ትራምፕ የአሜሪካ ከተሞች ወታደራዊ ማሰልጠኛ መሆን አለባቸው ሲሉ ለጄነራሎቻቸው ተናገሩ

የአሜሪካ ጦር ጄነራሎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ከተሞችን የወታደራዊ "ማሰልጠኛ ማዕከል" እንዲሆኑ እንደሚፈልጉ ተናገሩ።

ከዓለም ለተሰባሰቡ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአገሪቱ ጦር መሪዎች ባልተለመደ ሁኔታ "ተቃውሞ እና አለመረጋጋቶች" እንደ "ከውስጥ ያለ ጠላት" ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም "እናንተ ከተሳተፋችሁ ከቁጥጥር ውጭ አይወጣም" ብለዋል።

ትራምፕ በቅርቡ ወንጀልን ለመቀነስ እና ሰነድ አልባ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚል በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ፓርትላንድ፣ ኦሪጎን የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ማሰማራታቸው ይታወሳል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄጌስዝ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በፔንታጎን አካታችነት፣ ማኅበራዊ ፍትህ እና ብዝኃነት ፕሮግራሞች ላይ የተቀመጡት ከተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት፣ ጾታ፣ ዘረኝነት ጋር የሚገናኙ ባህሎች ማብቃታቸውን እና አዲስ "የወንዶች አቻ" አካላዊ ብቃት መስፈርት ለወታደራዊ ባለሥልጣናት ይፋ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዲሞክራቶች የሚመሩት ከተሞች ሳን ፍራንሲስኮ፣ ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ ላይ ትችታቸውን ዳግም ያቀረቡ ሲሆን ሕግ ለማስከበር የአገሪቱን ጦር መጠቀማቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

"ደህንነት የራቃቸው ስፍራዎች ናቸው፤ እንዲሁም አንድ በአንድ እናስተካክላቸዋለን" ካሉ በኋላ "እዚህ ላላችሁ ለአንዳንዶቻችሁ ዋነኛ ተግባር ይሆናል" ብለዋል።

"ከውስጥ ያለ ጦርነት ነው። ለብሔራዊ ደህንነት ድንበሮቻችንን በአግባቡ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሰዎች እንዲገቡ መፍቀድ የለብንም" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢሊኖይስ ገዢ ጄቢ ፕሪትዝከር ትራምፕ ወታደሮችን እና የስደተኛ እና ጉሙሩክ ኃይሎችን በመጠቀም የአሜሪካ ከተሞችን "ይወርራሉ እንዲሁም ያውካሉ" ሲሉ ተችተዋቸዋል።

"ወታደሮቻችን እና ሕዝባችን እንደ ትንሽ አምባገነን ከሚሰራው የተሻለ ይገባቸዋል" ሲሉ በኤክስ ልጥፋቸው ላይ ተናግረዋል።

በበርካታ የዓለም ክፍል የሚገኙት እና በቨርጂኒያ የተሰባሰቡት የአሜሪካ ጦር ጄነራሎች እና አድሚራሎች ሁለቱ ባለሥልጣናት ሲናገሩ በዝምታ ማዳመጥ መርጠዋል።

ስብሰባው የተጀመረው በሚኒስትሩ ንግግር ሲሆን የአሜሪካ ጦር ተዋጊዎች በአካላዊ ብቃት ፈተና "ከፍተኛ የወንድ መስፈርት" ማሟላት አለባቸው ብለዋል።

ሄግሴዝ ይህ ውሳኔ በመወሰኑ የተወሰኑ ሴቶችን ከጦሩ እንዲገለሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

"መስፈርቶች ወጥ መሆን አለባቸው፤ ከጾታ ነጻ የሆኑ እና ከፍተኛ" ሲሉ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል።

ሄግሴዝ በፔንታጎን እንዲመጣ የሚፈልጉትን የባህል ለውጥ እና ታላቅ "የተዋጊነት መንፈስ" ዘርዝረዋል።

ይህንን ሃሳባቸውን ከእርሳቸው በመቀጠል የተናገሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም አስተጋብተውታል።

ንግግራቸው በአሜሪካ ጦር ውስጥ ያለወን ባህል፣ ስልጠና፣ አመራር እና "ለአስርት ዓመታት የቆየውን መበስበስ መጠገን" የሚል ላይ ያተኮረ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም አካታችነት፣ ልዩነት እንዲሁም እኩልነት ላይ የሚያተኩረው የጦሩ ፕሮግራሞችንም በሚመለከት ንግግር አድርገዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ሄግሴዝ ስለ ጀመሩት ሪፎርም ሲናገሩ "የአካል ብቃት፣ ችሎታ እና ጠባይ" ተብለው የተዘራዘሩት "የማንንም ስሜት ለመከላከል" አይደለም ብለዋል።

"አገራቸንን ለመከላከል ነው፤ የአሜሪካን ነጻነት በምንከላከልብት ወቅት ሁሌም ትክክል ላንሆን እንችችላለን" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ መከላከያ ሚኒስቴር የሚለውን ወደ ጦር ሚኒስቴር በመቀየራቸው የፔንታጎን አዲሱ ስም በአምባገነኖች ሳይቀር "በጣም የሚታወቅ ነው" ብለዋል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት እምብዛም ሲናገሩ አልተደመጡም፤ ትራምፕ ለንግግር መድረክ ላይ ከወጡ በኋላ በቀልድ መልክ "ከዚህ በፊት እነዲህ ፀጥ ያለ ክፍል ውስጥ ተገኝቼ አላውቅም' ብለዋል።

"በጋራ ሁነን ያለንን የተዋጊነት መንፈስ እናነቃቃዋለን። ያ መንፈስ ነው ያሸነፈው እና አገራችንን የገነባው።"

ትራምፕ ለወታደራዊ አዛዦቹ በፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ያከናወኗቸውን በርካታ ተግባራት ጠቅሰው ሰባት ጦርነቶችን ማስቆማቸውን እና ሐማስ የቀረበለትን ምክረ ሃሳብ ከተቀበለ ስምንተኛውን ጦርነት አንደሚያስቆሙ ተናግረዋል።