እንግሊዝ ውስጥ በኤርትራዊው ግድያ የተጠረጠሩ 5 ሰዎች ተከሰሱ  

በረከት ሶሎሞን

የፎቶው ባለመብት, SBNA

የምስሉ መግለጫ, በረከት ሶሎሞን
ታትሟል

ከሳምንት በፊት እንግሊዝ ውስጥ በስለት ተወግቶ ከተገደለው ኤርትራዊ በረከት ሶሎሞን ሞት ጋር በተያያዘ አምስት ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ።

የ20 ዓመቱ ወጣት በረከት አስከሬን በተደጋጋሚ በስለት ተወግቶ የተገኘው ሰኔ 30/2014 ዓ.ም. ነበር በኽርትፎርድሻየር ፖሊስ የተገኘው።

በታዳጊነቱ ወደ እንግሊዝ እንደመጣ የተነገረው በረከት ሶሎሞን ግድያ ጋር በተያያዘ አምስት ሰዎች በፖሊስ ተይዘው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከግድያው ጋር በተያያዘ ድጋፍ በመስጠት እጁ አለበት የተባለ ሌላ አንድ ግለሰብ ፖሊስ ባካሄደው ምርመራ ተለቋል። ፖሊስ አሁንም በግድያው ዙሪያ ለሚደረገው ምርመራ የሚያግዝ መረጃ ያላቸውና እስካሁን ያላሳወቁ ሰዎች ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

ከበረከት ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች ሁሉም በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ሲሆኑ፣ እነሱም ጄላኒ ኦማር፣ ሮቤል ምስጋኔ፣ መላከ ፍስሃ፣ ተመስገን ገብረመድኅን እና ናትናኤል ሐድጉ ናቸው።

ግድያው የተፈጸመበት ቦታ

የፎቶው ባለመብት, SOUTH BEDS NEWS AGENCY

የምስሉ መግለጫ, ግድያው የተፈጸመበት ቦታ

መጀመሪያ ላይ ጥቃቱ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ የነበረ ቢሆንም፣ በግድያው ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎች ስም ግን እንደሟች ስደተኞች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ያመለክታል።

የግድያውን ወንጀል የያዘው ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ የሆኑት ኢንስፔክተር ኢያን ማክፈርሰን እንዳሉት “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የበረከት ቤተሰቦች እንዲጽናኑ ምኞታችን ነው” ብለዋል።

“ምርመራችን ቀጥሏል፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተያዙትን ተጠርጣሪዎች ተከትሎ ክስ ተመስርቷል። ነገር ግን አሁንም መረጃ ያላቸው ምስክሮች ወደ ፖሊስ መጥተው ቃላቸውን እንዲሰጡ እንጠይቃለን” በማለት ጥሪ እቅርበዋል።