የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጠባቂዎች ከፖላንድ እንዳይወጡ መደረጉ እያወዛገበ ነው

ልዑካን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፖላንድ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጠባቂዎች እና መገናኛ ብዙኃን ከ24 ሰዓታት በላይ ወደ ፖላንድ እንዳይገቡ የተደረገው በዘረኝነት ምክንያት አይደለም አለች።

በዋርሳው ቾፒን አውሮፕላን ማረፊያ ፍጥጫ ተከስቶ መነጋገሪያ ሆኗል።

አውሮፕላኑ እስከ ነገ ድረስ እዛው እንደሚቆይም የአውሮፕላን ማረፊያው ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አውሮፕላኑ ውስጥ ወደ 120 ሰዎች አሉ። ወደ ዩክሬኑ የሰላም ውይይት እየተጓዙ ነበር።

አንዳንዶቹ ተጓዦች ወደ ሆቴል እያመሩ ነው።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቀድመው ወደ ዩክሬን በመሄዳቸውን ጠባቂዎቻቸው ከፖላንድ እንዳያልፉ በመከልከሉ ፕሬዝዳንቱ ያለ ጠባቂ እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል።

የራማፎሳ ዋና ጠባቂ በተፈጠረው ነገር እጅግ ተበሳጭተዋል።

ዋና ጠባቂው ሜጀር ጀነራል ዋሊ ሮዴ “እያዘገዩን ነው። የፕሬዝዳንታችንን ሕይወት አደጋ ውስጥ እየጣሉ ነው” ብለዋል።

“የሚያደርጉትን ተመልከቱ። ይሄ ዘረኝነት ነው” ሲሉም አክለዋል።

ፖላንድ ግን ዘረኝነት አይደለም ብላለች።

የፖላንድ ብሔራዊ ደኅንነትና የልዩ ኃይል አስተባባሪ ቃል አቀባይ ስታሊው ዛሪን “ፖላንድ ዘረኛ ናት እየተባለ ነው። ይሄ ትርጉም አልባ ነው። ሕገ ወጥ መሣሪያ የያዙ ተጓዦችን ወደ አውሮፓ ኅብረት ማስገባት አንችልም” ሲሉ መልሰዋል።

መሣሪያቸውን አውሮፕላን ውስጥ ከተውት እንዲሄዱ እንደሚፈቀድላቸውም ገልጸዋል።

ነገሩ ወደ ዲፕሎማሲ ፍጥጫ አድጓል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ነገሩ “አሳዛኝ ነው” ብለዋል።

ቪንሰንት ምግዋንያ እንዳሉት የፕሬዝዳንቱ ጠባቂዎች ቢያንስ በሩሲያው ጉዞ ተገኝተው ሥራቸውን እንዲሠሩ ለማስቻል ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ቃል አቀባዩ እንደሚናገሩት ይህ የሚሆን አይመስልም።

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከፖላንድ በባቡር በሰላም የዩክሬን መዲና ኪዬቭ ገብተዋል።

አፍሪካውያኑ መሪዎች ከዩክሬን ቀጥሎ ወደ ሩሲያ በማምራት ሰላም የማውረድ ተልዕኳቸውን ይቀጥላሉ።

“ሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን እንዲያውቁ የምፈልገው የፕሬዝዳንቱ ሕይወት አደጋ ላይ የሚወድቅበት ዕድል እንደሌለ ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

የአፍሪካ ልዑካን ጉብኝት እያደረጉ ሳለ የሚሳዔል ጥቃት ተሰንዝሯል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሜትሮ ኩልባ እንዳሉት ሩሲያ ሚሳዔል የተኮሰችው “ለአፍሪካ መልዕክት ለማስተላለፍ” ነው።

“ሩሲያ ተጨማሪ ጦርነት እንጂ ሰላም አትሻም” ብለዋል።

ባለፉት ወራት ሩሲያም ዩክሬንም በአፍሪካ አገራት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እየሞከሩ ነው።

ደቡብ አፍሪካ በጦርነቱ የማንም ወገን እንዳልሆነች ብትገልጽም በሩሲያ ጎን ቆማለች ስትል አሜሪካ ከሳታለች።

የደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ሴኔጋል፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ኮሞሮስ፣ ዛምቢያ እና ኡጋንዳ ልዑካል የዩክሬንን ፕሬዝዳንት ያነጋገሩ ሲሆን በቀጣይ የሩሲያን ፕሬዝዳንትን እንደሚያነጋግሩ ተገልጿል።