ፑቲን የሰሞኑ የዩክሬን መልሶ ማጥቃት ‘ከዓላማችን አያሰናክለንም’ አሉ

ቪላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቪላድሚር ፑቲን
ታትሟል

ዩክሬን በቅርቡ የከፈተችው መልሶ ማጥቃት ዘመቻ ሩሲያ ከያዘችው ዓላማ እንደማያደናቅፋት ፑቲን ተናገሩ። 

ፑቲን ይህን የተናገሩት የዩክሬን መልሶ ማጥቃቱ ከተከፈተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ነው።

የዩክሬን ጦር ከሰሞኑ በከፈተው መጠነ ሰፊ እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ሰፋፊ ግዛቶችን ከሩሲያ ነጻ አውጥቷል።

በሰሜን ምሥራቅ ኻርኪቭ አውራጃ ብቻ በስድስት ቀናት ውስጥ 8 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር መልሰው መቆጣጠራቸውን ነው የዩክሬን የጦር አመራሮች የሚናገሩት።

ነገር ግን ፑቲን “እኛ ምንም የሚያጣድፈን ነገር የለም፤ በዩክሬን የዶንባስ አውራጃ የሚደረገው ጥቃት በተያዘለት ዕቅድ ይቀጥላል” ብለዋል።

ከዚህ አስተያየታቸው በላይ መነጋገሪያ የሆነው አገራቸው ሩሲያ በዚህ ጦርነት ሙሉ ኃይሏን እንዳላሰለፈች መናገራቸው ነው።

“በዶንባስ የጀመርነው ጥቃት እንዳሰብነው እየሄደ ነው፤ በፍጥነት ላይሄድ ይችላል። ቀስ በቀስ ግን መያዝ የምንሻውን ግዛት እየያዝን ነው” ብለዋል ፑቲን።

ፑቲን ይህን አስተያየት የሰጡት በኡዝቤክስታን የነበረን የመሪዎች ስብሰባ ተከትሎ ነው።

የኢንዱስትሪ ዞን ነው የሚባለው ዶንባስ አውራጃ የሩሲያ ወረራ በዋናነት ትኩረት ያደረገበት ቦታ ነው።

ፑቲን የሚሉት ትግላቸው የሩሲያ ተናጋሪዎች ላይ የሚደረግን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ማስቆም ነው።

ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ የዶንባስ አውራጃ የተወሰነው ክፍል በሩሲያ በሚደገፉ ተገንጣዮች ቁጥጥር ሥር ነው ያለው።

ሰሞኑን የዩክሬን ኃይሎች የተቆጣጠሩት የኻርኪቭ ክልል ግን በዶንባስ አውራጃ የሚገኝ አይደለም።

ፑቲን በዚህ አስተያየታቸው አሁን ዘመቻ ላይ ያለው እጅግ ውስን የሩሲያ ኃይል ነው ማለታቸው ምናልባት በቅርቡ የሠራዊት መጠናቸውን ሊጨምሩ ይሆን የሚል ስጋትን ጭሯል።

“ላስታውሳችሁ የምወደው አሁን እየተዋጋ ያለው ሠራዊታችን ካለን ከፊሉ እና የተመረጠው ብቻ ነው” ብለዋል።

ሩሲያ ዜጎቿን ወደ ግዳጅ ውትድርና አትልክም ቢባልም አሁን አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ግን ጥርጣሬን የሚያጭሩ ናቸው።

ሩሲያ አሁንም ቢሆን በዩክሬን ላይ ወረራ መክፈቷን አትቀበልም።

ምዕራባውያን ጦርነቱን ወረራ የሚሉት ቢሆንም ሩሲያ ግን “ልዩ የወታደራዊ ዘመቻ” በሚል ነው የምትጠራው።

በቅርብ ከክሬምሊን አካባቢ የተገኙ መረጃዎች፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ተጨማሪ ወታደሮችን እንድታሰማራ ጥያቄዎች እየቀረቡ ናቸው።

ለምሳሌ አንድ የሾለከ ተንቀሳቃሽ ምሥል በእስር ቤቶች የሚገኙ ፍርደኛ ታራሚዎች ጦሩን እንዲቀላቀሉ ሲበረታቱ የሚያሳይ ነው።

አንዳንድ ተንታኞች ሩሲያ የወታደሮቿ ቁጥር እየተመናመነባት እንደሆነ ይጠረጥራሉ።

 ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈቱ ወዲህ አገራቸው ሩሲያን ለቀው የሄዱት በጣት ለሚቆጠሩ ጊዜያት ነው።

በዚህ ሳምንት በኡዝቤክስታን፣ ሳማርካንድ ከተማ የሻንጋይ ኮርፖሬሽን ኦርጋናይዜሽን ጉባኤ ላይ ለመገናኘት ነበር የሄዱት።

ፑቲን በዚህ ጉባኤ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር መክረዋል።

በዚህ ጉባኤ ሕንድ እና ቻይና ለፑቲን ይህ የዩክሬን ጦርነት እንዳሳሰባቸው ገልጸውላቸዋል ተብሏል።