ጭምብል አጥልቆ አሜሪካዊውን ባለሀብት ገድሎ የተሠወረው ግለሰብ እየታደነ ነው

ተጠርጣሪው ከግድያው በፊት አንድ ካፌ ውስጥ ታይቶ ነበር

የፎቶው ባለመብት, NYPD

የምስሉ መግለጫ, ተጠርጣሪው ከግድያው በፊት አንድ ካፌ ውስጥ ታይቶ ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ጭምብል አጥልቆ የኢንሹራንስ ኩባንያውን ዋና ሥራ አስኪያጅ ገድሎ የተሰወረውን ግለሰብ እያደነው እንደሆ አስታወቀ።

መርማሪዎች ግድያው “ዓይን ያወጣ እና የታቀደበት” ነው ሲሉ ገዳዩን ለመያዝ እየተረባረቡ እንደሆ አስታውቀዋል።

ዩናይትድሄልዝኬር የተባለው ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብራያን ቶምፕሰን ረቡዕ ዕለት ነው የተገደለው።

የ50 ዓመቱ ቶምፕሰን በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋት 1 ሰዓት አካባቢ ማንሀታን ወደሚገኘው ሒልተን ሆቴል ሲያመራ ነው ጀርባውን በጥይት ተመትቶ የተገደለው።

ግድያው የታቀደበት ነው የሚለው ፖሊስ ገዳዩ ወዲያው ከሥፍራው ማምለጡን ገልፆ፣ ፊት መለያ ቴክኖሎጂ እና መንገድ ላይ ተጥሎ የተገኘ ስልክ በመጠቀም ፍለጋውን መቀጠሉን ይፋ አድርጓል።

ገዳዩ እንዴት ሊያመልጥ ቻለ?

ግድያው የተፈፀመው በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር 12፡45 ነው። ሥፍራው ደግሞ ማንሀታን ተብሎ ይታወቃል። ቶምፕሰን ረቡዕ በአንድ ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ለማድረግ ነው የተገኘው።

ፖሊስ እንደሚለው ተጠርጣሪው ጥቁር ጭምብል አጥልቆ ቆብ ያለው ጃኬት አድርጎ ቶምፕሰን እስኪወጣ ድረስ ለአምስት ደቂቃ ጠብቆታል።

በእግሩ ከሆቴል የወጣው ቶምፕሰን ጀርባውን እና እግሩን በጥይት የተመታ ሲሆን፣ ወደ አካባቢው ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

የኒው ዮርክ ፖሊስ መርማሪዎች ኃላፊ ጆሴፍ ኬኒ እንዳሉት ተጠርጣሪው መጀመሪያ ሽጉጡ አስቸግሮት የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን አስተካክሎ ነው ቶምፕሰንን የመታው።

ገዳዩ መጀመሪያ ከአካባቢው በእግር ሲያመልጥ የታየ ሲሆን፣ ሴንትራል ፓርክ በተባለው ሥፍራ ደግሞ የኤሌክትሪክ ብስክሌት ሲነዳ መታየቱ ተነግሯል።

ብራያን ቶምፕሰን

የፎቶው ባለመብት, UnitedHealth

የምስሉ መግለጫ, ባለሀብቱ የኢንሹራንስ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ብራያን ቶምፕሰን

ምርመራው የት ደረሰ?

እስካሁን ባለው ሁኔታ ፖሊስ የተወሰነ ማስረጃዎችን ይዞ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው።

ፖሊስ እንደሚለው ተጠርጣሪው ከግድያው ከደቂቃዎች በፊት ስታርባክስ የተባለ ካፌ አካባቢ እንደነበር በካሜራ ታይቷል።

ምንም እንኳ ግለሰቡ ጭምብል ቢያጠልቅም ዓይኑ እና የአፍንጫው የተወሰነ ክፍል እንደሚታይ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

መርማሪዎች ፊት የሚለይ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሰውየውን ማንነት ለመለየት ሙከራ እያደረጉ እንደሆነ ተሰምቷል።

በተጨማሪ በግድያ ሥፍራው ወድቀው የተገኙ ሦስት ቀለሀዎች እና ሦስት እርሳሶች የዘረ-መል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።

ከዚህ ባለፈ ፖሊስ ተጠርጣሪው ባመለጠበት መንገድ ላይ ሞባይል ስልክ ማግኘቱን አስታውቋል።

መርማሪዎች ቶምፕሰን ያረፈበት ማሪዮት ሆቴል ገብተው የተኛበትን ክፍል እንደሚፈትሹ ተናግረዋል። ማሪዮት ሆቴል ግድያው ከተፈፀመበት ሥፍራ መንገድ ተሻግሮ የሚገኘው ነው።

መርማሪዎች እስካሁን ለምን ተጠርጣሪው ግድያውን እንደፈፀመ ማወቅ አልቻሉም። ገዳዩ የቶምፕሰንን ምንም ዓይነት ንብረት ሳይወስድ ነው የሸሸው።

የቶምፕሰን ሚስት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በሰጠችው ቃል መሠረት ባሏ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አንዳንድ ዛቻዎች” ይደርሱበት ነበር።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በተለመከተ ጠቃሚ መረጃ ለሚሰጡ ሰዎች የ10 ሺህ ዶላር ወሮታ ለመክፈል ቃል ገብቷል።