አሜሪካ በየመን ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ሁቲዎች የአሜሪካ የጦር መርከቦችን አጠቁ

ተዋጊ ጄት ከአሜሪካ መርከብ ላይ ሲነሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የየመን ሁቲ አማጺያን በሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ ያደረሱት በርካታ የሚሳኤል ጥቃቶች መክሸፉን ፔንታጎን አስታወቀ።

ሰኞ ዕለት ቢያንስ ስምንት ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ አምስት ጸረ-መርከቦች ባለስቲክ ሚሳዔሎች እና ሦስት ጸረ-መርከብ ክሩዝ ሚሳዔሎች ዩኤስኤስ ስቶክዴል እና ዩኤስኤስ ስፕሩንስ የተባሉት የጦር መርከቦችን ዒላማ አድርገዋል።

የፔንታጎን ፕሬስ ሴክሬተሪ የአየር ሃይል ሜጀር ጄኔራል ፓት ራይደር ማክሰኞ፣ ህዳር 3/ 2017 ዓ.ም ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጥቃቶቹ እንዲከሽፉ በመደረጋቸው መርከቦቹ “ካለመጎዳታቸውም በላይ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።”

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በየመን የሚገኙ የሁቲ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ማዕከላት ላይ ያደረሰውን ተከታታይ የአየር ድብደባ ተከትሎ የተሰነዘረ ጥቃት ነው።

ጥቃቱ የተፈጸመው በኢራን የሚደገፈው አማጺ ቡድን በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ መካከል ባለው የባብኤል መንደብ ሰርጥ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ነው።

በየመኑ ሁቲ የሚተዳደረው አልማሲራህ ቲቪ የተሰኘው የቴሌቭዥን ጣብያ በበኩሉ ተከታታይ የአየር ድብደባው በሁለቱ የአሜሪካ የጦር መርከቦች እና በአረብ ባሕር ላይ በሚገኝ ሦስተኛ መርከብ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልጿል።

የቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ አል ሳሬአ በኤክስ ላይ በሰጠው መግለጫ አማጽያኑ ዩኤስኤስኤስ አብርሀም ሊንከን የተሰኘውን አውሮፕላን መጫኛ መርከብ በበርካታ የክሩዝ ሚሳዔሎች “በተሳካ ሁኔታ” መምታቱን ገልጿል።

ራይደር በበኩላቸው በአብርሃም ሊንከን መርከብ ላይ "ምንም አይነት ጥቃት እንደተፈጸመ አላውቅም" ብለዋል።

"ሁቲዎች የሚያደርጉት ህገወጥ እና ግድየለሽ ጥቃት የመልስ ምት እንደሚኖረው ግልጽ ማድረጉን እንቀጥላለን" ሲሉ አክለዋል።

በሊባኖስ የሚገኘው ሄዝቦላህን እና በጋዛ የሚንቀሳቀሰውን ሐማስ ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ በኢራን ከሚደገፉ የታጠቁ ቡድኖች ሁቲ አንደኛው ነው።

ቡድኑ ከአውሮፓውያኑ ህዳር 2023 ጀምሮ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦችን በተደጋጋሚ ዒላማ አድርጓል።

ሁለት መርከቦችን ሲያሰምጡ አንድ ሦስተኛውን መርከብ በቁጥጥር ስር አውለዋል። በርካታ መርከበኞችንም ገድለዋል።

በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በሚደረገው ጦርነት ፍልስጤማውያንን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ይገልጻሉ።

ከእስራኤል፣ አሜሪካ ወይም ዩናይትድ ኪንግደም ጋር የተገናኙ መርከቦች ላይ ብቻ እያነጣጠሩ መሆኑን ቢናገሩም ይህ ትክክል አለመሆኑ ተደጋግሞ ታይቷል።

ከወራት በፊት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች 12 አገራት የቀይ ባህር የመርከብ መስመሮችን ከሁቲዎች ጥቃት ለመከላከል 'ኦፕሬሽን ፕሮስፐሪቲ ጋርዲያን' የተባለ ዘመቻ ጀምረዋል።

በጥቅምት ወር የአሜሪካ ጦር በየመን በሚገኙ 15 የሁቲ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ከመግለጹም በላይ በዋና ከተማዋ ሰንዓ በርካታ ፍንዳታዎች እንደነበሩ ተዘግቧል።

ጥቃቱ የሁቲዎች መርከቦች ላይ የሚያደርጉትን ጥቃት ለመቀነስ ያለመ መሆኑን ቀደም ሲል ተናግሯል።