ስታድየሞችን የሚያደምቀው ተመልካቾች በእጅ ውዝዋዜ ማዕበል የሚፈጥሩበት እንቅስቃሴ አስደናቂ ታሪክ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከስታዲየሙ በስተቀኝ የሚወዛወዙ እጆች ይታያሉ። ከአንደኛው መቀመጫ ሥፍራ ወደሌላኛው የሚጓዙት ስልት ተከትለው ነው።

አንድ ሰው የተቀመጠበት ቦታ እጅ የማወዛወዝ ማዕበሉ ሲደርስ አለመቀላቀል አይቻልም። ይሄ ልማድ የእግር ኳስ ጨዋታ ድምቀት ነው።

የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የሆነው ጊነስ ወርልድ በአውሮፓውያኑ 2008 በአሜሪካ ቴነሲ ግዛት 157,574 ሰዎችን ያሳተፈ የእጅ ውዝዋዜን በግንባር ቀደምነት አስፍሯል።

ታዳሚዎቹ የመኪና ውድድር እየተመለከቱ ነበር።

በርካታ ሰዎች በእጅ ውዝዋዜው ቢሳተፉም ለረዥም ደቂቃ አልቆየም።

ኒው ጀርሲ ውስጥ በ2019 በተካሄደ የቪድዮ ጌም ውድድር ላይ ለ28 ደቂቃ የተካሄደው የእጅ ውዝዋዜ በርዝመት ቀዳሚው ነው።

በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ሜክሲኮ ሲቲ የእጅ ውዝዋዜ ክብረ ወሰኑን ለመያዝ ቆርጣ ተነስታለች።

የተመረጠው ቦታ ስታዲየም አይደለም። ፔሶ ደ ላ ሪፎርማ የተባለ ታሪካዊ እና ባህላዊ ጎዳና ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ጎዳና ተሰብስበው በታሪክ ሰፊውን የእጅ ውዝዋዜ ለማስመዝገብ ለሰኔ 6 ቀጠሮ ይዘዋል። ትዕይንቱን ለመቀላቀል ገንዘብ መክፈል አያስፈልግም።

ከ40 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ያለ ክንውን የዓለምን ቀልብ የገዛው በዚሁ ኤስታዲዮ አዝታካ በተባለ ከተማ ነው።

የእጅ ውዝዋዜ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከሜክሲኮ ጋር ትስስር ያለው ክንውን ተደርጎ ይወሰዳል።

ሜክሲካን ዌቭ (Mexican wave) ወይም የሜክሲኮ ማዕበል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ሆኖም ግን የእጅ ውዝዋዜው የሜክሲኮ ሳይሆን የአሜሪካ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ።

በአሜሪካ የእጅ ውዝዋዜ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በአውሮፓውያኑ 1986 እንደሆነ ይነገራል።

አሜሪካዊው ጆርጅ ሄንደርሰን (በቅጽል ስሙ ክሬዚ ጆርጅ) ይሄንን የእጅ ውዝዋዜ ማዕበል እንዳስጀመረ ይነገርለታል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 15/1981 በኦክላንድ አትሌቲክስ እና በኒው ዮርክ ያንኪስ መካከል በተካሄደ የቤዝቦል ግጥሚያ ላይ ነበር።

"የኦክላንድ አትሌቲክስ ሁለት ጊዜ ተሸንፈው ነበር። በሦስተኛው ማንም ሰው ያላደረገውን ለማድረግ አሰብኩ። ሦስት ቡድን ፈጥሬ የምፈልገውን ገለጽኩላቸው" ሲል ያስታውሳል።

ሁለት ጊዜ ሞክሮ አልተሳካለትም። በሦስተኛው እና በአራተኛው ዙር ግን ስታድየሙን በሚፈልገው መንገድ ማንቀሳቀስ ቻለ።

ስታዲየሙ ከጥግ እስከ ጥግ እየተነቃነቀ እንደነበር ይናገራል።

ግጥሚያው በቴሌቭዥን እየተላለፈ ስለነበር የእጅ ውዝዋዜው ዝነኛ ሆነ። በ1984 የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክም ተደገመ።

በ1986 በሜክሲኮ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ሲታይ ዓለም አቀፋዊ መልክ ይዟል።

ከ15 ዓመታት በኋላ በቡዳፔስት የሀንጋሪ አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ የስታትስቲክስ፣ ሥነ ሕይወት እና ፊዚክስ ባለሙያዎችን ትኩረት ሳበ።

ኤንፒአር ያነጋገራቸው ፊዚሲስት ኢልስ ፋርክስ "በእጅ ውዝዋዜው ላይ ትኩረት ያሳደርነው ሰዎች እንደ ቅንጣቶች (ፓርቲክልስ) እንዴት እንደሚንቀሳቀሱ ለመረዳት ነው" ይላሉ።

ታማስ ቪስክ እና ዴሬክ ሂልቢንግ የተባሉ የሥራ ባልደረቦቹ እንዴት መጀቡ እንደተፈጠረ ምርምር አድርገዋል።

የተወሰኑ ሕግጋትን በመከተል ማዕበሉን መፍጠር እንደሚቻል ተረድተዋል።

በ2002 ኔቸር በተባለው የሳይንስ መጽሔት ላይ በወጣ የጥናት ጽሑፍ ላይ እንደተመለከተው ቡድኑ የእጅ ውዝዋዜን የሚያሳዩ 50 ሺህ ሰዎችን ያሳተፉ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ላይ ምርምር አድርጓል።

የእጅ ውዝዋዜ የሚደረገው ከግራ ወደ ቀኝ እንደሆነ እና በሰከንድ 12 ሜትር ወይም 20 መቀመጫ እንደሚሻገር በጥናታቸው ደርሰውበታል።

የእጅ ውዝዋዜው በአማካይ ከ6 ሜትር እስከ 12 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን 15 ተከታታይ መቀመጫ ወንበሮችን ይሻገራል።

ከ25 እስከ 35 የሚደርሱ ሰዎች በአንድነት ከወንበራቸው ተነስተው የእጅ ውዝዋዜውን ያከናውናሉ። በእነዚህ ሰዎች ጀማሪነት የእጅ ውዝዋዜው በአስር ሺዎች የሚቆየሩ ሰዎችን ሊያሳትፍ ይችላል።

የእጅ ውዝዋዜውን ለመረዳት የተጠቀሙበት የሒሳብ ቀመር የኤሌክትሪክ ሲግናል በልብ ውስጥ ሲሠራጭ ወይም ሰደድ እሳት በደን ውስጥ ሲስፋፋ ካለው ጋር የሚመሳሰል ነው።

የእጅ ውዝዋዜው ዓለም አቀፍ የደስታ መግለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። አንድ ቦታ ላይ የተሰበሰቡ ሰዎች በጋራ ሐሴታቸውን የሚገልጹበት ነው።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜክሲኮ የሥነ ልቦና ምርምር ክፍል ባለሙያ ኤሪክ ሳልዛር ፍሎረስ "የእጅ ውዝዋዜውን ስናደርግ አንድ ላይ መሆናችንን እየገለጽን ነው" ይላሉ። ይህም የ "እኛነት" ስሜት የሚፈጥር ነው።

ቡድኖችን ለማበረታታት ወይም ደስታን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውለው የእጅ ውዝዋዜ ከመሰላቸት እና በሚከናወነው ነገር ፍላጎት ከማጣት ጋርም የሚተሳሰርበት ጊዜ አለ።

"ግጥሚያው ላይ አስደሳች ነገር ሳይታይ ሲቀር ተመልካቾች ጨዋታውን ለመመልከት ከፍለው የገቡትን ገንዘብ በማሰብ የእጅ ውዝዋዜውን ይጀምራሉ" ሲሉ ባለሙያው ያብራራሉ።

በዓለም ዋንጫ የመጨረሻው ግጥሚያ ላይ ቡድኖች አቻ ከሆኑ የእጅ ውዝዋዜ አይኖርም። አሸናፊው ሲለይ ግን የእጅ ውዝዋዜው እንደሚጀመር ይጠበቃል።

አንዳንድ ጊዜ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው በፊት የእጅ ውዝዋዜ ይስተዋላል። ለምሳሌ ተጫዋቾች ሰውነታቸውን ሲያሟሙቁ ሊጀመር ይችላል።

በስታዲየሞች ውስጥ ብዙዎች ትኩረት ሳያደርጉ ልዩ ትዕይንቶች የሚከሰቱበት ጊዜ ይኖራል።

የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ሰዎች በቡድን ሲሆኑ የሚያነቃቃ ነገር ያደርጋሉ።

ስለዚህም የእጅ ውዝዋዜ የደስታ መግለጫ ሳይሆን ማነሳሻ ይሆናል ማለት ነው።

የእጅ ውዝዋዜ በመላው ዓለም ከታወቀ 40 ዓመታት ቢሆንም አሁንም የስፖርት ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል።

በ1980ዎቹ በስፋት ከታወቀ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ እንደተቀዛቀዘ ተንታኞች ይገልጻሉ።

በአሜሪካ በቤዝቦል ጨዋታ ወቅት የእጅ ውዝዋዜ እንዳይደረግ ንቅናቄ ተጀምሮም ነበር። በ2014 የተነሳው ንቅናቄ የእጅ ውዝዋዜ "ክብር የሚነካ" እና ከጨዋታቸው "የሚያዘናጋ" ነው ተብሎ ተተችቷል።

በሌላ በኩል የእጅ ውዝዋዜ በየትኛው የጨዋታው ክፍል ላይ መከናወን እንዳለበት መወሰን የተሻለ ነው የሚል መከራከሪያ ይነሳል።

ደጋፊዎች የደስታ ስሜታቸውን የሚገልጹበትን ክንውን እንዴት በመመሪያ መቆጣጠር ይቻላል? የሚሉም አሉ።