ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ካንሰር ያለበት ልጅን ጨምሮ ሦስት አሜሪካውያን ልጆች ወደ ሆንዱራስ ተወሰዱ
አሜሪካውያን የሆኑ ሦስት ልጆች ወደ ሆንዱራስ መወሰዳቸው ተገለጸ።
የመብት ተሟጋቾችና የቤተሰቡ ጠበቆች እንደገለጹት አንደኛው ልጅ የካንሰር ታማሚ ሲሆን፣ ልጆቹ ከእናታቸው ጋር ነው ወደ ሆንዱራስ የተወሰዱት።
የአራት ዓመቱ ልጅ አራተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ካንሰር ታማሚ ሲሆን ያለ መድኃኒት ነው ወደ ሆንዱራስ የተወሰደው።
ዶናልድ ትራምፕ በስደተኞች ጉዳይ የሾሟቸው ቶም ሆማን እንዳሉት፣ እናትየዋ ወደ ሆንዱራስ ስትወሰድ አሜሪካዊ ልጆቿን ለመውሰድ መርጣለች።
"አሜሪካውያን ልጆች አሏት ማለት የአሜሪካ ሕግ አይመለከታትም ማለት አይደለም" ብለዋል።
እናትየዋ አሜሪካ እየኖረች የነበረው በሕገ ወጥ መንገድ ነበርም ብለዋል።
ትራምፕ በቀድሞው የሥልጣን ዘመናቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችን ከወላጆቻቸው በመለያየታቸው ትችት ሲሰነዘርባቸው ነበር።
የኒው ኦርላንድስ የስደተኞች ጉዳይ ወደ ሆንዱራስ የላከው ሁለት እናቶችን ሲሆን ልጆቹ የሁለት፣ አራት እና ሰባት ዓመት ናቸው።
አንደኛዋ እናት ነፍሰ ጡር ስትሆን አሜሪካ ለዓመታት ኖራለች።
የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም "ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ በጣም አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ነው ከአሜሪካ እንዲወጡ የተደረገው" ብሏል።
ዶናልድ ትራምፕ በስደተኞች ጉዳይ የሾሟቸው ቶም ሆማን እንዳሉት፣ ቤተሰቦችን ከመነጣጠል አንድ ላይ ከአገር ማስወጣት ይሻላል።
የካንሰር ታማሚው ልጅ መድኃኒትም ይሁን ሐኪም የሚያገኝበት መንገድ አይኖርም።
"ልጆቹ አሜሪካውያን ስለሆኑ ከአሜሪካ ልናስወጣቸው አንችልም።የወጡት በኛ ውሳኔ ሳይሆን በወላጆቻቸው ነው" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የፌደራል መንግሥት ዳኛ ሁለት ዓመቷ የሆነች አሜሪካዊ ያለ ሕጋዊ ሂደት ከአገር እንድትወጣ መደረጉን ተናግረዋል።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክረተሪ ካሮላይን ሌቬት እንዳሉት፣ትራምፕ ከስደተኞች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሁለት ውሳኔዎች ያሳልፋሉ።
አንደኛው ውሳኔ ለስደተኞች ከለላ የሚሰጡ ቦታዎችን ዝርዝር በይፋ እንዲወጡ የሚያስገድድ ነው።
እነዚህ ቦታዎች ለስደተኞች ከፌደራል መንግሥት ከለላ የሚሰጡ ናቸው።
በኮሎራዶ በሚገኝ የምሽት ክበብ ውስጥ ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ 100 ሰንድ አልባ ስደተኞችንና መሣሪያ እንዲሁም አደንዛዥ ዕፅ መያዙን ገልጸዋል።
የአገሪቱ የአደንዛዥ ዕፅ ተቆጣጣሪ አካል 114 ስደተኞች ወደ አገራቸው ሊመለሱ እንደሆነ ገልጿል።
ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።