በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ የተባበረው የቀድሞ ፖሊስ ተጨማሪ እስራት ተፈረደበት

ጄ አሌክሳንደር ኩንግ

የፎቶው ባለመብት, STAR TRIBUNE VIA GETTY IMAGES

ታትሟል

የቀድሞ የሚኒያፖሊስ ከተማ የፖሊስ ባልደረባ ጆርጅ ፍሎይድ ጀርባ ላይ በመቆም ለግድያው በመተባበሩ የሦስት ዓመት ተኩል እስር ተፈረደበት።

ጄ አሌክሳንደር ኩንግ ጥፋተኛነቱን አምኗል። በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ከተያዙ አራት ፖሊሶች አንዱ ነው።

ፍሎይድ እአአ በ2020 በፖሊሶች ተይዞ፣ አንደኛው ፖሊስ በጉልበቱ የፍሎይድን አንገት አፍኖ ነበር ሕይወቱ ያለፈው።

ሞቱ ዘረኝነት እና የፖሊስ ጭካኔን የሚቃወም ከፍተኛ ሕዝባዊ ቁጣን በአሜሪካ እና በመላው ዓለም ቀስቅሷል።

የቀድሞው ፖሊስ ከዚህ በፊት የፍሎይድን ሰብአዊ መብት በመጣስ የተፈረደበት ሲሆን፣ የአሁኑ በቀደመው ላይ ተጨማሪ የእስር ጊዜ ተፈርዶበታል።

በ2021 የቀድሞው የፖሊስ ባልደረባ ዴሬክ ሾቪን ፍሎይድ አንገት ላይ ለዘጠኝ ደቂቃ ተንበርክኮ በመግደል የ22 ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶበታል። ከዚህ ጎን ለጎን በሰብአዊ መብት ጥሰት የ20 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ከዚሁ ግድያ ጋር በተያያዘ ጄ አሌክሳንደር ኩንግ፣ ቶማስ ሌን እና ቶው ታዎ የተባሉ ሌሎች ፖሊሶችም በሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈርዶባቸዋል።

ፖሊሶቹ ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክሩ ለገጠመው የጤና እክል ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው ነው ብይኑ የተላለፈው።

ኩንግ እና ሌን በጋራ ሆነው ሾቪን የተባለው የቀድሞ ፖሊስ በፍሎይድ አንገት ላይ ተንበርክኮ ሲያፍነው ተባብረዋል።

ታዎ ደግሞ በአካባቢው የነበሩ እግረኞችን ሲያባርር ነበር።

ሾቪንን ጨምሮ በግድያው የታሰሩት ፖሊሶች ከቀረቡባቸው ክሶች አንዱ፤ ኩንግ የተባለው የቀድሞ ፖሊስ ፍሎይድን ለማዳን ጣልቃ ባለመግባቱ የተፈረደበት የ36 ወራት እስራት ይገኝበታል።

በተጨማሪም ታዎ በተመሳሳይ ክስ የ42 ወራት እስራት የተፈረደበት ሲሆን፤ ቶማስ ሌን በግድያ የሁለት ዓመት ተኩል እና የሦስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

የፍርድ ውሳኔው ሲተላለፍ ዐቃቤ ሕግ ማቲው ፍራንክ ኩንግ በግድያው ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው ብለዋል።

የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ ጠበቃ “ውሳኔው ለፍሎይድ ቤተሰብ ፍትሕን ያሰፈነ ነው” ብለዋል።

“ቤተሰቡ ያለ ፍሎይድ ሌላ ዓመት በዓል ሊያሳልፍ ነው። እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች በመጠኑም ቢሆን መጽናናት ይሰጧቸዋል ብዬ አምናለሁ” ሲሉም አክለዋል።