የኮንጎው ጀግና ሉሙምባ ጥርስ ከ61 አመታት በኋላ ተቀበረ

ፓትሪስ ሉሙምባ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የነጻነት አርበኛ ፓትሪስ ሉሙምባ ከተገደለ ከስልሳ አንድ አመታት በኋላ ጥርሱ እንዲቀበር ተደርጓል።

ከነፃነት በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሉሙምባ በቤልጂየም ከተገደለ በኋላ አስከሬኑ በአሲድ እንዲሟሟ የተደረገ ሲሆን የቀረው አካሉ ጥርሱ ብቻ ነበር።

አስከሬኑ በአሲድ እንዲወገድ ያደረገው የቤልጂየም ፖሊስ ጥርሱን እንደ ድል ወስዶት ነበር ተብሏል።

ጥርሱ ባለፈው ሳምንት ለቤተሰቡ የተመለሰ ሲሆን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በርካታ አካባቢዎች በአስከሬን ሳጥን ተደርጎም እንዲዘዋወር ተደርጓል።

በመዲናዋ ኬንሻሳ ቀብሩ ከመፈጸሙ በፊት በርካቶች ለክብሩ በተሰየመው መንገድ በመገኘት ክብራቸውንም ሲገልጹ ነበር።

የአስከሬን ሳጥኑ በልዩ ሁኔታ ወደተገነባው መካነ መቃብር ከመግባቱ በፊት ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ፣ የሉሙምባ ቤተሰቦች እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች በነበረው ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል።

"የአባቶቻችን ምድር ጣፋጭ እና የምትመች ትሁንህ" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የነጻነት ትግል መሪዎች አንዱ የነበረው ፓትሪስ ሉሙምባ ኮንጎ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር። በአፍሪካ ፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑት ታጋዮች አንዱ ተደርጎ ይታይ ነበር።

የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ቤልጂየም ኮንጎን ከተቆጣጠረች 62 አመታትን አስቆጥሯል።

ከነፃነት በኋላ ቤልጂየም በኮንጎ ላይ የነበራትን ተፅእኖ ለማስቀጠል እና በተፈጥሮ ሃብታም የሆነችውን አገር ለመበዝበዝ በምታደርገው ጥረት ሉሙምባን እንደ እንቅፋት ትመለከተው ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1960 የነፃነት ቀንን በማስመልከት የ34 ዓመቱ ሉሙምባ ባደረገው ንግግር ባውዶይንን ጨምሮ የቤልጂየም ሹማምንቶች ፊት ለፊት ቤልጂየም የኮንጎን ህዝብ በ“አዋራጅ ባርነት” ውስጥ ይዘዋቸዋል ብሎ ነበር።

አንድ ጥቁር አፍሪካዊ በአውሮፓውያን ፊት እንደዚህ ለመናገር ደፍሮ ስለማያውቅ ቤልጂየማውያንን ያስደነገጠ ነበር።

ሉሙምባ ከሁለት ወራት በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትርነቱ እንዲገረሰስ ተደረገ። ከዚያም በአውሮፓውያኑ  በቤልጂየም ገዳይ ቡድን ከሁለት አጋሮቹ ጋር በጥይት ተመታ።