በኦሮሚያ ምስራቅ ባሌ በኩፍኝ በሽታ የሰዎች ሕይወት አለፈ

በምስራቅ ባሌ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ ዞን በኩፍኝ በሽታ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ የዞኑ ጤና መምሪያ አሰታወቀ።

በአካባቢ የተከሰተው ድርቅ የሰዎችን የበሽታ መከላከል አቅም በማዳከሙ ሕይወታቸው ካለፉት በተጨማሪ 348 ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ተካ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምስራቅ ባሌ ዞን በሚገኙት ሳዌና፣ ራይቱ፣ ጎሎልቻ እና ለገ ሂዳ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 23 ቀበሌዎች ውስጥ በሽታው መዛመቱን አቶ ጥላሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኃላፊው “በለጋ ሂዳ እና ጎሎልቻ የተዛመተውን ስርጭት ለመግታት ተቃርበናል። በሳዌና እና ራይቱ በተለይ ደግሞ በሳዌና 12 ቀበሌዎች ውስጥ በስፋት ተዛምቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

የሳዌና ወረዳ አቀማመጥ አስቸጋሪ በመሆኑ የጤና ባለሙያዎች ወደ አካባቢው ተሰማርተው የመከላከል ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ ተገልጿል።

አምስት ሰዎች በኩፍኝ በሽታ መሞታቸው መረጋገጡን የሚናገሩት አቶ ጥላሁን፤ በበሽታው ተይዘው ከነበሩት 348 ሰዎች ለ202 ሰዎች ሕክምና ተደርጎላቸው ከበሽታው ማገገማቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

በደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሳቸው በሽታውን ወደ ምስራቅ ባሌ ማምጣቱን ጨምረው አስረድተዋል።

“በድርቁ ምክንያት ሰዎች የግጦሽ ሳር እና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ” ያሉት አቶ ጥላሁን፣ የሰዎች እንቅስቃሴን ተከትሎ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በአካባቢው በሽታው መዛመቱን ያስረዳሉ።

የኩፍኝ በሽታ ምንድነው?

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) መረጃ እንደ ሚያስረዳው ከሆነ ኩፍኝ በቀላሉ የሚዛመት የመተንፈሻ ሕመም ነው።

ከአፍ ውስጥ ወይም ፊት ላይ ጀምሮ ወደ ተቀረው የሰውነት ክፍል የሚዛመት ሽፍታ፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ሳል፣ ከአፍንጫ ፈሳሽ መፍሰስ እና የዓይን መቅላት በኩፍኝ በተያዘ ሰው ላይ ከሚታዩ ምልክቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ሲዲሲ በበሽታው የተያዘ ሰው ሽፋታው በሰውነቱ ላይ ከመታየቱ 4 ቀናት በፊት እና ከታየ 4 ከቀናት በኋላ በሽታውን ወደ ሌሎች ሊያስተላልፍ ይችላል ይላል።

በኩፍኝ በሽታ ምክንያት ከፍተኛ ሕመም እና ከበሽታው ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች የበለጠ ተጋላጭ የሚሆኑት፤ ዕድሜያቸው ከ5 በታች ያሉ ሕጻናት እና ጨቅላዎች፣ ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች፣ ነብሰ ጡር እናቶች እና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታ የለባቸው ሰዎች ናቸው።

ኩፍኝ በቀላሉ ከሚተላለፉ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ ይካተታል። በበሽታው የተያዘ ሰው ሲተነፍስ፣ ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ በሚወጡ ፍንጣቂዎች በሽታው ወደ ሌሎች ሰዎች ሊዛመት ይችላል።

ይሁን እንጂ የኩፍኝ በሽታ በክትባት መከላከል ይቻላል። ሲዲሲ እንደሚለው ሁለት ዙር የኩፍኝ ክትባት በሽታውን 97 በመቶ መከላከል ያስችላል።