ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለም በጣም አደገኛ ጊዜ ተጋርጦባታል- ፑቲን

ዓይናችን ፊት የወደፊቱ የዓለም ሥርዓት እየተፈጠረ ነው- ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም “ምናልባትም በጣም አደገኛ” የሚባሉ አስር ዓመታት ተጋርጦባታል ሲሉ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስጠነቀቁ።

ፕሬዝዳንቱ ሐሙስ ዕለት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ንግግር  አድርገዋል። ሃገራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትገለል ምንክንያት የሆነውንና በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ ምክንያታዊ ለማድረግም ጥረዋል።  

ፑቲን ወዳጆቻቸው ሞስኮ ላይ ፊታቸው እንዲያዞሩ ለማስገደድ ምዕራቡ ዓለም በሩስያ ላይ ሃሰተኛ የኒውክሌር ጥቃት ዘመቻ ፈጥረዋል ሲሉ ከሰዋል።

ምዕራባውያን በቅርቡ የክሬምሊንን የኒውክሌር ዛቻ አውግዘዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዩክሬን “ቆሻሻውን ቦምብ” [ራዲዮ አክቲቭ ንጥረ ነገር ያላቸው ቦምቦች ናቸው] ልትጠቀም ትችላለች በማለት ሩሲያ ያቀረበችውን ያልተረጋገጠ ውንጀላ ኔቶ አውግዟል።  

የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ የኅብረቱ አባላት "ይህንን ውንጀላ አይቀበሉም። ሩሲያ ጉዳዩን ለማባባስ እንደ ምክንያት መጠቀም የለባትም" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ንግግሩን ያደረጉት 300,000 የሚጠጉ ሩሲያውያንን ለጦርነት ለማሰባሰብ ባደረጉት እንቅስቃሴ እና በዩክሬን ተከታታይ ወታደራዊ ሽንፈቶች ገጥሟቸው በሃገር ውስጥ ህዝባዊ ቁጣው ከጨመረ በኋላ በዓመታዊው የቫልዳይ መድረክ ላይ ነው።

ከንግግሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኑክሌር ልምምዶችን ተከታትለዋል። "ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ምንም ነገር ተናግረን አናውቅም። የምዕራባውያን ሃገራት መሪዎች ለሚሰጡት አስተያየት ፍንጭ ሰጥተናል" ሲሉም ለታዳሚዎቹ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን የቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ በነሐሴ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አስፈላጊ ከሆነ የኒውክሌር ቁልፉን ለመጫን ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውን አንስተዋል። የዩናይትድ ኪንግደም አጋሮች አለመቃወማቸው እንዳስገረማቸው "ምን ማድረግ ነበረብን? ዝም ማለት? ያልሰማን መምሰል?" ሲሉ ገልጸዋል።

ሩሲያ ራሷን ለመከላከል “ያላትን ሁሉ” እንደምትጠቀም ደጋግመው ማስጠንቀቃቸው የኒውክልር ጥቃት ዛቻ ተደርጎ በብዙዎች ተወስዷል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩስያው መሪ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ዙሪያ “በጣም አደገኛ” ንግግሮች ውስጥ ገብተዋል ሲሉ ከሰዋል።

ጦር መሳሪያ

የፎቶው ባለመብት, RUSSIAN DEFENCE MINISTRY

“ለምንድነው እሱ ስለ ታክቲካዊ የኑክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም እያወራ ያለው? ምንም ሃሳብ ከሌለው ስለ ጉዳዩ ለምን ያወራል?” ሲሉ ባይደን ከአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጠይቀዋል።

የሃገሮችን ሉዓላዊነትና ልዩ መሆንን ለመንፈግ “አደገኛ፣ ደም አፋሳሽ እና ቆሻሻ ጨዋታ” ያደርጋሉ ሲሉ በቅርቡ በምዕራቡ ዓለም ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት ደግመዋል። በዓለም ጉዳዮች ላይ የምዕራቡ ዓለም “ያልተከፋፈለ የበላይነት” እያከተመ ነው ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል።

"እኛ ታሪካዊ ድንበር ነን። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በጣም አደገኛ፣ የማይገመት እና በተመሳሳይ ጊዜም በጣም አስፈላጊው አስርት ዓመታት ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

ምዕራባውያን ከእንግዲህ በኃላፊነት መምራት አልቻሉም። ሆኖም "በጣም እየሞከሩ" ነው። "ዓይናችን ፊት የወደፊቱ የዓለም ሥርዓት እየተፈጠረ ነው" ሲሉ በአሜሪካ የሚመራውን እና ሩሲያን ለማጥፋት የሚሞክሩ ያሏቸውን ምዕራባውያን ከሰዋል። ይህንን የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ ግን አልቀረበም።