በትግራይ ክልል ከፍተኛ የተባለ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመዘገበ

የፎቶው ባለመብት, DT
በትግራይ ክልል ከተሞች በሬክተር ስኬል እስከ 5.6 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተዘገበ።
የጀርመኑ የሥነ-ምድር ሳይንስ የጥናት ማዕከል ትናንት ቅዳሜ ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም. በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽት 1፡01 ላይ የመሬት መንቀጥቀጡ አጋጥሟል ብሏል።
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በበኩሉ ከመቀሌ ሰሜን ምሥራቅ 56 ኪሎሜትር ርቆ 5.2 እና 5.6 የተለኩ ሁለት ርዕደ መሬቶች በተከታታይ መመዝገባቸውን አስታውቋል።
ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በትግራይ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች መሰማቱን ጨምሮ ገልጿል።
በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ቅዳሜ ምሽት፣ ሁለት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን እና ንዝረቱ ከዚህ ቀደም ካጋጠሙት የመሬት መንቀጥቀጦች ጠንከር ብሎ የሚሰማ እንደነበር ዘግቧል።
በትግራይ ለሁለት ጊዜ በ17 ደቂቃ ልዩነት ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 5.6 መለካቱን የጀርመኑ የሥነ ምድር ሳይንስ ጥናት ማዕከልም መዝግቧል።
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በበኩሉ ቅዳሜ 9 ሰዓት አካባቢ በሬክተር ስኬል 4.2 የተላከ ሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ ከመቀለ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለ ቦታ ላይ መድረሱን ገልጿል።
ቅዳሜ ምሽት ከደረሱት የመሬት መንቀጥቀጦች የመጀመሪያው የተመዘገበው ከመቀለ ከተማ 56 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለ ቦታ ላይ መሆኑንም የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ ያሳያል።
የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በመቀለ እና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎችም የተሰማ ነበር።
በትግራይ ከተሞች ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው በ10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ መሆኑን የገለፀው የጀርመኑ የሥነ ምድር ጥናት ሳይንስ እንዲህ ዓይነት የመሬት መንቀጥቀጦች ለመሬት ውጭያዊ አካል ቅርብ በመሆናቸው በደንብ ሊሰሙ ይችላሉ ሲል አብራርቷል።
ቮልኬኖ ዲስከቨሪ በበኩሉ 5.5 የተመዘገበ ንዝረት ከውቅሮ ከተማ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሰማቱን መዝግቧል።
የርዕደ መሬቱ ንዝረት ከውቅሮ በተጨማሪ በሻጉባይ፣ ዶሎ፣ በእዳጋ ሐሙስ እና በአዲግራት ከተሞች እንደተሰማ ድረ ገጹ ጨምሮ ገልጿል።
በትግራይ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲሰማ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ በእነዚህ አካባቢዎች ተመሳሳይ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሞ ነበር።
በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙት የኢትዮጵያ ከተሞች ለርዕደ መሬት የተጋለጡ መሆናቸው ይነገራል።















