'ቦዲ ቢውልደሮች' በወጣትነታቸው እየሞቱ ያሉት ለምንድነው?

ጡንቻማ የሰው አካል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ብራዚላዊው ማይልሰን አራውጆ፣ የሰውነት ቅርጹን የሚያሳይ ፎቶ ጂም ውስጥ ተነስቶ ለጠፈ። ፕሮፌሽናል የሰውነት ግንባታ ስፖርተኛ (ቦዲቢውልደር) እና በአስር ሺህዎች ተከታይ ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪ ያደረገው ይህ የዳበረው ሰውነቱ ነው።

ቀይ ካኒቴራ አድርጎ ነበር። ፎቶው ላይ በስፖርት ማምጣት የማይቻል የሚመስሉት ጡንቻማ ክንዶቹ ይታያሉ። የጡንቻው ግዝፈት ፊልም ላይ ያለ 'ጀግና' ገጸ ባህሪ አስመስሎታል።

ከሰዓታት በኋላ ግን የ35 ዓመቱ ስፖርተኛ በብራዚል ባህያ ግዛት ቤቱ ውስጥ እያለ ሕመም ተሰምቶት ሕይወቱ አልፏል።

አራውጆ በምን ምክንያት እንደሞተ እስካሁን ባይረጋገጥም፣ በድንገት ሕይወታቸው ካለፈ የሰውነት ግንባታ ስፖርተኞች አንዱ ሆኗል።

ግንቦት ላይም በብራዚል ከሚገኙ ወጣት ታዋቂ የሰውነት ግንባታ ስፖርተኞች አንዱ የሆነው ገብርኤል ጋንሌይ በ22 ዓመቱ በድንገተኛ የልብ ሕመም ሕይወቱ አልፏል።

ባለፈው ዓመት ደግሞ ሁለት የ30 እና 40 ዓመት ብራዚላውያን ቦዲቢውልደሮች ከልብ ጋር በተያያዘ ሕመም ሞተዋል። አንዱ ሕይወቱ ያለፈው የሰውነት ቅርጽ ውድድር ላይ እያለ ነበር።

በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ተመሳሳይ ድንገተኛ ሞቶች ታይተዋል። በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ በ26 ዓመቱ የሞተው አሜሪካዊው ዳላስ ማክካርቨር እና 2023 ላይ በ30 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈውን ጀርመናዊው ጆ ሊንድነርን መጥቀስ ይቻላል።

ጠንካራ እና የተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው የሚመስሉት ቦዲቢውልደሮች በወጣትነታቸው በድንገት እየሞቱ ያሉት ለምንድነው?

ጡንቻማ ክንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሮፌሽናል የሰውነት ግንባታ ስፖርተኞች በድንገተኛ የልብ ህመም የመሞት ዕድል ከጀማሪዎች ጋር ሲነጻጸር ከአምስት እጥፍ በላይ እንደሚበልጥ አንድ ጥናት አሳይቷል

በ2025 በወጣ አንድ ጥናት ለሰውነት ቅርጽ ውድድር የሚደረግ የሰውነት ግንባታ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ዘርዝሯል።

ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች የመንግሥት የስፖርት መሥሪያ ቤት ከ2005 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ባካሄዳቸው ውድድሮች ላይ የተሳተፉ ጀማሪ እና ፕሮፌሽናል ቦዲቢውልደሮች ላይ ክትትል አድርገዋል።

በ'ዩሮፒያን ኸርት ጆርናል' ላይ የታተመው ጥናት፣ ከጀማሪዎች ጋር ሲነጻጸር ፕሮፌሽናል የሰውነት ግንባታ ስፖርተኞች በድንገተኛ የልብ ሕመም የመሞት ዕድላቸው ከአምስት እጥፍ በላይ ከፍ እንደሚል ደርሶበታል። እነዚህ ስፖርተኞች የልብ ምታቸው በድንገት ቆሞ ለሞት የመዳረግ ስጋት አለባቸው።

ወጣቶች እና ጤናማ ግለሰቦች በድንገተኛ የልብ ሕመም የመሞት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ይህ ዓይነቱ ክስተት ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥመው ተጨማሪ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ላይ ነው።

ጥናቱ ምርመራ ካደረገባቸው 121 የሞት ክስተቶች መካከል 46 ያህሉ የተከሰቱት በድንገተኛ የልብ ሕመም ነው።

በዚህ የጤና እክል የሚሞቱ ሰዎች አማካይ ዕድሜ 45 ነው። የሰውነት ቅርጽ ውድድሮች ላይ በንቃት የሚሳተፉ አትሌቶች ላይ ግን አማካይ ዕድሜ ወደ 34.7 ዓመት ዝቅ ይላል።

ይህ ፎቶ አሜሪካዊው ዳላስ ማክካርቨር በአውሮፓውያኑ 2017 ኮሎምበስ ኦሃዮ ውስጥ በተካሄደ የሰውነት ቅርጽ ውድድር ላይ የተነሳው ነው

የፎቶው ባለመብት, Maddie Meyer/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ይህ ፎቶ አሜሪካዊው ዳላስ ማክካርቨር በአውሮፓውያኑ 2017 ኮሎምበስ ኦሃዮ ውስጥ በተካሄደ የሰውነት ቅርጽ ውድድር ላይ የተነሳው ነው። ማክካርቨር በዚያው ዓመት ሕይወቱ አልፏል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጣልያን ውስጥ በሚገኘው ፓዶቫ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ማርኮ ቬኪያቶ የጥናቱ ዋና ፀሐፊ ናቸው። ዶ/ር ማርኮ፣ ለቦዲ ቢውልደሮች ሞት አስተዋጾ ያደረጉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ያረስዳሉ።

ከእነዚህ መካከል፣ የአካል ብቃት ማሳደጊያ መድኃኒቶችን "በተስፋፋ መልኩ መጠቀም"፣ ለውድድር ሲባል በፍጥነት የሰውነት ክብደትን መቀነስ እንዲሁም "ከመጠን በላይ የሆነ ልምምድ" ይጠቀሳሉ።

'ሰርኩሌሽን' በተባለ ጆርናል ላይ የታተመ አንድ የዴንማርክ ተመራማሪዎች ጥናት ደግሞ፣ የሰውነት መገንቢያ አናቦሊክ ስቴሮይዶችን [መድኃኒቶች] እንደሚጠቀሙ የሚታወቁ 1,189 ወንዶች ላይ ክትትል አድርጓል።

ለ11 ዓመታት ያህልም የእነዚህ ስፖርተኞችን የጤና ሁኔታ ከመደበኛው ሕዝብ ከተወጣጡ 60 ሺህ ሰዎች ጋር ሲያነጻጸር ቆይቷል።

የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው፣ ስቴሮይድ ተጠቃሚዎች የልብ ጡንቻን በሚያዳክመው 'ካርዲዮማዮፓቲ' በሽታ የመያዝ ዕድላቸው በዘጠኝ እጥፍ ገደማ ይጨምራል። ለልብ ድካም የመጋለጥ ዕድላቸው ደግሞ በሦስት እጥፍ የበለጠ ነው።

በተጨማሪም እንደ የወንድ የዘር ፍሬ ቁጥር መቀነስ እና ስንፈተ ወሲብ ያሉ ችግሮችም ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ።

ከዚህም ባሻገር አናቦሊክ ስቴሮይዶችን መጠቀም ለደም ግፊት መጨምር፣ የደም ቧንቧዎች ውስጥ ስብ በፍጥነት እንዲከማች እንዲሁም በራሱ በልብ መዋቅር ላይ ለውጦች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል።

በ'ዩሮፒያን ኸርት ጆርናል' ጥናታቸውን ያሳተሙት ተመራማሪዎች፣ ሕይወታቸው ያለፈ ቦዲ ቢውልደሮችን የአስክሬን ምርመራ ሪፖርቶች ገምግመዋል።

ብዙዎቹ ሟቾች የልባቸው መጠን ተልቆ ተገኝቷል። በተጨማሪም ደም የሚረጭበት የልብ ዋና ክፍል ወፍሮ የተገኘ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታም ለልብ ምት መዛባት እና ለልብ ድካም የመጋለጥን ዕድልን ይጨምራል።

የጤና ምርመራዎች እና ለሕዝብ ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሕይወታቸው ካለፈ ቦዲ ቢውልደሮች ውስጥ የተወሰኑት አናቦሊክ መድኃኒቶችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሲጠቀሙ ነበር።

በወጣትነታቸው ሕይወታቸው ያለፈ የሰውነት ግንባታ ስፖርተኞች ላይ የተደረጉ የአስከሬን ምርመራዎች ብዙውን ጊዜ መጠኑ ትልቅ የሆነ ልብ እንደነበራቸው ያሳያሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ መነጋጋሪ ከነበሩት ክስተቶች አንዱ፣ የ26 ዓመቱ አሜሪካዊ ወጣት ዳላስ ማካርቨር ሞት ነው። ማካርቨር በአውሮፓውያኑ 2017 ሕይወቱ ለካፈ በኋላ የተደረገው የአስክሬን ምርመራ የልቡ ክብደት 833 ግራም አሳይቷል።

ይህ የክብደት መጠን አንድ አዋቂ ዕድሜ ላይ ያለ ወንድ ሊኖረው ከሚገባው የልብ ክብደት ከሁለት እጥፍ በላይ የበለጠ ነው።

የኤምአርአይ ስካን ጤናማ የሆነ የአትሌት ልብን (በቀኝ የሚታየው) ደም የሚረጭበት ዋና ክፍሉ ከወፈረ ልብ መለየት ያስችላል። ቀዩ ቀስት የግራ ቬንትሪክል ግድግዳ ውፍረትን ያሳያል

የፎቶው ባለመብት, Bispo & Zago, 2024, Arquivos Brasileiros de Cardiologia (CC BY)

የምስሉ መግለጫ, የኤምአርአይ ስካን ጤናማ የሆነ የአትሌት ልብን (በቀኝ የሚታየው) ደም የሚረጭበት ዋና ክፍሉ ከወፈረ ልብ (በግራ የሚታየው) መለየት ያስችላል። ቀዩ ቀስት የግራ ቬንትሪክል ግድግዳ ውፍረትን ያሳያል

በአውሮፓውያኑ 2022 በአሜሪካውያን ቦዲ ቢውልደሮች የአስክሬን ምርመራ ሪፖርት ላይ የተደረገ ግምገማ፣ የልባቸው ክብደት ከመደበኛ ሰው ከሚኖረው ጋር መጠን ሲነጻጸር በ74 በመቶ ገደማ እንደሚበልጥ ደርሶበታል። ደም የሚረጭበት የልባቸው ዋናው ክፍል ደግሞ ከሚጠበቀው እስከ 125 በመቶ ድረስ ወፍሮ ተገኝቷል።

የሆርሞን እና የስፖርት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ክሌይተን ማሴዶ "ልብ እንደሌሎቹ ሁሉ ጡንቻ ነው" ይላሉ።

"ሁሌም እንደምናገረው፣ የታካሚን የክንድ ጡንቻን (ባይሴብስ) ተመልክቼ የልባቸው መጠን ምን ያህል እንደሚሆን መገመት እችላለሁ። ምክንያቱም ልብ ከሌሎች ጡንቻዎች ጋር አብሮ ያድጋል" በማለት ያስረዳሉ።

ስፖርተኞች ስቴሮይድ ሳይጠቀሙ ክብደት በማንሳት ልብ ጉዳት በሌለው እና በጤናማ ሁኔታ እንዲያድግ ሊያደርግ ይችላል።

ስቴሮይድን ተጠቅመው ከፍተኛ የክብደት ማንሳት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ግን ልብ ክብደቱ ከመጨመር ባሻገር በትክክል የመኮማተር አቅሙን ማጣት እንደሚጀምር የ'ብራዚሊያን ሶሳይቲ ኦፍ ካርዲዮሎጂ' ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኤድዋርዶ ፎንቴሌስ ሪት ይናገራሉ።

"ይህ የልብ ድካምን ያስከትላል፤ በሂደትም ወደነበረበት መመለስ የማይችልበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል" በማለት አደጋውን ያስረዳሉ።

አንዳንድ ጊዜያት ግን የልብ መወፈር በዘር ተላልፎ የመጣ ሊሆን ይችላል። ሪት "ግልፅ ያልሆነ ጉዳይ ነው" በማለት ያክላሉ።

"በዘረመል የመጣ የልብ ሕመም ሊሆን ይችላል። ከአናቦሊክ ስቴሮይዶች ጋር የተያያዘም ሊሆን ይችላል። ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ወይም የሦስቱም ድምር ሊሆን ይችላል" ሲሉ ያብራራሉ።

"ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ስቴሮይድ መጠቀም የሚቻልበት መንገድ የለም"

ሮድሪጎ ጎኤስ ሰውነት ቅርጽ ውድድር ላይ

የፎቶው ባለመብት, Rodrigo Góes

የምስሉ መግለጫ, ሮድሪጎ ጎኤስ በ26 ዓመቱ ፍሎሪዳ ውስጥ በተካሄደ አገር አቀፍ የተፈጥሮ ሰውነት ቅርጽ ውድድር ሁለተኛ ወጥቷል

የሰውነት ግንባታ ስፖርተኛ የነበረው ሮድሪጎ ጎኤስ 30 ዓመቱ ላይ በሕክምና ክትትል ሥር ሆኖ ስቴሮይድ መጠቀም እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ሲወዳደር የነበረው በተፈጥሯዊ የሰውነት ቅርጹ እንደሆነ ለቢቢሲ ኒውስ ብራዚል ተናግሯል።

ስቴሮይድ የሚወሰድ "በዙር" ነው። ዙር የሚለው ቃል ስፖርተኞቹ ስቴሮይድ እየተጠቀሙ የሚቆዩባቸውን በርካታ ሳምንታት ያመለክታል። አንዱ ዙር ሲጠናቀቅ ሰውነታቸው እንዲያገግም መድኃኒቱን መውሰድ ያቆማሉ።

ጎኤስ "ሰውነት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ አስደናቂ ነው" ይላል።

"በተፈጥሮ ሰውነትን ማሳደግ ከምታሳድገው በላይ እጅግ በፍጥነት ታድጋለህ። ስብ የሌለው ትሆናለህ፤ ጡንቻዎቻዎችም በፍጥነት ያገግማሉ። ለዚህ ነው እጅግ አጓጊ የሆነው" ሲል ያብራራል።

ጎኤስ በሕክምና ክትትል ሥር የሚወስደው የመድኃኒት መጠን በጥንቃቄ እንደሚመጠን ቢገልጽም፣ እንደ የፀጉር መረገፍ፣ ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣት እና ሌሊት ላይ የሚኖር ከባድ ላብ ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳጋጠሙት ይናገራል።

ከሁሉም የባሰው ግን ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንደሆነ ያስረዳል።

"መርፌ የመወጋት ሂደቱ በሙሉ ምቾት ሰጥቶኝ አያውቅም። በሆነ መልኩ የዕፅ ሱሰኛ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። እንዲህ ማለት ከባድ ነው ግን የሆነ የተሳሳተ ነገር እያደረኩ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር" ሲል ይናገራል።

ጎኤስ በአሁኑ ሰዓት ስቴሮይድን አላግባብ መጠቀምን በመቃወም ዘመቻ ያካሂዳል።

"አናቦሊክ ስቴሮይድስን ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ መጠቀም የሚያስችል መንገድ የለም። ሐኪሞች ሊያደርጉ የሚችሉት ጉዳቱን መቀነስ ብቻ ነው። ጉዳቱ ግን አይቀርም" ብሏል።

ሮድሪጎ ጎኤስ በእጁ ክብደት ይዞ

የፎቶው ባለመብት, Rodrigo Góes

የምስሉ መግለጫ, ጎኤስ በአሁኑ ሰዓት ስቴሮይድን አላግባብ መጠቀምን በመቃወም ዘመቻ ያካሂዳል

"የአንድ ሰውን ጡንቻ ተመልክቼ ማወቅ እችላለሁ"

ስቴሮይድ መጠቀም የሚያስከትላቸውን የጤና ጉዳቶችን ለይቶ ማስቀመጥን አዳጋች ያደረገው አንዱ ጉዳይ፣ በርካታ አገራት ከስቴሮይድ ጋር በተያያዘ ምክንያት የተፈጠሩ ሞቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ አለመመዝገባቸው ነው።

ብራዚል ውስጥ ከአናቦሊክ ስቴሮይድ ጋር የተያያዘ የተከሰቱ ሞቶችን የሚያሳይ ይፋዊ መረጃ የለም። ሌሎች በርካታ አገራትም በቋሚነት ስቴሮይድን እንደ የሞት መንስኤ አይመዘግቡም።

ብዙውን ጊዜ ሞቶቹ የሚመዘገቡት እንደ የልብ ድካም እና ስትሮክ ባሉት በቅጽበት በተከሰቱ የጤና እክሎች ነው። እነዚህ የጤና እክሎች እንዲፈጠሩ ዋነኛ ሚና ያለው የአካል ብቃት ማሳደጊያ መድኃኒት ይዘነጋል።

የሕክምና ምርመራ ባለሙያዎች እደሚናገሩት አናቦሊክ ስቴሮይዶች ሰውነት በተፈጥሮው ከሚያመርታቸው ሆርሞኖች ጋር ስለሚመሳሰሉ ከሞት በኋላ በሚደረግ ምርመራ ላይለዩ ይችለሉ።

እነዚህ ምክንያቶች ሲደራረቡ፣ ከአካል ብቃት ማሳደጊያ መድኃኒቶች ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ብዛት በትክክል ለማወቅ አዳጋች ይሆናል።

የሆርሞን እና የስፖርት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ክሌይተን ማሴዶ "በየቀኑ የምሠራው እዚህ ላይ ነው" በማለት ይናገራሉ።

"የአንድን ሰው ባይሴፕስ (የክንድ ጡንቻን) አይቼ ማወቅ እችላለሁ። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ እነዚያን ግዙፍ ጡንቻዎችን ስመለከት፣ ብዙውን ጊዜ የዚያ ሰው ልብ መዳከሙን ወይም መዳከም መጀመሩን እረዳለሁ። ጣጣው የሚመጣው ኋላ ላይ ነው" ይላሉ።