በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ከተከሰሱት ፖሊሶች የመጨረሻዎቹ ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል ክስ ከተመሠረተባቸው የቀድሞ ፖሊሶች መካከል የመጨረሻዎቹ ፍርደኞች ላይ ብይን ተላለፈ።
የቀድሞ የሚኒያፖሊስ ፓሊስ ጄ አሌክሳንደር ኬይንግ ሦስት ዓመት፣ ቶ ታዎ የተባለው የቀድሞ ፖሊስ ደግሞ 42 ወራት እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የፖሊስ አባlኣቱ እስር የተፈረደባቸው በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ውስጥ ተባብረዋል ተብሎ ነው።
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን ፖሊሶች ካስቆሙትበኋላ ዴሬክ ሻውቪን የተባለው ፖሊስ አንገቱ ላይ በጉልበቱ ተንበርክኮ በማፈን ገድሎታል።
እነዚህ የቀድሞ ፖሊስ አባላት ፍሎይድ ላይ የደረሰውን እንግልት ጣልቃ ገብተው ባለማስቆማቸው ነው ፍርድ ቤት እስራት የፈረደባቸው።
ፍሎይድ በፖሊሶች ሲገደል የሚያሳየው ቪድዩ በአንዲት መንገደኛ ተቀርጾ ከተለቀቀ በኋላ ከአሜሪካ አልፎ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ቀስቅሷል።
መሣሪያ ያልታጠቀውን ፍሎይድ ያስቆሙት ፖሊሶች መሪ የነበረው ዴሬክ ሻውቪን ፍሎይድ አንገት ላይ ተንበርክኮ ሲያፍነው፣ ጄ አሌክሳንደር ኬይንግ የፍሎይድን እግር በመያዝ ተባብሯል። ቶ ታዎ ደግሞ መንገደኞች ጣልቃ እንዳይገቡ ሲከላከል ነበር።
ዴሬክ ሻውቪን በግድያ ተከሶ አምና እስራት ተፈርዶበታል።
ሌላው የቀድሞ ፖሊስ ቶማስ ኬ ሌን ባለፈው ሳምንት የሁለት ዓመት ተኩል እስር ተወስኖበታል።
በቦታው የነበሩ ፖሊሶች የፍሎይድን ተማጽኖ ችላ በማለትና የሚያስፈልገውን፣ የሕክምና እርዳታ በመንፈግ ተፈርዶባቸዋል።
ፍሎይድ ለመተንፈስ ተቸግሮ ሲያጣጥር ዴሬክ ሻውቪን ጉልበቱን ከአንገቱ ላይ አላነሳም ነበር።
ፍሎይድ ደጋግሞ “መተንፈስ አልቻልኩም” በማለት ፖሊሱ ጉልበቱን ከአንገቱ ላይ እንዲያነሳለት ቢለምነውም ፖሊሱ ተማጽኖውን ችላ ብሏል።
በወቅቱ ቶማስ ኬ ሌን እና ጄ አሌክሳንደር ኬይንግ በዋና ፖሊሱ ዴሬክ ሻውቪን ሥር የመስክ ሥልጠና እየወሰዱ ነበር።
ፍሎይድ ሲታፈን ግን አንዳችም እርዳታ አልሰጡትም።
እስር ሲበየንባቸው ምንም ባይሉም፣ ጄ አሌክሳንደር ኬይንግ በፍሎይድ ግድያ ከታሰረ በኋላ “ተለውጫለሁ” ብሏል።
“እስር ቤት እንደገባሁ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ያነሳሁት። ለዚህ ሁሉ ሰቆቃ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ፈለግኩ፣ ፈለግኩ። ግን መልሱም አላገኘሁም” ሲልም ተደምጧል።
የፍሎይድ ፍቅረኛ ኮርኒ ሮስ የፍርድ ውሳኔው ሲተላለፍ “ጆርጅ የሕይወቴ ሕይወት ነበር። ያን ቀን ፖሊሶቹን እየታገላቸው አልነበረም። በትንሽዬ እስር ቤት ክፍል ሲገቡ፣ ጆርጅን የገደሉት ቀን ምን እንደተሰማው ያስታውሳሉ” ብላለች።












