ባለንበት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ሐዘናችንን የምንገልፀው እንዴት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ባለንበት የዲጂታል ዘመን የሰው ልጆች በአካል ከሚያደርጉት መስተጋብር ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሚያደርጉት እየበለጠ መጥቷል።
ሁሉም ሰበር ዜና አድራሽ፣ ሁሉም አስተያየት ሰጪ ሆኗል።
ደስታን እና ሐዘንን ለብዙኃኑ ማጋራት፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ አስተያየት ያለገደብ መስጠት፣ በተፈጠሩ ኩነቶች ላይ የራስን አመለካከት ማንፀባረቅ ለሁሉም ሰው ቀላል ነው።
የግለሰቦች ሞት እንደተሰማ “ነፍስ ይማር” የሚለው መልዕክት ከምስላቸው ጋር በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ሲጋራ አፍታ አይወስድም።
እነዚህ በምስል እና በጽሁፍ ተደግፈው የሚጋሩ መልዕክቶች፣ ቅብብሎሻቸው በፍጥነት ሲሳለጥ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
በተለይም ፌስቡክ አገልግሎት ላይ ከዋለበት ካለፉት 15 ዓመት ወደዚህ ተጠቃሚዎች የተለያዩ ይዘቶችን የሚያጋሩበት አካሄድ የተለመደውን የማኅበረሰቡን ወግ እና ልማድ ጥሶ የራሱን ፈር እየቀደደ መጥቷል።
በተለይ ተደጋጋሚ ግጭት ባስተናገደችው ኢትዮጵያ፣ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን እና የሞቱ ግለሰቦችን ምስል ማጋራት ተለምዷል።
ይህንን ጉዳይ በቅርበት ያስተዋሉት የታሪክ ምሁር እና ደራሲ የሆኑት አቶ ድሪቢ ደምሰው በኢትዮጵያ ውስጥ ሞት የሚገለጽበት መንገድ ወግና ሥርዓቱን እያጣ መምጣቱን ይናገራሉ።
በተደጋጋሚ በተከሰቱ ግጭቶች መካከል የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመር “ለሞት እና ለሟች ያለን ክብር” እንዲሸረሸር እንዳደረገው ይጠቅሳሉ።
በእርግጥ ይላሉ አቶ ድሪቢ “አሰቃቂ ወንጀሎችን እና የሰው ልጆችን ግድያዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራት በአንድ በኩል በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙትን በደሎች ማጋለጥ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ድርጊት እየተለመደ በሄደ ቁጥር የሰው ልጆችን ሕሊና እያደነዘዘ ይሄዳል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በግጭቶች መካከል የሞቱ ሰዎችን ምስል ማጋራት በደሎችን እና ጥቃቶችን እንደማጋለጥ ቢቆጠርም፣ ቤተሰብ እና ዘመዶች ግን ተጨማሪ ሰቀቀን መሆኑን አቶ ድሪባ ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቄስ የሆኑት ቄስ በላይ መኮንን በበኩላቸው አብዛኞቹ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ብዙ ‘ላይክ እና ሼር’ ለማግኘት እንዲሁም ታዋቂነት ለማትረፍ ሲሉ የማኅበረሰቡን ወግ እና ባሕል የሚተላለፉ መረጃዎችን ሲያጋሩ ይውላሉ ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት “የማንም ሰው አስከሬን ክብር አለው። በመሆኑም በማኅበረሰቡ የተለመደ ባሕል እና ዘይቤ መስተናገድ አለበት እንጂ የሞተ ሰውን ፎቶ መለጠፍ ከማኅበረሰባችን የኖረ የአኗኗር ጋር ተቃራኒ ነው” በማለት ይተቻሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ድሮ ሞት የሚረዳበት አካሄድ ነበረው። ወግም ነበረው። ለባለቤቱ በቀጥታ አይነገርም በጠዋት ቤቱ ይኬድ እና ቁጭ በሉ ተብሎ እንዲረጋጉ ከተደረገ በኋላ እርማቸውን እንዲያወጡ በተረጋጋ ሁኔታ ይነገራል እንጂ ገበያ ውስጥ ለሰው ሞት አይረዳም።
“አሁን ግን ሰው ሰው ምግብ እየበላ ሳለ ወይንም ገበያ ውስጥ ቆሞ የዘመዱን አስከሬን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያያል” በማለት የቀደመው የማኅበረሰቡ ወግ እንዴት እንደተጣሰ ይናገራሉ አቶ ድሪቢ።
ጨምረውም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሞትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የተለመዱ የማኅበረሰቡን የኖረ ወግና ባህል የሚያፋልሱ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ሲያጋሩ እንደሚውሉ ይጠቅሳሉ።
“ግለሰቦችን ይሰድባሉ። ቤተሰብን እና ዘመድን የሚበትን ጉዳይ ይለጥፋሉ። ከአንድ ግለሰብ ጋራ ቅሬታ ስላላቸው ብቻ ጎሳውን በሙሉ መሳደብ እየተለመደ መጥቷል” ይላሉ።
በአጠቃላይ ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ ተግባቦት ዘመን በጎ ፋይዳ እንዳለው ሁሉ የራሱን ተጽዕኖም ይዞ መምጣቱን ይናገራሉ።
አሁን እየሆነ ያለው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው የተናገሩት የታሪክ ባለሙያው፣ በአሁኑ ሰዓት ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ሞትን እንደተራ ነገር ቆጥረው ተላምደውታል ይላሉ።
“ሞት እየበዛ ሲሄድ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስከሬን መታየት ሲበዛ፣ የሰው ልጅ ሞት ተራ ነገር እየሆነ ይሄዳል። ሞት ምንም እንዳልሆነ እየተለመደ ይሄዳል። ሰው ነው የሞተው ከሚለው ይልቅ ስንት ሰው ሞተ ወደሚለው እንሻገራለን። ይህም ማለት ለቁጥር እንጂ ለክቡሩ የሰው ልጅ ነፍስ ክብር መስጠት እየቀረ ይሄዳል” ሲሉ ይናገራሉ።
ሐዘን ለመግለጽ ወይስ ታዋቂነት ለማትረፍ
ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ሞት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራት ሐዘናቸውን ይገልጻሉ።
ይህም በተለያዩ ዓለማት በቅርብ እና በርቀት ያሉ ዘመዶችን እና ወዳጆችን በአንድ መድረክ ማግኘት ስለሚቻል በዚያው ሐዘናቸውን ለመግለጽ ነው።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሟቾችን ምስል የሚያጋሩ እና ስለሞቱት ግለሰቦች የተለያዩ ነገሮችን የሚጽፉ ግለሰቦች የተለያዩ ግብን አንግበው እንደሆነ ያላቸውን ጥርጣሬ አቶ ድሪቢ ያነሳሉ።
አቶ ድሪቢ “ገሚሶቹ የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለጽ፣ የተቀሩት ደግሞ ታዋቂነትን ለማግኘት ሲሉ ይለጥፋሉ” ይላሉ።
ቢሆንም ግን ይህ የቴክኖሎጂ ወይንም የማኅበራዊ ሚዲያ ችግር ሳይሆን ሰዎች ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙበት መንገድ ነው ይላሉ ቄስ በላይ እና የታሪክ ምሁሩ አቶ ድሪቢ።
ለምሳሌ ሰዎች ታዋቂነትን ለማግኘት ሲሉ ስለ አንድ የሞተ ሰው ምስል፣ የፈለጉትን መረጃ ሲለጥፉ የፖለቲካ ግብ ይዘው ሊሆን ይችላል የሚሉት አቶ ድሪቢ፣ ይህ ድርጊት ደግሞ የሟቹን ዘመድ እና ቤተሰብ በሐዘን ላይ ሌላ ሐዘን የሚጨምር መሆኑን ያነሳሉ።
ያም ሆነ ይህ አንድ የሞተ ሰውን ካለ ቤተሰብ ፈቃድ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራት በተለያየ መንገድ በሟቹ ቤተሰቦች እና በማኅበረሰቡ የተለመደ ወግ እና ሥርዓት የራሱ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ይስማሙበታል።
በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ወንጀሎች እየተስፋፉ በመጡበት በዚህ ወቅት በዚህ ዘመን ሰዎች የሚያካፍሉትን ማንኛውም መረጃ ኃላፊነት በተሞላው ሁኔታ መሆን እንዳለበት ምክር አስተላልፈዋል።












