የኒውዮርክ ፖስት ጋዜጠኛን በገጀራ ያስፈራሩት የኮሌጅ ፕሮፌሰር ከሥራ ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሃንተር ኮሌጅ ፕሮፌሰር የኒው ዮርክ ፖስት ሪፖርተርና ፎቶ አንሺን በገጀራ በማስፈራራታቸው ሥራቸውን አጥተዋል።
ጋዜጠኞቹ ወደ ፕሮፌሰር ሼሊአን ሮድሪጉዌዝ ቢሮ ያቀኑት በቅጥር ግቢው ስለተካሄደው ፀረ-ጽንስ ማቋረጥ ሰልፍ ቃለ-መጠይቅ ለማድረግ ነው።
ኒው ዮርክ ፖስት እንዳለው ፕሮፌሰሯ ይህን ሰልፍ በመቃወማቸው ነው ጋዜጠኞቹ ሊያናግሯት የሻቱት።
ተንቃሳቃሽ ምስል ላይ እንደሚታየው ሼሊአን ሁለቱን ግለሰቦች በገጀራ አሳደዋቸዋል።
የኒው ዮርክ ከተማ ዩኒቨርሲቲ አካል የሆነው ሃንተር ኮሌጅ “ከሥራቸው ተነስተዋል” ሲል የፕሮፌሰሯን መባረር አሳውቋል።
ፕሮፌሰሯ በግቢው የተካሄደውን ሰልፍ ሲቃወሙ የሚሳይ አንድ ምስል መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ሪፖርተር ሩቨን ፌንተን እና የፎቶ ባለሙያው ወደ ፕፎፌሰሯ ያቀኑት ይህን ጉዳይ ይዘው ነበር።
ኒው ዮርክ ፖስት እንደዘገበው ከሆነ “ከበሬ ሂዱልኝ፤ ካልሆነ በዚህ ገጀራ ነው የምከትፋችሁ” ሲሉ ዝተዋል።
የጋዜጣው ዘገባ አክሎ “በሩን ሲከፍቱ ገጀራውን የጋዜጠኛው አንገት ግድም አድርገው ነበር” ይላል።
የጋዜጣው ባልደረቦች ከሥፍራው ወዲያው ቢወጡም ፕሮፌሰሯ እንደተከተሏቸው ይገልጣሉ።
ይሄኔ ነው አንድ በአቅራቢያው ያለ መኪና በካሜራው ጋዜጠኞቹ በፕሮፌሰሯ ሲሳደዱ ምስል ማስቀረት የቻለው።
ይህን ተንቀሳቃሽ ምስል ኒው ዮርክ ፖስት በማሕበራዊ ገፁ ለተከታዮቹ አጋርቷል።
የሃንተር ኮሌጅ ቃል አቀባይ ቪንስ ዲሚቼሊ “ኮሌጁ ተቀባይነት የሌለው የሼሊአን ሮድሪጉዌዝ ድርጊትን ይቃወማል፤ አስፈላጊውን እርምጃም ወስዷል” በማለት ቃላቸውን ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
“ሮድሪጉዌዝ ከሥራቸው ወዲያውኑ ተነስተዋል። ከዚህ በኋላም እዚህ ትምህርት ቤት አያስተምሩም።”
ስቱደንት ፎር ላይፍ የተሰኘውና ከ120 ሺህ በላይ ወጣት አባላት ያሉት ፅንስ ማቋረጥን የሚቃወም ድርጅት ነው ሰልፍ የጠራው።
አስተማሪዋ ይህንን ሰልፍ በመቃወም “እያስተማራችሁ አይደለም. . . ይህ ፕሮፖጋንዳ ነው። ይህ አመፅ ነው። ተማሪዎቼን እያነሳሳችሁ ነው” ሲሉ ታይተዋል።
በቃላት ልውውጥ በታጀበው ምስል ላይ አስተማሪዋ፤ ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ሲያዙ ከዚያም ከአዳራሹ ጥለው ሲወጡ ይታያሉ።
የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ክስተቱ መፈጠሩን አምኖ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ ገልጧል።
አስተማሪዋን ለማግኘት የተደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም።












