ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን ወታደራዊ አገዛዙን በመቃወም በተካሄደ ሰልፍ በርካቶች መጎዳታቸው ተገለጸ
በሱዳን ወታደራዊ መንግሥቱን በመቃወም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ባካሄዱት ሰልፍ በርካቶች መጎዳታቸው ተገለጸ።
ተቃዋሚዎቹ ቁጣቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡት በአገሪቷ በሲቪል የሚመራ መንግሥት ለመመሠረት የሚደረገው የመጨረሻ ስምምነት በመዘግየቱ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ አውሮፓውያኑ 2019 አገሪቷን ለአስርት ዓመታት የመሩትን ጀነራል ኦማር አል በሽርን ከሥልጣን ለማስወገድ የተካሄደውን ተቃውሞ ለማሰብም ያለመ ነው።
ሐሙስ መጋቢት 28፣ 2015 ዓ.ም. በዋና መዲናዋ ካርቱም እና በሌሎች ከተሞች በተካሄደው ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች አውራ ጎዳናዎችን በመዝጋት ወታደራዊ አገዛዙ ሥልጣኑን ለሲቪል አስተዳደሩ እንዲያስረክብ ጠይቀዋል።
በርካቶችም መፈክር በመያዝ እና በማሰማት ጦሩ በፖለቲካ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ አውግዘዋል።
የጸጥታ ኃይሎችም በዋና መዲናዋ በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ለማምራት አቅደው የነበሩ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።
ተቃውሞው የተቀሰቀሰው የሱዳን መሪዎች የሲቪል መንግሥት እንደገና ለመመስረት የሚያደርጉትን ስምምነት በድጋሜ ካራዘሙ በኋላ ነው።
ስምምነቱን እንዲዘገይ ያደረገው በወታደራዊ ቡድኑ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ነው።
የሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጄነራል ሐምዳን 'ስህተት ነበር' ባሉት እና እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 2021 በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ፖለቲካዊ ቀውስ አጋጥሟታል።
መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎም የጦር ኃይሉ አዛዥ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በየሳምንቱ በሚባል ደረጃ የጸረ መፈንቅለ መንግሥት ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
የጸጥታ ኃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ገድለዋል በሚል ይከሰሳሉ።
ጦሩ ሥልጣኑን መያዙ ለጋሾች ዕርዳታ እንዲያቋርጡ ያደረጋቸው ሲሆን ይህም የሱዳን ኢኮኖሚም እንዳይረጋጋ አድርጎታል ተብሏል።
ከአል-በሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሱዳን የአገሪቱ ጦር ሥልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር አሳልፎ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ቆይቷል።
ይህንን ተከትሎ ከጥቂት ወራት በፊት ወታደራዊው ሉዓላዊ ምክር ቤት ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር አስተላልፋለሁ ብሎ ነበር።
የሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጄነራል ሐምዳን ዳጋሎ የካቲት ወር ላይ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር፣ ጦሩ ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር አስተላልፋለሁ ማለቱ የሚወደስ መሆኑን ገልጸው፤ በአገሪቱ የደኅንነት ሪፎርሞች እንደሚካሄዱ እንዲሁም እርሳቸው የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ወደ አገሪቱ ጦር እንደሚቀላቅሉም መናገራቸው ይታወሳል።