የፕሪሚየር ሊጉ መሪዎች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ውጤት ግምቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ታላላቆቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች ግጥሚያ ይኖራቸዋል። በእነዚህ ጨዋታዎች የሚገኙ ውጤቶች የሊጉ መሪዎች የያዙትን ደረጃ እንዲያጠናክሩ ወይም ከፍ እና ዝቅ እንዲሉ ያደርጋቸዋል።
በሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ ላይ ከአንድ አስከ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቡድኖች ወሳን ግጥሚያ ይኖራቸዋል። በዚህም መሪው ሊቨርፑል ከብሬንትፈርድ፣ አርሰናል ከበርንሊ፣ ማንችስተር ሲቲ ከቼልሲ ጋር ይጫወታሉ።
እነዚህን እና ሌሎች የሳምንቱ ማብቂያ ግጥሚያዎች ምን ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል የቢቢሲ የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ግምቱን አስቀምጧል።

ብሬንትፈርድ ከ ሊቨርፑል
ብሬንትፈርድ ከዚህ በፊት በሜዳው ከሊቨርፑል ጋር በገጠመባቸው ሁለት ጨዋታዎች ሦስተ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፣ ስለዚህም የቅዳሜው ግጥሚያ ለሊቨርፑል ቀላል ይሆናል ብዬ አላስብም።
አርሰናል እና ማን ሲቲ ብሬንትፈርዶችን በሜዳቸው ለማሸነፍ ከባድ ፈተና ነበር የገጠማቸው፣ ስለዚህም በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በመሪነት ለመቆየት የርገን ክሎፕ ቀላል የማይባል ፈተና ይጠብቃቸዋል።
በቅርቡ የተጫዋቾች ጉዳት የገጠመው ሊቨርፑል አሁን ደግሞ የቴሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ ጉዳት ሌላ ጫና ቢኖረውም፣ የኮነር ብራድሊ ልምምድ መጀመር እና የሞሐመድ ሳላህ ወደ ሙሉ ብቃት መመለስ በቅዳሜው ጨዋታ ቡድኑን ይጠቅመዋል።
ግምት፡ ብሬንትፈርድ 1 – 2 ሊቨርፑል

በርንሊ ከ አርሰናል
አንዳንድ ሰዎች እንደሚገምቱት ይህ ጨዋታ ለአርሰናል ቀላል ይሆናል ብዬ እኔ አላስብም። በርንሊዮች በሊቨርፑል ሲሸነፉ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተው፣ ጥሩ ጀምረው፣ ወሳኝ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም ፍሬያማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በውድድር ዘመኑ ሦስት ጨዋታዎችን ነው ያሸነፉት ከወራጅ ቀጠናው ቢያንስ ሦስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። ስለዚህም ከዚህ በኋላ ያሏቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች ‘ማሸነፍ አለብን’ ብለው ነው መግባት ያለባቸው።
ይህ ጨዋታ ለአርሰናልም ወሳኝ ነው። የቀደሙ ወሳኝ ጨዋታዎችን ያሸነፉት የሚኬል አርቴታዎቹ አርሰናሎች ከበርንሊ ጋር የሚያደርጉት ግጥሚያ ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በሊጉ ውስጥ ለመቆየት የሚፋለሙት በርንሊዮች ግጥሚያውን አደገኛ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ግምት፡ በርንሊ 1 – 2 አርሰናል

ፉልሃም ከ አስተን ቪላ
በጉዳት ምክንያት ቡባካር ካማራ አለመሰለፉ ለአስተን ቪላ አሳሳቢ ጉዳይ ሲሆን፣ በሜዳቸው ሲጫወቱ በአብዛኛው ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኑት ፉልሃሞች ለአስቶን ቪላ ከባድ ፈተና ይሆናሉ።
ከማንችስተር ዩናይትድ እና ከቶተንሃም ጋር በቀዳሚዎቹ አራት ቡድኖች ውስጥ ለመካተት የሚጥረው ቪላ፣ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ አለበት።
ነገር ግን ፉልሃም ባለፉት ጨዋታዎች ካሳየው ብቃት አንጻር ከዚህ ጨዋታ አንድ ነገር ይዞ ይወጣል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ ፉልሃም 1 – 1 አስተን ቪላ

ኒውካስት ከ ከቦርንማውዝ
ኒውካስሎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውጤት እያስመዘገቡ ነው። ቦርንማውዝ በዚህ የውድድር ወቅት ኒውካስልን አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።
የቀድሞ ቡድናቸውን የሚገጥሙት የኒውካስሉ አሠልጣኝ ኤዲ ሃው በሜዳቸው ይህንን ጨዋታ ይሸንፋሉ ብዬ አላስብም።
ግምት፡ ኒውካስል 2 – 1 ቦርንማውዝ

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ዌስት ሃም
ሁለቱም ቡድኖች ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይፈልጋሉ፤ 2024 ከገባ በኋላም ቡድኖቹ ያሸነፉት ጨዋታ የለም፤ ስለዚህ ይህንን ዕድል ሁለቱም ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ።
ዌስት ሃሞች ባለፈው በሜዳቸው በአርሰናል ከገጠማቸው የ6 ለዜሮ ሽንፈት ለማገገም ይህንን ጨዋታ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሊያዩት ይችላሉ።
ሱተን ግን ይህ የሚሆን አይደለም ይላል፤ ምንም እንኳን የዴቪድ ሞይስ ቡድን ጠንካራ ቢሆንም፣ ቀደም ባለው ሳምንት ከባድ ሽንፈት የገጠመው ቡድናቸው በቀላሉ ወደ አሸናፊነት ይመለሳል ብሎ እንደማያስብ ሱተን ይናገራል።
ዌስት ሃሞች ከአርሰናል ጋር በነበራቸው ግጥሚያ ላይ እንደታዩት ቀላል ሆነው ባይቀርቡም፤ ኖቲንግሃም ፎረስቶች ግን የማሸነፍ ዕድል አላቸው ይላል።
ግምት፡ ኖቲንግሃም ፎረስ 2 – 1 ዌስት ሃም

ቶተንሃም ከ ዎልቭስ
ባለፈው ኅዳር ላይ ዎልቭስ ቶተንሃምን ማሸነፉ ይታወሳል፤ ነገር ግን አሁን ቶተንሃሞች ሽንፈታቸውን ሊበቀሉ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ።
ባለፈው ሳምንት ሱተን ቶተንሃም ብራይተንን ያሸንፋል ብሎ የሰጠው ግምት ትክክል ነበር። በዚህም ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሎ ነበር።
ግምት፡ ቶተንሃም 3 – 1 ዎልቭስ

ማንችስተር ሲቲ ከ ቼልሲ
ኮል ፓልመር ለቼልሲ ተሰልፎ የቀድሞ ቡድኑን ለመግጠም ወደ ኢቲሃድ ስታዲየም ያመራል። የማንችስተር ሲቲው አሠልጣን ፔፕ ጓርዲዮላ ፓልመር ቡድኑን እንዲለቅ መፈቀዱ ስህተት ነው ይላል ሱተን።
ቢሆንም ግን የሲቲ እና የቼልሲ ጨዋታ የሚጠናቀቀው ምርጥ ተጫዋቾችን በሚያሰልፈው እና በጥሩ አቋም ላይ በሚገኘው በማንችስተር ሲቲ አሸናፊነት ብቻ እንደሚሆን ገምቷል።
ግምት፡ ማን ሲቲ 2 – 0 ቼልሲ

ሼፊልድ ዩናይትድ ከ ብራይተን
ሼፊልድ ዩናይትድ ባለፈው ሉተንን ባሸነፉበት ጊዜ አሁንም ለአሸናፊነት የመፋለም ኃይል እንዳለው አሳይቷል። ነገር ግን ይህንን ብቃት አሁንም ብራይተን ላይ መድገም ያስፈልገዋል።
ቢሆንም ግን በዚህ ሼፊልድ ዩናይትዶች በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ የአሸናፊነት ዕድላቸው የጠበበ መሆኑን ሱተን በግምቱ ላይ አስቀምጧል።
ግምት፡ ሼፊልድ ዩናይትድ 0 – 2 ብራይተን

ሉተን ከ ማንችስተር ዩናይትድ
ባለፈው ሳምንት ሉተን በወራጅ ቀጠና ውስጥ በሚገኘው ሼፊልድ ዩናይትድ ይሸነፋል ብሎ የገመተ ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ስለዚህም ይህ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ለእነሱ በጣም ወሳኝ ነው።
ሉተኖች በሜዳቸው ከታላላቅ ክለቦች ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ በጣም ጥሩ ብቃትን ያሳያሉ። በመጪው እሁድ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር በሚኖራቸው ግጥሚያም ተመሳሳይ ይሆናሉ ብዬ እጠብቃለሁ።
ባለፈው ኅዳር ላይ ሉተኖችን በኦልድ ትራፎርድ ያስተናገዱት ዩናይትዶች በጠባብ ውጤት ነበር ለማሸነፍ የቻሉት። አሁን ደግሞ ይህ ውጤት የበለጠ እንደሚጠብ ሱተን ይጠብቃል።
ግምት፡ ሉተን 2 – 2 ማንችስተር ዩናይትድ












