የጣሪያ ቆርቆሮ ሰረቁ የተባሉት የኡጋንዳ ሚኒስትር ፋሲካን እስር ቤት ሊያሳልፉ ነው

ታትሟል

የኡጋንዳ የካቢኔ ሚኒስትር ሜሪ ኪቱቱ የጣሪያ ቆርቆሮ ሰርቀዋል በሚል ተከሰሱ።

ሚኒስትሯ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብለዋል።

የጣሪያ ቆርቆሮዎቹ ለሰሜን ምሥራቅ ኡጋንዳ ተፈናቃዮች እንዲደርሱ ነበር የታሰቡት።

የሙስና አጣሪ ኮሚሽን እንዳለው ቆርቆሮዎቹ ለታሰበላቸው ወገኖች ሳይደርሱ ሚኒስትሮች ተከፋፍለዋቸዋል።

ከነዚህ ሚኒስትሮች አንዷ ደግሞ የካቢኔ ሚኒስትር የሆኑት ሜሪ ኪቱቱ ናቸው ሲል ከሷል።

ሜሪ ኪቱቱ የዚህ ካራሞጃ የተባለው ክልል አስተዳዳሪ ናቸው።

ከሜሪ ኪቱቱ ሌላ 10 ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቆርቆሮውን ተቀራምተውታል ተብሏል።

መርማሪ ኮሚሽኑ እንዳለው የጣሪያና የአጥር ቆርቆሮውን ከተቀራመቱት መሀል ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፓርላማ አፈ ጉባኤው ይገኙበታል።

በጠቅላላ ተዘረፉ የተባሉት የጣሪያ ቆርቆሮዎች ብዛት 14ሺህ 500 ይደርሳል።

ስማቸው ከዘራፊዎች ተርታ የተጠቀሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ይቅርታ ጠይቀው ቆርቆሮ የመለሱ ሲሆን ሌሎችም የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ መክረዋል።

አንድ ሌላ ሚኒስትርም ደግሞ ተቀብለው የነበረው ቆርቆሮ ከአጥር ላይ ነቅለው መልሰዋል ሲሉ የአገሬው ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ካራሞጃ ክልል ለተከታታይ ዓመታት በድርቅ የሚጎሳቆል ሲሆን ዝናብ ሲዘንብ ደግሞ በጎርፍ የሚጠቃ አካባቢ ነው። በዚህ የተነሳም አካባቢው በተረጂነት የሚታወቅ ነው።

የዚህ አካባቢ አስተዳዳሪ ሚኒስትሯ ሜሪ ኪቱቱ ረቡዕ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ክሳቸው እንደሚለው እርሳቸው ቆርቆሮዎቹን ለተረጂዎች ከማድረስ ይልቅ ለዘመዶቻቸውና ለባለሥልጣናት አከፋፍለዋል።

እርሳቸው ግን ክሱ ውሸት ነው ሲሉ ፍርድ ቤት ተከራክረዋል።

ከርሳቸው ጋር ወንድማቸው ማይክል ኪቱቱም የተከሰሰ ሲሆን 100 ቆርቆሮ ወስዷል ይላል ክሱ።

እርሱም ልክ እንደ እህቱ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።

የሚኒስትሯ ሜሪ ኪቱቱ ፍርድ ቤት መቅረብ በኡጋንዳ ሚዲያ በስፋት ሲጠበቅ የነበረ ነው ተብሏል። በርካታ ሚዲያዎችም ፍርድ ቤት ታድመዋል።

ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅትም ፊታቸውን እና ጭንቅላታቸውን በሻሽ ሸፍነው ነበር።

የሚኒስትሯ ጠበቃ የዋስ መብት እንዲከበርላቸው የጠየቁ ሲሆን ጥያቄያቸው ግን ተቀባይነት አላገኘም።

አቃቢ ሕግ በዋስ እንዳይለቀቁ የተከራከረ ሲሆን በተለይ ኪቱቱ የእናታቸው ቤት ሲፈተሽ ቆርቆሮ የተገኘ ቢሆንም ቃል እንዳይሰጡ ከልክለዋቸዋል ብሏል።

ስለዚህ በዋስ ቢለቀቁ አደጋው የከፋ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ኪቱቱ የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስት ሲሆኑ ማውንት ኢልጎን የሚባለውን የተወለዱበትን አካባቢ በስፋት በማጥናት ይታወቃሉ።

የፓርላማ አባል የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2016 ሲሆን ከዚህ ቀደም የኢነርጂና ማዕድን ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

በኡጋንዳ ትልልቅ ባለሥልጣናት በሙስና መዘፈቅ ዜና የተለመደ ቢሆንም ሚኒስትሮቹ ይቅርታ ሲጠይቁ አልያም ሥልጣን ሲለቁ ማየት ግን ብዙም አልተመለደም።

ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የሰረቁት ሁሉ ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙም ጠይቀዋል።