ኪዬቭ ከሩሲያ የአየር ድብደባ በኋላ ያጋጠማት የኃይል መቋረጥ ለረጅም ጊዜ ይቆያል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሩሲያ የኃይል መሠረተ ልማት ላይ በፈፀመችው ጥቃት ሳቢያ በዋና መዲናዋ ኪዬቭ የተከሰተው የኃይል መቋረጥ ከአራት ሰዓት በላይ ለሆነ ረጅም ጊዜ እንደሚቆይ የዩክሬን ባለሥልጣናት በመዲናዋ የሚኖሩ ሕዝቦችን አስጠነቀቁ።
የኃይል መቋረጡ ያጋጠመው በኪዬቭ ብቻ ሳይሆን ድኒፕሮ ከተማን ጨምሮ በማዕከላዊ የዩክሬን ክልል ጭምር ነው።
ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ "አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለችግር የተዳረገ ቢሆንም ይህ ጥቃት ግን እኛን አይሰብረንም!” ብለዋል።
በዚህ ወር ሩሲያ ወደ ዩክሬን በርካታ ሚሳይሎችን የተኮሰች ሲሆን ኢራን ሰራሽ በሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ጥቃት ፈፅማለች።
ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ በትቃቱ የዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማቶች መመታታቸውን ተናግረዋል። እንደ ፕሬዚደንቱ ከሆነ አንድ ሦስተኛው የአገሪቷ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያም ወድሟል።
ባለቤትነቱ የግል የሆነው የኃይል ኩባንያ ድቴክም ኪዬቭ ግዛት 30 በመቶ የሚሆነው የኃይል ምንጯን ማጣቷን ገልጿል።በዚህም ምክንያት ያልተጠበቀ የኃይል መቋረጥ ማጋጠሙ አይቀሬ ነው ብሏል።
የኩባንያው ዳይሬክተር ዲሚይትሮ ሳክሃሩክ የደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኃይል መቋረጡ በግለሰቦች ቤት ከፈጠረው ችግር ባሻገር የመንገድ መብራቶች እና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎቶች ገድቧል።
የአውሮፓ ኅብረት እና የኪዮቭ ዓለም አቀፍ አጋሮች ሆን ተብሎ ሰላማዊ ሰዎች የሚገለገሉባቸው መሠረተ ልማቶች ኢላማ መደረጉን አውግዘዋል።
የዩክሬን ሁለተኛዋ ከተማ ካርኪቭም በሩሲያ ድብደባ ክፉኛ የተጎዳች ሲሆን ከዚይቶሚር፣ ፖልታቫ እና ቸርኒሂቭ ከተሞች ጋር ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የኃይል መቋረጥ አጋጥሟታል።
ሩሲያ ከሳምንታት በፊት ወደ ጠቀለለቻት ክሪሚያ የሚያገናኛት ኬርች ድልድይ ላይ ለደረሰው የቦምብ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት በዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና ሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈፅመውን የሚሳይል ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በድልድዩ ላይ የተፈጠረውን ፍንዳታ “ የዩክሬን የሽብር ተግባር” ብለውታል። ድልድዩ ትላልቅ የዩክሬን ግዛቶችን ወደ ሩሲያ የመጠቅለል ዘመቻ ምልክት ነው።
በኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተቀጣሪ የሆነው ፓቭሎ "ለመጀመሪያ ጊዜ መጠነ ሰፊ የሆነውን ውድመት ተጋፍጠናል" ሲል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።
ስሙ ያልተጠቀሰው የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ሁለት ጊዜ በሚሳይል እና 'ካሚካዜ' በተባለው ኢራን ሰራሽ ድሮን ኢላማ ሆኗል።
ጥገናው ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ሲደረግ እንደቆየ የተናገረው ፓቭሎ፣“ የወደሙት መሣሪያዎች ልዩ በመሆናቸው አሁንም ችግሮች አሉ።ተመሳሳይ መለዋወጫ ማግኘት አስቸጋሪ ነው” ብሏል።












