ሳዑዲ 4 ኢትዮጵያውያንን በሞት ስትቀጣ፣ ኢትዮጵያ ከ1600 በላይ ምህረት እንደተሰጣቸው ገለጸች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሳዑዲ አረቢያ በዚህ ሳምንት አራት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቅጣቷን ስታሳውቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ከ1600 በላይ ዜጎቹን ክሳቸው ተቋርጦ በምህረት እንዲለቀቁ ማድረጉን ገለጸ።

የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሰኔ 1 ሁለት እንዲሁም ሰኔ 3/2018 ዓ.ም. ሁለት ኢትዮጵያውያን በስቅላት መገደላቸውን አስታውቋል።

የሞት ቅጣቶቹ የተፈጸሙት ሰኔ 1/2018 ዓ.ም. በናጅራን ግዛት እንዲሁም ሰኔ 3/2018 ዓ.ም. ደግሞ በአሲር ግዛት መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል።

አራቱም ኢትዮጵያውያን በሞት የተቀጡት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሃሺሽ ይዘው በመግባታቸው መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት የሚገኙ 1655 ኢትዮጵያውያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲደረግላቸው ማድረጉን አስታውቋል።

ሂውማን ራይትስ ዎች የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ሚያዚያ 13/2018 ዓ.ም. ሦስት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቀጣታቸውን ገልጾ የ65ቱ ፍርድ ተፈጻሚነት ግን እንዲዘገይ መደረጉን ገልጾ ነበር።

የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያየ ጊዜ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ ላይ የሃይማኖት መልዕክቶችን እና የሸሪዓ ሕግን በመጥቀስ የሟቾችን ስም ይዘረዝራል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያውያኑ ምህረት የተደረገው ሚኒስቴሩ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽ/ቤት በማስተባበር ባደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ከዚህ ቀደም ሂውማን ራይትስ ዎች በሳዑዲ አረቢያ ቢያንስ 65 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ክስ የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ገልጾ ነበር።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙን አስታውቋል።

የሂውማን ራይትስ ዎች ሳዑዲ አረቢያ መሠረታዊ የፍትህ ሂደትን የተነፈጉ የውጭ አገር ዜጎች አመጽ ባልተቀላቀለባቸው ወንጀሎች የተነሳ በሞት ለመቅጣት ፍቃደኛ መሆኗ ለመብታቸው እና ለሕይወታቸው ከፍተኛ ግድ የለሽነት እንዳላት ያሳያል ሲል ኮንኗል።

የመብት ተሟጋቹ ከመርፈዱ በፊት የሳዑዲ አረቢያ አጋሮች በፍጥነት ጣልቃ በመግባት የሞት ቅጣቱን እንዲያስቀሩ ጥሪ አቅርቧል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ምንጮችን ጠቅሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ እንዳሉ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

"ከ200 በላይ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን በካሚስ ሙሻይት እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ" ሲልም ጠቅሷል።