ዛሬ በሚጠናቀቅ የዝውውር መስኮት የተሰሙ ጭምጭምታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጥር ወር የአውሮፓ ሊጎች የዝውውር መስኮት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ.ም. በእንግሊዝ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ሌሊት ላይ ያበቃል።
የዝውውር መስኮቱ ከመጠናቀቁ በፊት የእንግሊዝ ክለቦች በአዲስ ተጫዋቾች ራሳቸውን ለማጠናከር በመጨረሻ ሰዓታት ትንቅንቅ እያደረጉ ይገኛሉ።
ቼልሲ አርጀንቲናዊውን አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝን ከቤኔፊካ ለማስፈርም የሚያደርገውን ጥረት ዳግም መጀመሩን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል።
እንደ ሜትሮ ዘገባ ከሆነ ቼልሲ ተጫዋቹን ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ ለማዘዋወር ለቤኔፊካ 100 ሚሊዮን ዩሮ እከፍላለሁ ብሏል። እንደ ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ከሆነ ደግሞ ቼልሲ እንደሁኔታው ተጫዋቹን ለማዘዋወር እስከ 120 ሚሊዮን ዩሮ ሊከፍል ይችላል።
ቼልሲ ይህን ዝውውር የሚያሳካ ከሆነ በአሜሪካዊው ባለሃብት ሥር መተዳደር ከጀመረ በኋላ ለተጫዋቾች ዝውውር ያወጣው የገንዘብ መጠን 500 ሚሊዮን ፓዎንድ የቀረበ ይሆናል።
ብራይተን ደግሞ አርሰናል ካይሴዶን ለመውሰድ ያቀረበውን 65 ሚሊዮን ፓዎንድ እና የ5 ሚሊዮን ፓዎንድ ጭማሪን ውድቅ አድርጓል።
ብራይተን የአርሰናልን የግዢ ዋጋ ውድቅ ሲያደርግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አትሌቲክ ዘግቧል። አማካዩ ቶማስ ፓርቴን ተክቶ መጫወት ይችላል የተባለውን ኢኳዶራዊውን ሞይሴስ ካይሴዶ ለመውሰድ አርሰናል ሦስተኛ ጥረት ሊያደርግ እንደሚችል ይገመታል።
ካይሴዶ ወደ አርሰናል የመዘዋወር ጽኑ ፍላጎት ያለው ሲሆን፤ ይህ ዝውውር የሚሳካ ከሆነ በአርሰናል ታሪክ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ተጫዋች ሊሆን ይችላል።
ኖቲንግሃም ፎረስት ደግሞ የኒውካስሉን ጆንጆ ሼልቪን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል። እንደ ቴሌግራፍ ከሆነ በኒውካስል በመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድልን ተነጥቆ የቆየው የ30 ዓመቱ ሼልቪ፤ ፎረስት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካደገ በኋላ የክለቡ 25ኛ ፈራሚ ይሆናል።
ቶተነሃም ደግሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና የቦሪሺያ ዶርትሙንድ አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም ታናሽ ወንድም የሆነውን የ17 ዓመቱን ጆብ ቤሊንግሃም ከበርሚንግሃም ሲቲ ለማስፈረም ጥረት እያደረገ መሆኑን ፉትቦል ኢንሳይደር ዘግቧል።
አሜሪካዊው አማካይ ዌሰተን ማኬኒ ወደ ሊድስ ተጉዞ ወደ ኤላንድ ሮድ የሚያደርገውን ዝውውር ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የጁቬንትስ አማካይ በበርካታ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ሲፈለግ የነበረ ቢሆንም የአገሩ ልጆች የሆኑት ታይለር አደምስ እና ብራንደን አረሰን የሚጫወቱበትን ሊድስ ዩናይትድን መርጧል። ማኬኒ ወደ ሊድስ የሚያመራው በውሰት ቢሆንም ወደ ፊት ግን ዝውውሩ ቋሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ኖቲንግሃም ፎረስት የፓሪስ ሴንት-ጀርሜን ግብ ጠባቂ ከይለር ናቫስን ለማስፈረም መቃረቡን የዘገበው ፉትቦል ኢንሳይደር ነው።
ክርስታል ፓላስ ደግሞ ለጀርመኑ ክለብ ስቱትጋርት የሚጫወተውን ናኦኢሩ አሕማዳ ለማስፈርም ከጫፍ መድረሱን ፋብሪዚዮ ሮማኖ ዘግቧል። ፓላስ ለ20 ዓመቱ ፈረንሳዊ አማካይ 12 ሚሊዮን ዩሮ ይከፍላል።












