ጄኔፈር ሎፔዝ በአራተኛ ፍቺዋ ከቤን አፍሌክ ጋር ልትለያይ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እውቋ ደምጻዊት እና ተዋናይት ጄኔፈር ሎፔዝ ከሁለት ዓመታት የትዳር ቆይታ በኋላ ከሆሊዉድ ተዋናዩ ቤን አፍሌክ ጋር ለመፋታት ለፍርድ ቤት ማመልከቻ አስገባች።
በመጽሔቶች ‘ቤኒፈር’ በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ጥንዶች፤ በሥራ አማካኝነት ከተገናኙ በኋላ ድል ባለ ሠርግ የተሞሸሩት ከሁለት ዓመታት በፊት ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ነበር።
ጄሎ እና ቤን አፍሌክ ከሁለት ዓመት በፊት ይጋቡ እንጂ ትውውቃቸው የጀመረው በ1990ዎቹ አጋማሽ ነበር።
ጥንዶቹ እ.አ.አ በ2003 የወጣውን ‘ጊግሊ’ የተሰኘ ፊልም ሲቀርጹ ተቀራርበው በፍቅር ወድቀው ነበር። ከዚያም ለመጋባት ቢወስኑም ትዳር ከመመስረታቸው በፊት ዓመቱ ተለያይተዋል።
ይሁን እንጂ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ፍቅራቸውን አድሰው ተጋብተዋል።
ጄኔፈር ከሁለት ዓመታት በፊት በሎስ አንጀለስ ከቤን አፍሌክ ጋር በትዳር መጣመሯን ይፋ ስታደርግ “ፍቅር ውብ ነገር ነው። ፍቅር ሩህሩህ ነው። ፍቅር ታጋሽም ነው። የ20 ዓመታት ታጋሽ” ብላ ነበር።
የፍርድ ቤት ሠነዶች እንደሚያሳዩት ሁለቱ ግለሰቦች ገቢያቸውን፣ ወጪያቸውን፣ ያላቸውን ንብረት እና ዕዳ የሚያትት የግል የፋይናንስ መረጃ ለፍርድ ቤቱ ይፋ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ጥንዶች የሚጠበቅባቸውን የፋይናንስ መረጃ ይፋ የማያደርጉ ከሆነ በፍርድ ቤት የንብረት እግድ ይጣልባቸዋል።
ጄሎ እና ቤን አፍሌክ ሊለያዩ እንደሆነ የሚጠቁም ዘገባዎች ከዚህ ቀደም ሲወጡ ቆይተዋል።
ጥንዶቹ በቅንጡዋ የካሊፎርኒያ ከተማ በቨርሊ ሂልስ የሚገኘውን ግዙፉን መኖሪያ ቤታቸውን በ65 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጠ ማስታወቂያ ማስነገራቸው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የጋብቻ ቀለበታቸውን ሳያደርጉ፣ ተነጣጥለው በተደጋጋሚ በአደባባይ ሲታዩ ቆይተዋል።
ጄሎ በሚሰኘው ዝነኛ የመድረክ ስሟ የምትታወቀው ጄኔፈር ሎፔዝ፤ ከቤን አፍሌክ ጋር የምትለያይ ከሆነ አራተኛ የትዳር ፍቺዋ ይሆናል።
የ55 ዓመቷ ጄሎ፤ ከእ.አ.አ 1997 እስከ 2024 ድረስ ከአራት ስዎች ጋር በትዳር የተጣመረች ሲሆን ለ10 ዓመታት በትዳር አብራው ከቆየችው ከድምጻዊው ማርክ አንቶኒ መንታ ልጆችን ወልዳለች።
ጄሎ ከአራቱ የትዳር አጋሮቿ በተጨማሪ የኒው ዮርክ ያንኪስ ቤዝ ቦል ተጫዋች የነበረው አሌክስ ሮድሪጌዝ እጮኛ ነበረች።
ሁለት ጊዜ የኦስካር አሸናፊው የ52 ዓመቱ ቤን አፍሌክ ደግሞ ጄኔፈር ጋርነር ከተባለችው ተዋናይት ጋር ለ10 ዓመታት ገደማ በትዳር ቆይቶ ሦስት ልጆችን ወልዷል።












