የእስራኤል እና ኢራን ግጭት ተባብሶ ቢቀጥል ምን ሊፈጠር ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስካሁን ባለው የእስራኤል እና ኢራን ግጭት በሁለቱ አገራት ብቻ የተገደበ ይመስላል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአንዳንድ አገራት ጥቃቶቹ እንዲቆሙ ጥሪዎች እየቀረቡ ናቸው።
ይሁን እንጂ እነዚህ ጥሪዎች ሰሚ ቢያጡስ? ግጭቱ ተባብሶ እና ተስፋፍቶ ቢቀጥልስ ምን ይፈጠራል የሚለውን እስቲ እንመልከት።
አሜሪካ ትሳተፋለች
ምንም እንኳ አሜሪካ በጥቃቱ አለመሳተፏን ብትክድም ኢራን አሜሪካ እና ሌሎች አጋሮቿ ጥቃቱን ደግፈዋል አልያም በታክቲክ አግዘዋል የሚል እምነት አላት።
በዚህም ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ የአሜሪካ ዒላማዎችን ልትመታ ትችላለች።
ለምሳሌ ያህል በኢራቅ ያሉ የአሜሪካ ልዩ ኃይል ካምፖች፣ በገልፍ ያሉ የጦር ሠፈሮች እና በቀጣናው የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎችን ልትደበድብ ትችላለች።
የኢራን ወኪል ኃይሎች ሐማስ እና ሒዝቦላ በጣም እየተዳከሙ ቢሆንም በኢራቅ የሚገኙ ደጋፊ ሚሊሻዎቻቸው ታጥቀው ይገኛሉ።
አሜሪካ እንደዚህ አይነት ጥቃቶች ሊፈፀሙ ይችላል የሚል ስጋት ስላላት የተወሰኑ ሠራተኞችን ከአካባቢው አስወጥታለች።
አሜሪካ ኢራን በዒላማዎቿ ላይ ጥቃት ብትሰነዝር አፀፋዊ እርምጃ እንደምትወስድም አስጠንቅቃለች።
በቴላቪቭ ወይም በሌላ ቦታ የአሜሪካ ዜጋ ቢገደልስ? ምን ይፈጠራል?
ዶናልድ ትራምፕ እርምጃ እንዲወስዱ ሊገደዱ ይችላሉ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ኢራንን ለማሸነፍ አሜሪካ እንድትረዳቸው ይፈልጋሉ በሚል ለረጅም ጊዜ ሲወነጀሉ ቆይተዋል።
የውትድርና ባለሙያዎች የኢራንን ኒውክለር ጣቢያ ድምጥማጥ የሚያጠፉ ፈንጅዎች በአሜሪካ እጅ ብቻ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
ትራምፕ ለታማኝ ደጋፊዎቻቸው በመካከለኛው ምሥራቅ "የዘላለም ጦርነት" ላለመጀመር ቃል ገብተዋል። ይሁን እንጂ በርካታ ሪፐብሊካኖች የእስራኤልን መንግሥትን እና በቴህራን ያለውን አገዛዝ ለመለወጥ የያዘችውን ሀሳብ ይደግፋሉ።
ነገር ግን አሜሪካ በግጭቱ ንቁ ተሳታፊ ብትሆን ረጅም፣ አስከፊ እና ተቀጣጣይ መዘዝ ይከተላል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ይሳተፋሉ
ኢራን ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግላቸውን የእስራኤል ወታደራዊ እና ሌሎች ዒላማዎችን መጉዳት ባትችል እንኳ ሚሳኤሎቿን በባሕረ ሰላጤው ወደሚገኙ አነስተኛ ዒላማዎች ልታነጣጥር ትችላለች።
በተለይም ደግሞ ባለፉት ዓመታት ባላንጣዎቿን ረድተዋል ወደምትላቸው አገራት ፊቷን ልታዞር ትችላለች።
በቀጣናው በርካታ የኃይል እና የመሰረተ ልማት ዒላማዎች ይገኛሉ።
እአአ በ2019 ኢራን የሳዑዲ አረቢያን የነዳጅ ማውጫ በመደብደብ ተነስሳ የነበረ ሲሆን እንዲሁም በ2022 ደግሞ ወኪሏ ሁቲ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ዒላማ መትተው ነበር።
ከዚህን ጊዜ ጀምሮ በኢራንን እና በአንዳንድ የቀጣናው አገራት መካከል እርቅ ወርዷል።
ነገር ግን በእነዚህ አገራት የአሜሪካ አየር ኃይል ጦር ሠፈር ይገኛል።
አንዳንዶቹ ደግሞ በድብቅም ቢሆን ባለፈው ዓመት ከኢራን ሚሳኤል እስራኤልን ተከላክለዋል።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ጥቃት ቢሰነዘርባቸው የአሜሪካ እና እስራኤል የጦር አውሮፕላኖች መጥተው እንዲከላከሉላቸው መጠየቃቸው አይቀሬ ነው።
እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር አቅም ማጥፋት ይሳናታል
የእስራኤል ጥቃት ቢከሽፍስ? የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች በጣም ጥልቅ፣ በጣም የተጠበቁ ቢሆኑስ?
የኢራን ኒውክሌር በሚስጥራዊ ማዕድኖች የተደበቀ እንደሆነ ይታመናል።
እስራኤል ጥቂት የኒውክሌር ተመራማሪዎችን ብትገድልም፤ምንም ያህል ቦምብም የኢራንን እውቀት እና አዋቂዎች ሊያጠፋ አይችልም።
የእስራኤል ጥቃት የኢራን መሪዎች ቀጣይ ጥቃቶችን ለመመከት መውጫው የኒውክሌርን አቅም በፍጥነት መጨመር እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ቢደርሱስ?
አዳዲሶቹ የጦር አለቆች ከሞቱት የቀድሞ መሪዎች በበለጠ ጠንካሮች እና ለጥንቃቄ ግድ ባይሰጣቸውስ?
ይህ ቢያንስ እስራኤል ተጨማሪ ጥቃቶችን እንድትፈፅም ያስገድዳታል። ይህም ቀጣናውን ቀጣይነት ወዳለው የግጭት አውድማነት ያስገባዋል።
ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ቀውስ
የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ነው።
ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን ለመዝጋት ብትሞክር እና የነዳጅ እንቅስቃሴ የበለጠ ቢገደብ ምን ይፈጠራል?
በሌላኛው የአረቢያ ባሕር ገብ መሬት በየመን የሚገኙ ሁቲዎች ኃይላቸውን አሰባስበው በቀይ ባሕር እቃ የጫኑ መርከቦችን ቢያጠቁስ?
ሁቲዎች የኢራን ቀሪ ወኪሎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ያልተጠበቁ እና ከፍተኛ ጥቃቶችን በማድረስ ይታወቃሉ።
በመላው ዓለም በርካታ አገራት በኑሮ ውድነት ቀውስ እየተናጡ ነው። የነዳጅ ላይ ዋጋ መጨመር በትራምፕ ታሪፍ ምክንያት አስቀድሞ ጫና በደረሰበት የዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ የዋጋ ግሽበትን ከፍ ያደርጋል።
የነዳጅ ዋጋ ከጨመረ ሊጠቀሙ የሚችሉ አንድ ሰው መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም።
ከእነዚህም መካከል አንዱ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው።
የነዳጅ ዋጋ ከጨመረ በዩክሬን ለጀመሩት ጦርነት የሚሆን ቢሊዮን ዶላሮች ወደ ካዝናቸው ይገባል።
የኢራን አገዛዝ ወድቆ መንበሩ ባዶ ይሆናል
እስራኤል የኢራንን እስላማዊ አብዮታዊ መንግሥት ለማፍረስ ለዘመናት የያዘችው ውጥን ቢሰምር ምን ይፈጠራል?
ኔታኒያሁ የመጀመሪያ ዓላማቸው የኢራንን ኒውክሌር አቅም ማውደም እንደሆነ ይናገራሉ።
ነገር ግን ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ትልቁ ዓላማቸው የአገዛዝ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቃቱን የፈፀሙት "አረመኔ እና ጨቋኝ" ካሉት አገዛዝ "ኩሩው የኢራን ሕዝብ ነፃነትህን የምትቀናጀበትን መንገድ እየጠረግን ነው" ብለዋል።
የኢራንን መንግሥት መጣል ለአንዳንድ ክልሎች በተለይም ለእስራኤላዊያን ሳቢ ነው።
ነገር ግን ምን ውጥንቅጥ ጥሎ ያልፋል? ምን ያልተጠበቁ ውጤቶች ሊኖሩት ይችላሉ? በኢራን የእርስ በእርስ ግጭት ምን ሊመስል ይችላል?
በኢራቅ እና ሊቢያ ጠንካራ የተማከሉ መንግሥታት ሲወድቁ ምን እንደተከሰተ አብዛኞቻንን እናስታውሳለን።
ስለዚህ አብዛኛው እጣ ፈንታው በሚቀጥሉት ቀናት ግጭቱ በሚሄድበት ርቀት ይወሰናል።
ኢራን እንዴት እና ምን ያህል አፀፋዊ እርምጃ ትወስዳለች? አሜሪካ ለእስራኤል ለመድረስ ምን ያግዳታል?
በእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ምላሽ ሁሉም ይወሰናል።















