ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመረተው አፈር መመርመሪያ መሣሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘ

ታትሟል

አፈር መርምሮ ምን ቢዘራ አዋጭ እንደሆነ የሚለው መሣሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች የተሠራው ይህ መሣሪያ ከሌሎች በጅምር ላይ ካሉ ኩባንያዎች ጋር በኡጋንዳ፣ ካምፓላ ተወዳድሮ አንደኛ ደረጃን በመያዝ የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት አግኝቷል።

ይህ በዓለም አቀፍ መድረክ ዕውቅና ያገኘው ‘ኦሚሽቱ-ጆይ’ ተብሎ የተሰየመው አፈር መመርመሪያ መሣሪያ ከጥቂት ዓመታት በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች ነበር የተሠራው።

አነስተኛ መጠን ያለው መሣሪያው፣ በአፈር ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች በመመርመር በዛ አፈር ውስጥ የትኛው ተክል ቢተከል ወይም የትኛው ዘር ቢዘራ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ይለያል።

ኦሚሽቱ-ጆይ በዓለም ባንክ በሚደገፈው 'Africa Start Up Award' ውድድር ከ23 አገራት ከተወጣጡ ሥራዎች ጋር ተወዳድሮ ነው በአንደኛነት በማጠናቀቁ ሽልማቱን የተረከበው።

መሣሪያው የአፈርን የንጥረ ነገር ይዘት፣ የሙቀት መጠን (ቴምፕሬቸር) እና እርጥባማነት ለይቶ ውጤቱን ወደ ስማርት ስልኮች ይልካል።

2013 ዓ. ም. ላይ ተማሪዎች ለመመረቂያ ፕሮጀክት ያነሱት ጽንሰ ሐሳብ በመምህራን ተደግፎ ከዚህ መድረሱን በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩተር ሳይንስ መምህር ጃርሚያ ባይሳ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በአንድ አካባቢ ዘር ከመዘራቱ በፊት አፈሩ ለየትኛው የዘር ዓይነት ምቹ እንደሆነ መለየት መቻል የምርት ውጤትን ከፍ ያደርጋል።

ግብርና የምጣኔ ሀብቷ የጀርባ አጥንት በሆነችው ኢትዮጵያ፣ የአፈር ምርመራ ማዕከላት ጥቂት ናቸው።

ለአፈር ምርመራ ማዕከላት የሚውሉ መሣሪያዎችም ውድ እና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉ ግዙፍ ናቸው።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ በመጠን አነስተኛ የሆነው አፈር መመርመሪያ መሣሪያ መፍትሄ ይዞ መምጣቱን ፈጣሪዎቹ ይናገራሉ።

መምህር ጃርሚያ ‘ኦሚሽቱ-ጆይ’ ሲል የሰየመው መሣሪያ፣ የአፈር ናሙና ከወሰደ በኋላ በአፈሩ ላይ ምርመራ አካሂዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአፈሩ ውስጥ ያለውን አሲድ፣ ንጥረ ነገሮች እና እርጥበት በመለየት ውጤቱን ወደ ሞባይል ስልክ ይልካል በማለት ያስረዳል።

መሣሪያው የረቀቀውን ሰው ሠራሽ ልኅቀት ቴክኖሎጂ (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ከመጠቀሙም በላይ መጠኑ አስተኛ በመሆኑ ሰዎች በቀላሉ ከቦታ ቦታ ይዘውት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ጃርሚያ ያስረዳል።

ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ሰዎችም መሣሪያውን በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ ጆይ-ኦሚሽቱ ትዕዛዝ በድምጽ ተቀብሎ የምርመራ ውጤቱን በድምጽ መግለጽ እንዲችል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጃርሚያ አክሏል።

“አንድ አርሶ አደር ስማርት ስልክ ካለው በድምጹ አዝዞ ውጤቱንም እንዲሰማ ለማድረግ እየሠራን ነው” ብሏል።

“ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ እና ትግርኛ በአጠቃላይ በአምስት ቋንቋዎች እየሠራን ነው። በደቡብ ክልል ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል ሁለት ቋንቋዎችን ለመጨመርም አስበናል” ሲልም ተናግሯል።

የአርሶ አደሩን የግብርና ምርታማነት ለመጨመር ኦሚሽቱ-ጆይ መሣሪያን በብዛት ለማምረት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ መሣሪያውን ለማምረት የሚረዱ ኮምፒዩተሮች እና ግብዓቶችን ከውጪ ማስመጣት ግን እንቅፋት እንደሆነባቸው ይገልጻል።

“መሣሪያውን ለማምረት የሚያገለግሉ ግብዓቶች በውጪ አገራት በቀላሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እነዚህን እቃዎች ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉ ያስረዳል።