በአፍጋኒስታን ታሊባን ሴት ሠራተኞችን ከሥራ ካገደ በኋላ የውጪ አገራት ሰብዓዊ ድርጅቶች ሥራ አቆሙ

ታትሟል

ታሊባን ሴቶች መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋመት መስራት አይፈቀድላቸውም ካለ በኋላ 5 ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአፍጋኒስታን የሚያደርጉትን ሥራ ማቋረጣቸውን አስታወቁ።

ኬር ኢንተርናሽናል፣ ኖርዌጂያን ሪፊውጂ ካውንስል እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) "ያለ ሴት ሠራተኞቻችን መቀጠል እንችልም" ብለዋል።

ከእነዚህ ተቀሟት በተጨማሪ ኢንተርናሽናል ሪሴኪው ኮሜቴ አገልግሎቱን ማቋረጡን ሲገልጽ ኢስላሚክ ሪልፍ ደግሞ የተሰኘው ተቋም ደግሞ በርካታ ስራዎቹን ማቆሙን ገልጿል።

አፍጋኒስታንን እየመራ የሚገኘው ታሊባን በየጊዜው የሴቶችን ሰብዓዊ መብቶች የሚጋፉ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል።

ታሊባን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ሴቶች መስራት አይችሉም የሚለው ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ቀደም ብሎ ሴት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንዳይማሩ አግዶ ነበር።

የታሊባን ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አብድል ራህማን አባቢ በውጪ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሴት ሠራተኖች ሂጃብ ባለመልበስ የአለባበስ ደንብን እያከበሩ አይደሉም ሲሉ ከሰዋል።

እገዳውን ተላልፈው ሴቶችን የሚቀጥሩ ተቋማትን ፍቃዳቸውን እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ታሊባን ዝቷል።

በርካታ የዕርዳታ ተቋማት ሴቶች አብረውን እንዲሰሩ ሊፈቀድ ይገባል የሚል ጥያቄ እያቀረቡ ነው።

ኬር ኢንተርናሽናል፣ የኖርዌ ሪፍጂ ካውንስል እና ሴቭ ዘ ችልድረን በጋራ ባወጡት መግለጫ ሴት ሠራተኞች ባይኖሩ ከፈረንጆች 2021 ነሐሴ ወር ጀምሮ በጋራ ተደራሽ ያደረግናቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ተደራሽ ማድረግ አንችልም ነበር ብለዋል።

“እገዳው ግልጽ በሆነ መንገድ ቢነገርም ሴቶች እና ወንዶች በእኩል የሕይወት አድን ሥራዎች መስራት እንዲፈቀድላቸው ለመጠየቅ በአፍጋኒስታን ያለንን የእርዳታ ፕሮግራሞች ገተናል” ብለዋል።

በመላው አፍጋኒስታን 3 ሺህ ሴት ሠራተኞች አሉኝ ያለው ‘ኢንተርናሽናል ሪሴኪው ኮሜቴ’ በተናጠል ባወጣው መግለጫ በሁሉም ደረጃዎች ያሉ አገልግሎቶች ሴት ሠራተኞች ላይ የተመረኮዘ ነው።

“እኛም ሴት ሠራተኞች መቀጠር ካልቻሉ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ አይቻልም” ብሏል።

ኢስላሚክ ሪልፍ በበኩሉ “በአፍጋኒስታን ከሕይወት አድን ውጪ ያሉ ሥራዎቹን በጊዜያዊነት ለማቋረጥ ከባድ ውሳኔ ላይ” መድረሱን ገልጿል። ያተቋረጡት አገልግሎቶች በድኅነት ያሉ ሰዎች ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችለውን እንዲሁም ከትምህርት እና ጤና ጋር የተያያዙ ድጋፎችን ያካትታል።

እገዳው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዕርዳታ ፈላጊዎች ላይ ከባድ ተጽእኖ ይፈጥራል ያለው ተቋሙ “ኢስላሚክ ሪልፍ የአፍጋኒስታን ባለስልጣናት እገዳውን በፍጥነት እንዲያነሱ ጥሪ ያቀርባል” ብሏል።

የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ ራምዚ አልካብሮቭ የእገዳ ውሳኔው እንዲቀለበስ ተመድ እየጣረ ነበር ያሉ ሲሆን “ይህ እርዳታን ለሚያቀርብ ቀይ መስመር ነው” ብለዋል።

ኃላፊው ውሳኔው የማይቀለበስ ከሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት በአፍጋኒስታን የሚያደርሰውን የሰብዓዊ እርዳታ ሊያቋርጥ ይችላል ሲሉ ኋላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አልካብሮቭ ታሊባን የጣለው እገዳ ግልጽ አይደልም ብለዋል።

የታሊባን የጤና ሚኒስትር ተመድ ከጤና ጋር በተገናኘ የሚሰራው ሥራ መቀጠል አለበት ማለታቸውን የተናገሩት አስተባባሪው ሴቶች ሪፖርት አርገው አገልግሎታቸውን ማቆም ይችላሉ እንዳሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል ሌሎች ሚኒስትሮች የመንግስታቱ ድርጅት ከአደጋ አመራር ጋር የተገናኙ ስራዎች መቀጠል አለባቸው ማለታቸውን ጠቅሰዋል።

ታሊባን የጣለው እገዳ ዓለም አቀፍ ቅሬታን የቀሰቀሰ ሲሆን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኋላፊ አንቶኒ ብሊንከን ውስሳኔው “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ የህይወት አድን እርዳታዎች ላይ ተጽሆኖ ሊፈጥር ይችላል” ብለዋል።

ታሊባን ባለፈው ዓመት ወደ ስልጣን ዳግም ሲመለስ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1990ዎች ከነበረው የተሻለ እና እምብዛም ያልጠበቀ አስተዳደር ይኖረኛል ሲል ከገባው ቃል በተቃራኒ የሴቶችን መብት የሚጸረሩ ውሳኔዎች በየጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።

መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ከሚሰሩ ሴት ሰራተኞች እና ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ከተጣለው እገዳ በተጨማሪ በበርካታ ግዛቶች ሴቶች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየታገዱ ነው።

በሌላ በኩል ሴቶች መናፈሻዎች እና አካላዊ እንቅስቃሴ በሚገደረጉባቸው ስፖርት ቤቶች እንዳይገቡ ከተከለከሉባቸው ቦታዎች የሚጠቀሱ ናቸው።