በተከታታይ አምስት ጊዜ መንታ የወለዱት ጥንዶች ተለያዩ

አምስት ጊዜ መንታ ልጆችን የወለዱት ናይጄሪያውያን ጥንዶች ደስተኛ ባለመሆናቸው ለመለያየት ተገደው አባት ልጆቹን ብቻውን እያሳደገ ነው።
አዮፖ ኦጉንሌዬ እና ባለቤቱ ባልተለመደ ሁኔታ አምስት ጊዜ መንታ ልጆችን በመታደላቸው በአህጉሪቱ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ በሆነችው በምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ ታዋቂ ናቸው።
ቢሆንም ግን የባለቤቱ ቤተሰቦች በዚህ ሁኔታ ደስተኞች አልሆኑም።
በናይጄሪያዋ ኦጉን ግዛት ውስጥ አዶ ኦዶ በተባለው አካባቢ ነዋሪ የሆነው አባት አዮፖ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ በተደጋጋሚ መንትዮችን በመውለዳቸው የሚስቱ ወላጆች ቅር መሰኘታቸውን ተከትሎ ባለቤቱ ትታው ሄዳለች።
በአርባዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው አዮፖ ከባለቤቱ በተከታታይ አምስት ጊዜ መንታ ልጆችን ቢያገኝም አሁን ብቻውን እያሳደጋቸው ያሉት ሰባቱን ብቻ ነው።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመጀመሪያ የተወለዱት መንትዮች ጨቅላ እያሉ እንዲሁም በመጨረሻ ከተወለዱት መንትዮች አንዱ በመሞታቸው ነው።
አባት ከመጀመሪያው አንስቶ መንታ ልጆች ይኖሩኛል ብሎ አስቦ እንዳልነበር በመግለጽ፣ ከመጀመሪያው እርግዝና ሚስቱ መንታ መገላገሏን ሐኪሞች ሲነግሩት መደነቁን ያስታውሳል።
“ባለቤቴ መውለዷን ስሰማ የጠየቅኩት ወንድ ነው ሴት ብዬ ነበር፤ እነሱም መንታ ናቸው ሲሉኝ ተገርሜያለሁ።”
ነገር ግን አልደነገጠም። ይህ ዘወትር ሲመኘው የነበረ መሆኑን ይናገራል።
“ከልጅነቴ ጀምሮ መንታ ልጆች እንዲኖሩኝ እመኝ ነበር፣ ጸሎቴን በመስማቱም እግዚአብሔርን አመሰገንኩ። ሚስቴንም አቅፌ እንኳን ደስ አለሽ አልኳት” ሲል የመጀመሪያዎቹን መንትዮች ያስታውሳል።
አዮፖ የሚኖርበት ዮሮባ ማኅበረሰቦች በአብዛኛው በምዕራባዊ የናይጄሪያ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መንትዮች ከሚወለዱባቸው አካባቢዎች አንዱ እንደሆንም ይነገራል።
በማኅበረሰቡ ውስጥ መንታዎች “ኢቤጂ” ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ በባሕሉ መሠረትም መንትዮች ከተወለዱ በኋላ አንድ ልጅ ይወለዳል ተብሎ ይታመናል ይህም “ኢዶዉ” ይባላል።
ነገር ግን አዮፖ እና ባለቤቱ በባሕሉ ከሚታመነው እና ከተለመደው በተቃራኒ ከመጀመሪያው ተከትሎ በነበሩት አራት እርግዝናዎችም የወለዱት መንታዎች ናቸው።
“ሁለተኛውም መንታ፣ ሦስተኛውም መንታ፣ አራተኛውም መንታ አምስተኛውም መንታ ሆኑ” በማለት በአምስት እርግዝናዎች ባለቤቱ አሥር ልጆች መውለዷን ይናገራል።
ከሌሎች ሰዎች የተለየ የሚመገበውም የሚያደርገውም ነገር ሳይኖር ሁሉም ልጆቹ መንታ ሊሆኑ የቻሉበትን ምክንያት ለማወቅ ቢጥርም አስካሁን ምሥጢር እንደሆነበት ይናገራል።
“ልጆች የፈጣሪ በረከቶች ናቸው” የሚለው አዮፖ ኦጉንሌዬ፣ ምንም እንኳን ልጆቹን ለማሳደግ የአቅም ችግር ቢኖርበትም፣ ሌላ ሚስት አግብቶ ብዙ ልጆች የመውለድ ፍላጎት አሁንም አለው።












