ውሃ ተከልክሎ በጥም የሞተው አሜሪካዊ ተማሪ አትሌት ቤተሰቦች 14 ሚሊዮን ዶላር ሊከፈላቸው ነው

የ20 ዓመቱ ግራንት ብሬስ

የፎቶው ባለመብት, Brace Familu

ታትሟል

በስልጠና ላይ እያለ ውሃ እንዳይሰጠው በአሰልጣኞቹ ተከልክሎ በጥም የሞተው አሜሪካዊ አትሌት ቤተሰቦች ካሳ ሊከፈላቸው ነው።

በኬንታኪ ግዛት የሚገኘውና አትሌቱ ይማርበት ዩኒቨርስቲ ለቤተሰቦቹ 14 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈልም ተስማምቷል።

የ20 ዓመቱ ግራንት ብሬስ የፍልሚያ ስፖርት ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን ኮረብታማ የሆነ ስፍራ ላይ ወደላይና ወደታች በተደጋጋሚ ከሮጠ በኋላ ህይወቱ ያለፈው ከሁለት ዓመት በፊት ነሐሴ ወር ላይ ነበር።

በከፍተኛ ሙቀት እየተቃጠለ ውሃ ስጡኝ ቢልም አሰልጣኞቹ ውሃ እንዲጠጣ እንዳልፈቀዱለት ጠበቆቹ ተናግረዋል።

በክሱ ላይ የተጠቀሱት ሁለት አሰልጣኞች በቡድኑ ላይ “የሚያስፈራራ ድባብ ፈጥረዋል” ተብሏል።

የኩምበርላንድ ዩኒቨርስቲ ሂደቱ በዚህ መጠናቀቁ ለቤተሰቡ ትንሽ እፎይታ ሊፈጥር እንደሚችል ተስፋ አለኝ ብሏል።

ሆኖም ክሱ ወደ ፍርድ ቤት ቢያመራ ኖሮ ዩኒቨርስቲው እንደሚያሸንፍ ሙሉ እምነቱን ገልጿል።

“ጉዳዩን በህጋዊ ሂደቱ ጅማሮ ላይ መቋጨት ለቤተሰቡ በተወሰነ መልኩ ሰላምና ፈውስ እንደሚያመጣላቸው ከልብ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ቻንስለር ጄሪ ጃክሰን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በክሱ መሰረት ሉዊስቪል በምትባል ስፍራ ተወላጅ የሆነው ግራንት በግቢው ውስጥ “የቅጣት ተራራ” ተብሎ የሚጠራው ፈታኝ ልምምድ ካደረገ በኋላ ከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ገብቶ ነበር።

ግራንት ከዚህ ቀደም በሚጥል በሸታና ኤዲኤችዲ የተባሉ ህመሞች ስላሉበት መድኃኒት መውሰድ እንዲሁም በተለይም በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወቅት ብዙ ውሃ መጠጣት ይጠበቅበት ነበር።

ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ህመሞች ቢኖሩበትም ሁለቱ አሰልጣኞች ግራንት የውሃ እረፍት ሲጠይቅ ያፌዙበትና ያሸማቅቁት እንደነበርና “አንተ የተለየህ ስለሆንክ ነው ተጨማሪ ውሃ ስጡኝ የምትለው” ይሉት ነበር።

በሞተበት ዕለትም ኮረብታማውን ስፍራ ወደላይና ወደታች ከወጣ በኋላ በጣም በከፍተኛ ድካም ተቀምጦ እንደነበር ክሱ አትቷል።

በማረፉ ከቡድኑ እንደሚባረር ከተነገረው በኋላ እንገደገና ወደ ሩጫው እንደተመለሰና በመጨረሻም በኮረብታው አናት ላይ “በቃኝ ከዚህ በላይ አልቻልኩም” በማለት ተናግሯል።

በከፍተኛ ሙቀትም እየተሰቃየ ውሃ እፈልጋለሁ እባካችሁ እርዱኝ ብሎ ሲለምን እንደነበርና ለሰዎች እንደሚሞትና ቃላቱም መቆራረጥ መጀመሩ ተጠቅሷል።

ቡድኑ ወደ ክፍላቸው ከተመለሱበት በኋላ አሰልጣኞቹ በቁጣ የጮሁበት ሲሆን እነሱን ትቶ ውሃ እየፈለገ እንደነበርና ሳያገኝም ወድቆ እንደሞተ ተጠቅሷል።