አዲሱ ትውልድ ከአልኮል መጠጥ ወደ አደገኛ መድኃኒቶች ለምን ፊቱን አዞረ?

መድኃኒት እና መጠጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የ20 ዓመቷ ሜይ ከጓደኞቿ ጋር ለመውጣት እየተዘጋጀች ነው። ጉሮሮዋ አካባቢ ሕመም ተሰማት፤ እጇ ላብ በላብ ሆነ። አንዳች የተሳሳተ ነገር እላለሁ ብላ ነበር የፈራችው።

የ20 ዓመቷ ቻይናዊት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መድኃኒት አገኘች።

ፕሪጋባሊን ይባላል መድኃኒቱ። የነርቭ ሕመም እና የሚጥል በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ለማከም ይውላል። መድኃኒቱ ለልብ ሕመም እና ጭንቀት የሚያስከትለውን አካላዊ ሕመም ለመቀነስም ይሰጣል።

ሜይ መድኃኒቱን በሕገ ወጥ መንገድ በበይነ መረብ ገዛች።

"በጣም በደስታ እሞላለሁ። በጣም ተጫዋቿ ሰው እኔ እሆን ነበር። 10 ብርጭቆ መጠጥ የመጠጣት ያህል ነው። እንደ መጠጥ ግን አያሳምምም።"

መድኃኒቱ በከፍተኛ መጠን ሲወሰድ የመስከር ዓይነት ስሜት አለው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት መድኃኒቱን ያለ ሐኪም ፈቃድ መውሰድ አደገኛ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ሕይወትን እስከማጣት ያደርሳል።

ለረዥም ጊዜ መድኃኒቱን መውሰድ ለሱስ ያጋልጣል። መድኃኒቱን የሚወስዱ ሰዎች የትኛውንም ዓይነት ማኅበራዊ ክንውን ለመፈጸም መድኃኒቱ ላይ ጥገኛ ይሆናሉ።

ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣት እና መድኃኒቱን ለማቆም ሲሞክሩ ራስን ለማጥፋት ማሰብን እንደሚያባብስም ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አዲሱ ትውልድ መጠጥ እምብዛም አይወስድም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ ትውልድ መጠጥ እምብዛም አይወስድም
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሜይ (ስሟ ተለውጧል) ምሽት ላይ መውጣትን የዘወትር ልማድ አድርጋለች። መድኃኒቱን በየቀኑ ትወስዳለች።

"ያለ መድኃኒቱ ከቤት መውጣት አልችልም" ትላለች።

በሜይ ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች በብዛት ፊታቸውን ወደ መድኃኒት እና ዕፅ እያዞሩ መጥተዋል።

ከአውሮፓውያኑ 1997 እስከ 2012 የተወለዱ አዲሱ ትውልድ (ጄን ዚ) ወጣቶች የሚያዘወትሩት አልኮል መጠጥ ሳይሆን መድኃኒቶች እና ዕፆችን ሆኗል።

አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ከአውሮፓውያኑ 1997 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ውስጥ የታየው የጭንቀት መጠን ከዚያ ቀደም ባልነበረ መጠን ጨምሯል።

ጭንቀት የተስተዋለው ከ10 እስከ 24 ዓመት ባሉ ሰዎች ዘንድ ሲሆን ቁጥሩ ከ10 ሚሊዮን ወደ 16 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።

የ61 ጥናቶች ውጤት ላይ የተሠራ ምርምር እንደሚያሳየው፤ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ከነበረው አንጻር የወጣቶች የጭንቀት መጠን ጨምሯል።

መጠጥን በመተው ሌሎች "ጤናማ" አማራጮች መሞከር የሚለው ዝንባሌ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚተዋወቁ ዕፆች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ምክንያት ሆኗል።

እነዚህ ዕፆች ከመጠጥ በኋላ የሚፈጠረውን ራስ ምታት እና ድካም (ሀንጎቨር) የማያስከትሉ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።

በቴሲዲ ዩኒቨርስቲ የሱስ ጥናት ባለሙያ ሊየም ኖውልስ "ወጣቶች እነዚህ ዕፆች የተሻሉ አማራጮች እንደሆኑ ያስባሉ። ይሄ ግን የተሳሳተ ግንዛቤ ነው" ሲል ያስረዳል።

ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማሳለጥ በሚል ምን ያህል ወጣቶች መድኃኒት ወይም ዕፅ እንደሚወስዱ በትክክል ለማወቅ ከባድ ነው። አብዛኞቹ ወጣቶች የሚገዙት በሕገ ወጥ መንገድ በበይነ መረብ ነው።

በኔቸር ኮምንኬሽንስ መጽሔት የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ፕሪጋባሊን (pregabalin) መድኃኒት ከ2008 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ሥርጭቱ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።

መድኃኒቱን ባልተገባ ሁኔታ የሚጠቀሙ እና በመድኃኒቱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ሆኗል።

ከቀደመው ትውልድ አንጻር በአዲሱ ትውልድ ዘንድ መጠጥ አይዘወተርም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከቀደመው ትውልድ አንጻር በአዲሱ ትውልድ ዘንድ መጠጥ አይዘወተርም

በቻይና ፕሪጋባሊን መድኃኒት መበዝበዝ የተጀመረው በ2024 ሲሆን፤ ዘንድሮ የአገሪቱ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውቋል።

ሕንድም ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ይፋ አድርጋለች። በዮርዳኖስ እና ዩክሬን መድኃኒቱን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።

ከዚህ መድኃኒት ጋር ተያይዘው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚመጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቪድዮዎች፤ ተጠቃሚዎች የተለያዩ መድኃኒቶችን እየቀላቀሉ እንዲወስዱ ያበረታታሉ።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተዋወቀው መድኃኒቶችን መቀላቀል (ስታኪንግ) ብቻ ሳይሆን እንዴት መድኃኒቶችን ማግኘትም እንደሚቻልም ነው።

ቢቢሲ እነዚህን መድኃኒቶች የሚሸጡ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን አግኝቷል።

ሜይ እንደምትለው በቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መድኃኒቶቹን የሚሸጡ "በሺህዎች የሚቆጠሩ" ሲሆኑ መድኃኒቶቹን ለማግኘት እና ለማዘዘም "ቀላል" ነው።

በዩክሬን የደንበኞች አገልግሎት ላይ የምትሠራው የ26 ዓመቷ ሎራ ለቢቢሲ እንደገለጸችው እነዚህን መድኃኒቶች በጓደኞቿ አማካኝነት በበይረ መረብ ማግኘት "ቀላል" ነበር።

አዲሱ ትውልድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'የማይጠጣው ትውልድ'

አዲሱ ትውልድ አልኮል መጠጥ አያዘወትርም። መድኃኒት ወይም ዕፅ መውሰድ እየተለመደ የመጣውም መጠጥ ካለመጠጣት ጋር በተያያዘ ነው።

አዲሱ ትውልድ 'መጠጥ የማይጠጣው ትውልድ' ወይም 'ሶበር ጄነሬሽን' የሚባለውም ለዚህ ነው።

ብሉምበርግ ባወጣው ዘገባ መሠረት በመላው ዓለም የመጠጥ የገበያ ድርሻ በ830 ሚሊዮን ዶላር ቀንሷል።

መጠጥ መውሰድ ከቀነሰበት ምክንያት አንዱ የወጣቶች የባህሪ ለውጥ ነው። ከወጪ እና ከጤና ጋር የተያያዙ ምክንያቶችም ይሰማሉ።

የሱስ ጥናት ባለሙያው እንደሚለው፤ ፕሪጋባሊን የሚወስዱ ወጣቶች ጤናቸውን መጠበቅ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

"ካሎሪ ወደ ሰውነታቸው ማስገባት አይፈልጉም። ይህም ክብደታቸው እንዲጨምር እና ቶሎ እንዲያረጁ ስለሚያደርጋቸው ነው" ይላል።

ዩናይትድ ኪንግደም የሚኖረው የ22 ዓመቱ ማት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያዘወትራል። መጠጥ ከመጠጣት ይልቅ መድኃኒት መውሰድ በኩላሊት እና ልብ ጤና ላይ "ያነሰ ጉዳት" እንዳለው ያምናል።

"እነዚህ መድኃኒቶች ከመጠጥ የተሻለ ጤናማ ናቸው ብለን እናስባለን" ይላል።

የጤና ቀውስ

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው አልኮል ቢያንስ ከሰባት የካንሰር ዓይነቶች ጋር ይተሳሰራል።

በ2023 ባወጣው መረጃ መሠረት፤ አልኮል በየትኛውም መጠን ለጉዳት ይዳርጋል።

በኢምፔሪያል ኮሌጅ ለንደን የሚሠሩት ኒውሮሳይኮፋርማኮሎጂስት ፕሮፌሰር ዴቪድ ነት እንደሚሉት፤ ሜይ የምትወስደው መድኃኒት ከመጠጥ ያነሰ ጉዳት ያስከትላል። ሆኖም ግን አደጋ እንዳለው ይገልጻሉ።

ፕሮፌሰር ዴቪድ የመድኃኒት ቁጥጥር የላላ እንዲሆን ይፈልጋሉ። ሆኖም ፕሪጋባሊን በከፍተኛ መጠን ሲወሰድ እንደሚጎዳ ይናገራሉ።

"መጠጥ የሚፈጥረውን ስሜት ለመፍጠር መድኃኒቱን የሚወስዱ ከሆነ ጥገኛ ይሆናሉ" ሲሉ ይገልጻሉ።

ፕሪጋባሊን ለመዝናናት የሚወስዱ ሰዎች ሰውነታቸው መድኃኒቱን መቋቋም ስለሚጀምር የሚፈልጉትን የደስታ መጠን ለማግኘት በየጊዜው መጠኑን ከፍ ማድረግ አለባቸው።

ፕሪጋባሊን በከፍተኛ መጠን ሲወሰድ ትንፋሽን ዝግ ያደርጋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሕይወትን ለአደጋ ያጋልጣል።

መጠኑ በጨመረ ቁጥር ራስን ስቶ መውደቅ እና የልብ ምት መቀነስ ይከተላል።

የመድኃኒት ጥቁር ገበያ

በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የሥነ ልቦና ባለሙያ ፕሮፌሰር ኤምሊ ጆንስ እንደሚሉት፤ እነዚህን መድኃኒቶች እና መጠጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ማወዳደር ሙሉ ምሥሉን አያሳይም።

ለፕ/ር ኤምሊ ዋናው ጥያቄ ሰዎች ማኅበራዊ መስተጋብርን ለመቋቋም የግድ መድኃኒት መውሰድ ካለባቸው መጨረሻቸው ምን ይሆናል? የሚለው ነው።

"አልኮል ሲበዛ አደገኛ ነው። ያለ ሐኪም ፈቃድ እና ክትትል መድኃኒት መውሰድም ጎጂ ነው" ይላሉ።

በማኅበራዊ መስተጋብር ወቅት መድኃኒት መውሰድ የሚያስተላልፈው መልዕክት ማኅበራዊ ግንኙነቶች አስፈሪ ናቸው የሚል ነው።

"መድኃኒት ስወስድ ብቻ ነው የምዝናናው ብሎ ማመን፤ አጠቃላይ ሕይወትን ከመድኃኒት ጋር የሚያስተሳስር ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በጊዜ ሒደት በራስ መተማመንን የሚሸረሽር ነው። ሰዎች በራሳቸው አቅም መወጣት የሚችሉትን ነገር ያለ መድኃኒት ወይም ዕፅ መተግበር እንደማይችሉ እንዲያምኑ ያደርጋል።

ሎራ መጀመሪያ ላይ የጭንቀት መድኃኒት የምትወስደው ከማኅበራዊ ክንውኖች በፊት ነበር። ቀስ በቀስ ግን ሥራ ቦታ ሆናም መድኃኒት መውሰድ ቀጠለች።

"ያግዘኝ ነበር። ከሰዎች ጋር ነው የምሠራው። መድኃኒቱ በቀላሉ እንድግባባ እና ችግሮችን እንድፈታ ረድቶኛል" ትላለች።

ለሁለት ሳምንት መድኃኒቱን ማግኘት ሳትችል ስትቀር ግን ድባቴ እና ራስን የማጥፋት ስሜት ተጫጫናት።

"ምን እየሆንኩ እንደሆነ አልገባኝም ነበር። ተጨነቅኩ፤ መብላት አቃተኝ፤ ጓደኞቼን ማግኘትም አልቻልኩም።"

ብዙ አገራት እነዚህ መድኃኒቶች ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ቢያስታውቁም፤ ቁጥጥሩ የበለጠ አደጋውን የጎላ ያደርገዋል ብለው የሚያምኑም አሉ።

በዩክሬን ሱስን ለማስወገድ የሚሠራ ተቋም ኃላፊ እና ኤፒዲሞሎጂስት ማይካይታ ላፒን እንደሚለው መድኃኒቶች ወይም ዕፆችን መከልከል ሙሉ በሙሉ ሰዎች እንዳይጠቀሙ አያግድም።

"እገዳ መጣል ሰዎችን ወደ ጥቁር ገበያ ይወስዳቸዋል። የሚገዟቸው መድኃኒቶችም ደረጃቸው የወረደ ይሆናሉ" ሲል ያስረዳል።

መድኃኒቱን ማገድ ተጠቃሚዎች ምን ዓይነት መድኃኒት እንደሚገዙ ሳያውቁ ሌሎች መድኃኒቶችን እንዲገዙ እንደሚገፋፋ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ለምሳሌ መጠጥ ሲሸጥ የአልኮም መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ በጠርሙሱ ላይ ይጻፋል። ይህ ግን ከበይነ መረብ ለሚገዛ መድኃኒት አይሠራም።

ሜይ መድኃኒቱን ለመዝናናት በሚል መውሰድ ብትጀምርም ማቋረጥ እንደማትችል ስታስብ ትጨነቃለች።

"አስፈሪ ነው። እንዴት ያለ መድኃኒቱ መኖር እንደምችል አላውቅም።"