በቻይና ስታዲየም በተፈጸመ የመኪና ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በደቡባዊ ቻይና በተፈጸመ የመኪና ጥቃት ቢያንስ 35 ሰዎች ተገደሉ። በአገሪቱ ባለፉት አሥርት ዓመታት በላይ በሕዝብ ላይ የተፈጸመ እጅግ አስከፊው ጥቃት እንደሆነ ይታመናል።
ፖሊስ እንደገለጸው ከሆነ ሰኞ ዕለት አንድ ግለሰብ ዙሃይ በሚገኘው ስታዲየም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎችን በመኪናው ገጭቷል።
“በአስከፊው እና በአሰቃቂው ጥቃት” አዛውንቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 45 ሰዎችም መቁሰላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ፖሊስ እንዳለው ከሆነ የ62 ዓመቱ አሽከርካሪ ፋን እንደሚባልና ድርጊቱን የፈጸመው በፍቺው ውሳኔ ዙሪያ ደስተኛ ባለመሆኑ የተነሳ ይመስላል ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግለሰቡ ከዙሃይ ስፖርት ማዕከል ለመሸሽ ሲሞክር በቁጥጥር ስር መዋሉን እና በራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት ኮማ ውስጥ እንደሚገኝ ፖሊስ በመግለጫው አክሏል።
ክስተቱ በቻይና ብሔራዊ ቅሬታን የቀሰቀሰ ሲሆን ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው ወንጀል ፈጻሚው ግለሰብ "ከባድ ቅጣት" እንደሚጠብቀው ቃል ገብተው የተጎዱትን ለማከም "ሁሉን አቀፍ ጥረት" እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ስለተገደሉት ሰዎች ዝርዝር መረጃ በባለሥልጣናት በኩል አልተገለጸም። ሐዘንተኞች እና ነዋሪዎች ማክሰኞ ዕለት ከስታዲየም ውጭ አበባዎችን እና ሻማዎችን ማስቀመጥ ጀምረዋል።
ጥቃት የደረሰበት ስፍራ በአካባቢው ነዋሪዎች ተወዳጅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ ማዕከል ነበር። ፋን ሆን ብሎ ሰዎችን ያጠቃ ይመስላል ሲሉ የዓይን እማኞች ለቻይና መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ቼን የተባለ አንድ ግለሰብ እሱ እና የቡድን አጋሮቹ ሮጠው እንደጨረሱ “ብዙ ሰዎችን እየገጨ” በፍጥነት የሚመጣ መኪና መመልከታቸውን ለቻይሲን የዜና መጽሔት ተናግሯል።
በስፍራው የነበረ ሌላ ሰው በበኩሉ "እየተዘዋወረ በመግጨቱ በሁሉም የሩጫ ስፍራዎች ሰዎች ተጎድተዋል።" ብሏል
የመጀመሪያ የምርመራ ውጤትን ተንተርሶ ማክሰኞ ዕለት መግለጫ የሰጠው የአካባቢው ፖሊስ እንደገለጸው ከሆነ ፋን ጥቃቱን የፈጸመው ፍቺን ተከትሎ በተፈጠረ የንብረት ክፍፍል አለመግባባት እንደሆነ ጠቁሟል። ኮማ ውስጥ መሆኑን እና ምንም አይነት ጥያቄ እንዳልቀረበለት ፖሊስ ተናግሯል።
ጥቃቱ ከቅርብ አስርት ዓመታት ወዲህ በቻይና ውስጥ በሕዝብ ላይ የተፈጸመ ድርጊት ሊሆን ይችላል። በየካቲት ወር በሻንዶንግ ቢያንስ 21 ሰዎችን የገደለ የጅምላ የስለት እና የጦር መሳሪያ ጥቃትን ጨምሮ በዚህ ዓመት በርካታ ጥቃት ተዘግቧል። ክስተቱ በቻይና ባለስልጣናት ከፍተኛ ሳንሱር ተደርጎበታል።

የፎቶው ባለመብት, BBC/ ED LAWRENCE
የሰኞው ጥቃት የሚመለከቱ ሪፖርቶች ማክሰኞ ዕለት በበይነ መረብ ላይ እንዲገደቡ ተደርገው ነበር። በቦታው የነበሩ ምስክሮች የቀረጿቸው በርካታ ቪዲዮዎች ከቻይና ማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ተወግደዋል።
አሁንም በበይነ መረብ እየተሰራጩ ያሉ አንዳንድ ምስሎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መሬት ላይ ተኝተው እና በሕክምና ባለሙያዎች ድጋፍ ሲደረግላቸው ያሳያሉ።
በቻይና ከከፍተኛ የወንጀል ክስተቶች ጋር የተያያዙ የማህበራዊ ሚዲያ ቪዲዮዎችን በፍጥነት ማውረድ የተለመደ ነው።
ማክሰኞ ዕለት ጁሃይ የሚገኘው ስታዲየም ለዘገባ የደረሱት የቢቢሲ ጋዜጠኞችም ከደረሰባቸው እንግልት በተጨማሪ ቀረጻ እንዲያቆሙ ተነግሯቸዋል።
ቻይና ከቅርብ ወራት ወዲህ በህብረተሰቡ ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በተለያየ ደረጃ ዘግበዋል።
በጥቅምት ወር በቤጂንግ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ውስጥ በስለት በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች ቆስለዋል። በመስከረም ወር ደግሞ አንድ ግለሰብ በሻንጋይ ሱፐርማርኬት በፈጸመው የስለት ጥቃት ሦስት ሰዎችን ገድሎ በርካቶችን አቁስሏል።
በተመሳሳይ በመስከረም ወር የ10 ዓመት ጃፓናዊ ተማሪ በደቡብ ቻይና በሚገኘው ትምህርት ቤቱ አካባቢ በስለት ጥቃት ከደረሰበት ከአንድ ቀን በኋላ ህይወቱ አልፏል።
የሰኞውን የመኪና ጥቃት ተከትሎ የጃፓን ኤምባሲ በአገሪቱ የሚኖሩ ዜጎቹ ጃፓንኛ ቋንቋን በአደባባይ ጮክ ብለው ከመናገር እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል።
በዚህ ሳምንት ከፍተኛ ወታደራዊ የአየር ትዕይንት በምታስተናግደው ዙሃይ ጥበቃው በተጠናከረበት ወቅት ነው ክስተቱ ያጋጠመው። የሰኞ ምሽቱ ጥቃት የተፈጸመው ኤርሾው ቻይና ማክሰኞ ዕለት ከጀመረበት 40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው።
ቻይና አዳዲስ የጦር አውሮፕላኖቿን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በማሳየት ላይ ትገኛለች። የሩሲያ የመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣን እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ በስፍራው ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የማዕከሉ አስተዳደር ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ከሆነ በአየር ትዕይንቱ ወቅት የስፖርት ማዕከሉ በርካታ መግቢያ እና መውጫ መግቢያዎች ተዘግተዋል።












