ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤሎን መስክ ከትዊተር ጋር ካለው የፍርድ ሂደት በፊት ጃክ ዶርሲን ፍርድ ቤት ሊያስቀርበው ነው
ኤሎን መስክ ከትዊተር ጋር ካለው ፍርድ ሂደት በፊት የኩባንያው መስራች ጃክ ዶርሲ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ለማድረግ ህጋዊ እርምጃ ጀምሯል።
ኩባንያው በሐሰተኛ አካውንቶች ቁጥር ላይ በቂ መረጃ አለመስጠቱን በመግለጽ መስክ ትዊተርን ለመግዛት ያቀረበውን 44 ቢሊዮን ዶላር ውል ለማቋረጥ ፈልጓል።
ማህበራዊ ድር አምባው በበኩሉ በውሉ መሰረት እንዲገዛ ለማስገደድ መስክን እየከሰሰው ነው።
ሁለቱም ወገኖች አስቀድመው ከፍርድ ቤት ውጭ ጉዳዩን ለመፍታት ካልወሰኑ በስተቀር ጉዳዩ በዴላዌር፣ አሜሪካ በመጪው ጥቅምት ይታያል።
የዓለማችን ቁጥር አንድ የሆነው መስክ በተስማማው መሰረት በ 54.20 ዶላር እያንዳንዱን አክሲዮን ገዝቶ እንዲያጠናቅቅ ፍርድ ቤቱ እንደሚወስን ትዊተር ተስፋ አድርጓል።
የመስክ ጠበቆች ከቀድሞው የትዊተር አለቃ ዶርሲ የማህበራዊ ሚዲያው የሐሰተኛ አካውንቶችን ቁጥር በተመለከተ ለቴስላው አለቃ የሚደገፍ መረጃ እንደሚያገኙ ተማምነዋል።
በህጉ መሰረት ዶርሲ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ወይንም ህጋዊ ማስረጃዎችን እንዲያቀርብ ይደረጋል።
በሐምሌ ወር ነው ቢሊየነሩ ትዊተርን ለመግዛት ካደረገው ስምምነት ለመራቅ ማቀዱን የተናገረው። በዘህም ኩባንያው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንዲወስደው አስገድዶታል።
መስክ ኩባንያውን ስለ ሀሰተኛ አካውንቶች መረጃ አልሰጥም ብሏል ይላል። ትዊተር ግን ይህ ላለመግዛት የተሰጠ ሰበብ ነው ሲል ያስተባብላል።
ትዊተርም ከመስክ ጋር በተደረገው ስምምነት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያቀዱ ሰዎች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጠርቷል።
ዶርሲ ባለፈው ዓመት ነበር ከትዊተር ዋና ስራ አስፈፃሚነት የለቀቀው። “ኤሎን የማምነው ብቸኛ መፍትሄ ነው። ሊያስፋፋ የሚፈልገውን የንቃተ ህሊና ብርሃን እደግፋለሁ" ሲልም መስክን በመደገፍ በትዊተር ገጹ ላይ መልዕክቱን አስፍሯል።
ባለፈው ወር አንድ ትዊተር መስክ ላይ ያቀረበው ክስ በጥቅምት ወር ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተወስኗል።
መስክ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ከቴስላ 6.88 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው 7.92 ሚሊዮን አክሲዮኖችን ሸጧል። ትዊተርን ለመግዛት ከተገደደ ገንዘቡን እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ነው የአክሲዮን ሽያጩን ያከናወነው።
መስክ አስገመገምኳቸው ካላቸው ከሚታዩ የትዊተር አካውንቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ የሐሰተኛ ናቸው በማለት ድርጅቱን ይከሳል። ይንን አሃዝ በመጠቀምም ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆኑት ዕለታዊ ተጠቃሚዎች ኮምፒውተር ሠራሽ እንደሆኑ ገምቷል።
ከትዊተር ጋር ባለው የፍርድ ቤት ክርክር ዙሪያ የህግ ቡድኑ ኮምፒውተር ሰራሽ ተጠቃሚ ሲል ያቀረባቸው ሰነዶች በተመራማሪዎች ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።
ትዊተር በየቀኑ ከአምስት በመቶ ያነሱ ንቁ ተጠቃሚዎቹ ኮምፒውተር ሰራሽ እንደሆኑ ይገምታል።