በደቡብ ኢትዮጵያ አዲስ ክልል ለመመስረት የሕዝበ ውሳኔ ድምጽ እየተሰጠ ነው

በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት የተሰለፉ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, nebe

የምስሉ መግለጫ, በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት የተሰለፉ ነዋሪዎች
ታትሟል

የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰቦች ክልልን በአዲስ መልክ ለማዋቀር በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ድምጻቸውን መስጠት ጀመሩ።

በሕዝበ ውሳኔው የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ክልል ውስጥ አንድ አዲስ ክልል ለመፍጠር ወይም ያለው ክልል እንዲቀጥል ውሳኔ ይሰጥበታል።

ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በደቡብ ክልል ውስጥ እንዲህ ያለው ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ ይህ ሦስተኛው ነው።

ቀደም ባሉት ሁለት ሕዝበ ውሳኔዎች የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በአዲስ የአስተዳደር መዋቅር ክልል ሆነው ወጥተዋል።

ዛሬ በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ድምጻቸውን ለመስጠት መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል።

በዛሬ ሰኞ ጥር 29/2015 ዓ.ም. የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በደቡብ ክልል ስር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ድምጽ ይሰጣል።

በዚህም በኮንሶ፣ በወላይታ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በጋሞ፣ በጌዲዮ እና በጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አማሮ፣ አሌ እና ዲራሼ ልዩ ወረዳዎች ወስጥ ሕዝበ ውሳኔው ይካሄዳል።

ነዋሪዎች በሚሰጡት ድምጽ መሠረት ከደቡብ ክልል በሚወጣ አዲስ ክልል ለመደራጀት ወይም በነባሩ ክልል ውስጥ ለመቀጠል ይወስናሉ።

በሕዝበ ውሳኔው አዲስ ክልል የሚመሠረት ከሆነ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየውን የደቡብ ክልልን በማክሰም፣ በምትኩ አንድ አዲስ ክልል እንዲመሰረት እና “ነባሩ” በአዲስ ቅርጽ እንዲዋቀር ያደርገዋል።

የኢህአዴግ ሥልጣን መያዝን ተከትሎ አገሪቱ ቋንቋ እና ማንነትን መሠረት ባደረገ ፌደራላዊ የክልል ሥርዓት ስትዋቀር ያልነበረው የደቡብ ክልል፣ አምስት ክልሎችን በማቀፍ ከእንደገና የተመሠረተ መሆኑ ይታወቃል።

ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች በተለየ ሁኔታ ከ50 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎ በተመሠረተው የደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ በርካታ ዞኖች የእራሳቸውን ክልል ለመመስረት ሲጠይቁ ቆይተዋል።

አሁን በሚካሄደው አዲስ አወቃቀር ላይ ተቃውሞን በማንሳት የራሳቸው ክልል የመመስረት ጥያቄን እያቀረቡ ይገኛሉ።

ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም 410 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቢቢሲ ገልጿል።

ቦርዱ በስድስት ዞኖች እና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ስር ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን 31 ማስተባበሪያ ማዕከላትን እና 3 ሺህ 752 የምርጫ ጣቢያዎችን ማደረጀቱንም ጠቅሷል።

በተጨማሪም ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች 4 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን አቋቁሟል።

በሕዝበ ውሳኔውን ከ11 ሺህ 400 በላይ አስፈጻሚዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ የመራጮች ምዝገባም ከታኅሣሥ 11 እስከ 26 ባሉት ቀናት ይከናወናል።

በሕዝበ ውሳኔው የቀረቡት አማራጮች በነጭ እርግብ እና በጎጆ ቤት [በደቡብ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው ዓርማ ዓይነት] የተወከሉ ሲሆን በአዲስ ክልል መደራጀት ደግሞ በነጭ ርግብ ተወክሏል።