ ነውም ብሏል።
የእስላማዊው ቡድን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች ሂጃብ ባለመልበሳቸው የአለባበስ ሥርዓትን ጥሰዋል ሲል ውሳኔው ትክክል መሆኑን ገልጿል።
ይህ ሴት ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ከታገዱ ከቀናት በኋላ የተላለፈ አዋጅ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር “የአፍጋኒስታንን ሕዝብ የሚጎዳ ነው” ሲሉ ድርጊቱን ተችተዋል።
የቤተሰባቸው ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆኑ እና መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሴት አፍጋኒስታናዊያን በውሳኔው ፍርሃት እና አቅመ ቢስነት እንደተሰማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዷ "ወደ ሥራዬ መሄድ ካልቻልኩ ቤተሰቤን ማን ሊረዳቸው ይችላል?" ብላለች።
ሌላኛዋ ደግሞ የታሊባንን የአለባበስ ስርዓት ስታከብር እንደነበር ገልጻ ውሳኔውን “አስደንጋጭ” ብላዋለች።
ሦስተኛዋ ደግሞ ዕዳዋን ለመክፈል እና ልጆቿን ለመመገብ እንደምትቸገር በመግለጽ የታሊባንን "ኢስላማዊ ስነ-ምግባር" ዓላማ ጠይቃለች።
ሌላዋ ሴት ቃለ መጠይቅ የተደረገላት ደግሞ “ዓለም እየተመለከተን ምንም ነገር እየሠራ አይደለም" ብላለች። ሴቶቹን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲል ቢቢሲ ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
የቅዳሜው ትዕዛዝ ከኢኮኖሚ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ ለሃገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደርሷል።
በፍጥነት የማይተገብር ድርጅት ፈቃድ እንደሚሰርዝም ደብዳቤው አትቷል።
በደብዳቤው ማብራሪያው መሠረት ሴቶች ሂጃብ ባለመልበሳቸው የሸሪዓን ህግ እየጣሱ ነው ብሏል።
እርምጃው ዓለም አቀፍ ቁጣን ቀስቀሷል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጉዳዩ እጅጉን እንዳሳሰባቸው በመግለጽ “ለሚሊዮኖች አስፈላጊ እና የህይወት አድን እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋል” ብለዋል።
"ሴቶች በዓለም ዙሪያ ለሚከናወኑ የሰብአዊ ተግባራት ማዕከል ናቸው። ይህ ውሳኔ ለአፍጋኒስታን ህዝብ ከባድ ሊሆን ይችላል" ብለዋል ብሊንከን።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣንም "የሰብአዊ መብት መርሆዎችን በግልፅ የጣስ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች በሃገሪቱ የእርዳታ እና የልማት ሥራዎችን በማከናወን ትልቅ ቦታ አላቸው። ለጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት የሰብዓዊ ሃገራት ቡድን ለእሑድ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።
የሴቭ ዘ ቺልድረን ባልደረባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቡድኑ ከታሊባን ባለስልጣናት ጋር ለመገናኘት አቅዷል። ሴቶች እንዳይሠሩ ከተከለከሉ አንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሊዘጉ ይችላሉም ብለዋል።
ድርጅቶቹ ወንዶችን ብቻ እንዲቀጥሩ ከተፈቀደላቸው የአፍጋኒስታን ሴቶች እርዳታ በቀጥታ ማግኘት እንዳያገኙ ሊያደርግ ይችላልም ተብሎ ተሰግቷል። የታሊባን ህግ ወንዶች ከሴቶች ጋር እንዳይሰሩ ይከለክላል።
ሴት ሠራተኞች ሌሎች ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ለማግኘት "አስፈላጊ" ነበሩ ሲሉ የኬር ኢንተርናሽናል ባልደረባ የሆኑት ሜሊሳ ኮርኔት ገልጸዋል።
አክለውም “አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል ለሕይወት አስጊ ለሆነ ረሃብ በተጋረጠበት ሁኔታ ሴቶች ከሌሉ የሰብአዊ ቀውሱ በፍጥነት ሊባባስ ይችላል” ብለዋል።
የደቡብ እስያ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቅርንጫፍ ውሳኔውን "ሴቶችን ከአፍጋኒስታን ፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምህዳር ለማጥፋት የተደረገ ሌላ አሳዛኝ ሙከራ" ሲል ገልጾታል።
በሰሜናዊው ማዛር-ኢ-ሻሪፍ ከተማ በሚገኙ መንደሮች የምትሠራ አንዲት ዶክተር በእገዳው "አዝኛለሁ" ስትል ተናግራለች።
ቢቢሲ ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጋቸው አንድ ኢማም በበኩላቸው ታሊባን "ለየትኛውም ኢስላማዊ እሴት ቁብ የለውም" ብለዋል።
“እስልምና ወንድ መማር ይችላሉ፤ ሴቶችም ደግሞ አይችሉም አላለም።ወይም ወንዶች ሠርተው ሴቶች አይችሉም አላለም።በውሳኔው ግራ ተጋብተናል” ብለዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሴቶች በአፍጋኒስታን ዩኒቨርሲቲዎች እንዳይማሩ መታገዳቸው ተመሳሳይ ትችት ገጥሞታል።
ቅዳሜ ዕለት ሄራትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞ ቢቀሰቀስም ታሊባን በፍጥነት አፍኖታል።