የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ በግብር ማጭበርበር ወንጀሎች ሊከሰስ ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ የሆነውን ሀንተር ባይደንን በግብር ማጭበርበር ወንጀሎች እና መሣሪያ ለመግዛት የሐሰት ሰነድ በማዘጋጀት ለመክሰስ በቂ ማስረጃ ማሰባሰቡን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘገበ።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በአገሪቱ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ምርመራ እየተካሄደበት ነው።
የወንጀል ክስ ይቅረብበት የሚለው ውሳኔም በዴላዌር ግዛት የሚገኘው የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ እጅ ላይ ወድቋል።
የሀንተር ጠበቃ እንሚለው እስካሁን የፌደራል ምርመራ መሥሪያ ቤቱ ወኪሎች ከሀንተር ጋር አልተገናኙም።
ሀንተር በተደጋጋሚ ሕግ አለመጣሱን የተናገረ ሲሆን፣ የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
የ52 ዓመቱ ሀንተር ባይደን በሙያው የሕግ ባለሙያ ሲሆን ቻይና እና ዩክሬንን ጨምሮ ከአገር ውጭ ሰርቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2014 የኮኬይን ዕጽ መጠቀሙ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ በአሜሪካ ባሕር ኃይል ክስ ቀርቦበት ነበር።
እንደ ዋሽንግተን ፖስት ከሆነ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ወኪሎች ከ2018 ጀምሮ በሀንተር ላይ ምርመራ የጀመሩ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ላይ በባሕር ማዶ ባለው ቢዝነስ እና የማማከር ሥራው ጋር በተያያዘ ያሉ የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገዋል።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ሀንተር ገቢውን በትክክል ማሳውቅ አለማሳወቁን እንዲሁም፣ በ2018 የጦር መሣሪያ ለመግዛት የሐሰት ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ትኩረት አድርገው ምርመራ እየተካሄደበት ነው።
ባለፈው ዓመት በታተመ መጽሐፍ ላይ በወቅቱ አደገኛ የሆነውን የኮኬይን ዕጽ ተጠቃሚ እንደነበር አምኗል።
ይሁን እንጂ በፌደራል ወኪሎች የማሪዋና ወይም ማንኛውም አደንዛዥ ዕጽ፣ አነቃቂ፣ ናርኮቲክ ዕጽ ወይም ማንኛውንም መድኃኒት በሕገ ወጥ መንገድ ተጠቃሚ አሊያም ሱሰኛ እንደሆነ ሲጠየቅ ምላሹ "አይደለሁም" የሚል እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
የጦር መሣሪያ ለመግዛት ሐሰተኛ ሰነድ የማዘጋጀት ወንጀል ክስ ያልተለመደ ነመሆኑ በዚህ ዙሪያ በየዓመቱ የሚቀርቡ ክሶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው።
ለሲቢኤስ በተላከ መግለጫ የፕሬዝዳንቱ ልጅ ጠበቃ፣ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ስለ ምርመራው መረጃ ያወጡ አካላትን “በትጋት እንደሚመረምር እና ውሳኔ ያሳልፋል” ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ጠበቃ ክሪስ ክላርክ በመግለጫቸው “ሕግ እንደሚጠይቀው በዚህ ጉዳይ ዐቃቤያነ ሕግ በፌደራል ወኪሎች የቀረበላቸውን ማስረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በመከላከያ ያሉ የዐይን ምስክሮችን ጨምሮ ሁሉንም ሌሎች የዐይን ምስክሮች በትጋት እና ትኩረት ሰጥተው እንደሚመለከቱት እናምናለን” ብለዋል።
“ይህ የዐቃቤያነ ሕግ ሥራ ነው። በግፊት፣ በችኮላ አሊያም በሚሰነዘርባቸውን ትችት ሳቢያ ሊከናወን አይገባም” ብለዋል ጠበቃው።
ክላርክ ጨምረውም ከማንኛውም የፌደራል መርማሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳልነበራቸውም ተናግረዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩን በዘገበው ዋሽንግተን ፖስት የተጠቀሱ ከወኪሎች የሚመጡ መረጃዎችም “ገለልተኛ ያልሆኑ፣ ወገንተኝነት ያላቸው እና ትክክለኛ ያልሆኑ ነበሩ” ብለዋል።
ሀንተር ባይደን ከአገር ውጭ ያለው የቢዝነስ ስምምነቶች የሚያመለክቱት ከሙስና ጋር የተገናኘ ነው በሚልም በወግ አጥባቂዎች ለረዥም ጊዜ ኢላማ ሆኖ ቆይቷል።
ሪፐብሊካኖች በሚቀጥለው ወር በሚደረገው የኮንግረስ ምርጫ አብላጫ መቀመጫ ካሸነፉም በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ምርመራ እንደሚያካሂዱበት ቃል ገብተዋል።
የባይደን ልጅ ከባድ ሕይወት እንደነበረው እና ቀደም ብሎ ከፍተኛ የሆነ የዕጽ ሱስ እንደነበረበት ያመነ ቢሆንም በሌላ ሕገ ወጥ ድርጊት ተሳትፏል የሚለውን ግን ፕሬዝዳንት ባይደንም ሆኑ ልጃቸው አልተቀበሉትም።
እየተካሄደበት ስላለው ምርመራ ታኅሣሥ 2020 ላይ እንዳወቀም የተናገረው ሀንተር፣ በጊዜው በሰጠው መግለጫ “ሙያዊ የሆነ እና የእነዚህን ጉዳዮች ዓላማ በተጨባጭ በመመልከት ብቻ፣ ሥራዎቼን በሕጋዊ መንገድና በትክክል ከባለሙያ የግብር አማካሪዎች ጋር እንደማከናውን እንደሚያስረዱ እምነት አለኝ” ብሏል።
ሚያዝያ ወር ላይ የጆ ባይደን ጽ/ቤት ኃላፊ ሮን ክሌን፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ልጃቸው ሕግ እንዳልጣሰ እንደሚተማመኑ ተናግረው፣ ጉዳዩ ግን ለፍትሕ መሥሪያ ቤቱ የሚተውና ዋይት ሐውስ ጣልቃ እንማይገባ ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2018 ሀንተር ባይደን ምርመራ የተደረገበት በወቅቱ የነበረችው ፍቅረኛው የእርሱ የነበረውን ሽጉጥ ትምህርት ቤት አቅራቢያ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ከወረወረች በኋላ እንደነበር የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በዚያው ወር መጀመሪያ የደኅንነት ወኪሎች የጦር መሣሪያውን የገዛበትን ዴላዌር መደብር በመጎብኘትና የጀርባ ታሪኩን የሚያሳዩ መረጃዎች በመጠየቅ ጣልቃ መግባታቸውን ፖሊቲኮ ዘግቧል።
የመሣሪያ መሸጫ መደብሩ ሰነዶቹን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልነበር ድረ ገጹ የዘገበ ሲሆን ክስም አልተመሰረተበትም።












