የመንግሥታቱ ድርጅት እስራኤል በጋዛ ሆስፒታል ላይ በተከታታይ ለፈጸመቻቸው ጥቃቶች ፍትህ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል በጋዛ ሆስፒታል ላይ በተከታታይ ጥቃት ፈጽማ ቢያንስ 20 ሰዎችን ከገደለች በኋላ "ፍትህ ሊሰፍን ይገባል" አለ።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ "በሐማስ የተቀመጠ ካሜራ" ላይ ያነጣጠረ ነበር ብሏል።
አምስት ጋዜጠኞች እና አራት የጤና ባለሙያዎችን የገደለው ይህ ጥቃት ከበርካታ አካላት የሚያጋጥመው ውግዘት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር "ፍፁም ምክንያት ሊቀረብለት የማይችል" ሲሉ ገልጸውታል።
ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ጥቃቱን በተመለከተ በርካታ "ክፍተቶችን" ማግኘቱን አስታውቆ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልገው በመግለጫው ላይ ተናግሯል።
ይህ የሆነው እስራኤላውያን ታጋቾቹ እንዲለቀቁ መንግሥታቸው የቀረበለትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቀበል በመጠየቅ በመላ አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፎችን ባደረጉበት ወቅት ነው።
ሰኞ ዕለት በካን ዮኒስ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ላይ የተፈጸመው የመጀመርያው ጥቃት ቢያንስ አንድ ሰው፣ ከሆስፒታሉ ሕንጻ ጎን ደረጃ ላይ ሆኖ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ እየሰራ የነበረ የሮይተርስ ካሜራ ባለሙያን ገድሏል።
ከ10 ደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ ቦታ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመው ጥቃት ግን ጋዜጠኞች እና የነፍስ አድን ሠራተኞችን መትቷል።
በዚህ ጥቃት ለአሶሼትድ ፕሬስ፣ ሮይተርስ፣ አልጀዚራ እና ሚድል ኢስት አይ የሚሰሩ አምስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ አራት የጤና ባለሙያዎች የተገደሉ ሲሆን በአጠቃላይ በትንሹ 20 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ታሚን አል ኬታን ማክሰኞ ዕለት "ይህ አስደንጋጭ እና ተቀባይነት የሌለው ነው" ብለዋል።
"ይህ በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በተመለከተ ብዙ፣ ብዙ ጥያቄዎችን ያጭራል። እና እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ፍፁም ምርመራ ሊደረግላቸው እና ተጠያቂዎችም ሊጠየቁ ይገባል።"
ቀደም ሲል እስራኤል በጋዛ ውስጥ ስለገደለቻቸው ሰዎች የተደረገውን ምርመራ በተመለከተ ሲናገሩ "እነዚህ ምርመራዎች ውጤት ማምጣት አለባቸው። ፍትህ ሊኖር ይገባል። እስካሁን ድረስ ውጤት ወይም የተጠያቂነት እርምጃዎችን አላየንም።"
የእስራኤል መከላከያ ባወጣው መግለጫ ላይ ሐማስ በሆስፒታሉ አካባቢ "የመከላከያ ሠራዊቱ እንቅስቃሴን ለመከታተል የሚያገለግል" ካሜራ ማስቀመጡን ለይተናል ሲል ተጨማሪ ማስረጃ ሳይሰጥ ተናግሯል።
መግለጫው አክሎም "ወታደሮቹ ካሜራውን በመምታት እና በማውደም ስጋቱን ለማስወገድ ጥረት አድርገዋል" ብሏል።
ከተገደሉት መካከል ስድስቱ "አሸባሪዎች" ናቸው ሲልም ደምድሟል።
በኋላ ላይ የወታደራዊ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ እና ለአሶሼትድ ፕሬስ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ዒላማ አለመደረጋቸውን ተናግረዋል።
የመከላከያ መግለጫ ሰኞ ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "አሳዛኝ ጥፋት" ሲሉ ከሰጡት መግለጫ የተለየ ይመስላል።
የእስራኤል መከላከያ የመጀመርያውን ጥቃት ከፈጸመ ከደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛው ጥቃት ለምን እንደተፈጸመ አልገለፀም።
ይልቁንም ጥቅም ላይ የዋሉትን ጥይቶች እና ወታደራዊ ትዕዛዙን በተመለከተ "የመስክ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱን" ጨምሮ በፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
እስራኤል በጦርነቱ ጊዜ ሁሉ ምንም እንኳ በዓለም አቀፍ ሕግ ከለላ ቢደረግላቸውም በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎችን ሐማስ እየተጠቀመባቸው ነው በሚል ደጋግማ ዒላማ አድርጋለች።
በቴል አቪቭ እና በሌሎች ከተሞች ተቃዋሚዎች ጎማ እያቃጠሉ አውራ ጎዳናዎችን በመዝጋት መንግሥታቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲቀበል በመጠየቅ ቀሪዎቹን በሐማስ የተያዙ ታጋቾችን እንዲያስመልስ እና ጦርነቱን እንዲያቆም ጠይቀዋል።
የእስራኤል መንግሥት ሐማስ የተቀበለውን የተኩስ አቁም ምክረ ሃሳብ ቀደም ሲል ተቀብሎት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ውድቅ አድርጎታል።
ኔታንያሁ መንግሥታቸው አሁን ሁሉም ታጋቾች በአንድ ጊዜ እንዲፈቱ የሚያደርግ የተለየ ስምምነት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
በጋዛ በሐማስ ከተያዙት 50 ታጋቾች መካከል 20ዎቹ ብቻ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በሐማስ ጥቃት ታግቶ የነበረው የናምሩድ ኮኸን አባት ዩዳ ኮኸን "እስራኤል ከኔታንያሁ እና ከአገዛዛቸው በተቃራኒ ቆማለች" ብለዋል።
"ሌላ የተቃውሞ ቀን፣ የታጋቾቹ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን የማረጋገጫ ሌላ ቀን። ኔታንያሁ ላይ ጫና ለመፍጠር እና ጦርነቱን እንዲያቆሙ እና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የማስገደድ ሌላ ቀን።"
በእየሩሳሌም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የጸጥታው ካቢኔ ስብሰባ እያካሄደበት ባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደጃፍ ተሰብስበው ነበር።
በተኩስ አቁም ድርድር ላይ ከተሳተፉት መካከል አንዷ የሆነችው ኳታር አደራዳሪዎች አሁንም በቅርቡ ለቀረበው ምክረ ሃሳብ ከእስራኤል "ምላሽ እየጠበቁ ናቸው" ብላለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጅድ አል አንሳሪ "በጠረጴዛው ላይ ለቀረበው ምክረ ሃሳብ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነቱ አሁን በእስራኤል እጅ ነው።ሌላ ማንኛውም ነገር ፖለቲካዊ ማሳያ ነው" ብለዋል።
በጋዛ የሚገኘው በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው የ75 ፍልስጤማውያን አስከሬን ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ወደ ተቋሙ መምጣቱን አስታውቋል።
እስራኤል ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እና ከአገር ውስጥ ሰፊ ተቃውሞ ቢያጋጥማትም ሠራዊቷ የጋዛ ከተማን እንዲቆጣጠር ዕቅድ አውጥታለች። የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ሐማስ ትጥቅ እንዲፈታ እና ሁሉንም ታጋቾች ለመልቀቅ ካልተስማማ ጋዛ ከተማ እንደምትወድም ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው ተቋም በጋዛ ከተማ እና አካባቢው ረሃብ እየተከሰተ መሆኑን አረጋግጧል።
እንደ ድርጅቱ ሪፖርት ከሆነ በመላ ጋዛ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች "በረሃብ፣ ችጋር እና ሞት" የተነሳ "አሰቃቂ" ሁኔታዎች እያጋጠሟቸው ነው ብሏል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ ረሃብ የለም በማለት ሪፖርቱን "ፍጹም ውሸት" ስትል አጣጥላለች።
መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን ካገተ በኋላ የእስራኤል መከላከያ በጋዛ መጠነ ሠፊ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 62,819 ሰዎች ተገድለዋል ሲል የግዛቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አብዛኛው የጋዛ ሕዝብ በተደጋጋሚ ተፈናቅሏል። ከ 90 በመቶ በላይ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ፈራርሰዋል ወይም ወድመዋል ተብሎ ይገመታል።
በግዛቲቱ የሕክምና ተቋማት፣የውሃ፣የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ሥርዓቶች በሙሉ ወድመዋል።















