ሚስጥራዊ ሰነዶች የተገኙባቸው ትራምፕ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ወደ ፍሎሪዳ አቀኑ

ታትሟል

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው አስቀድሞ ወደ ፍሎሪዳ ሚያሚ አቅንተዋል።

ብሄራዊ የደህንነት ሰነዶችን ባልተገባ ሁኔታ በመያዝ የተከሰሱት ትራምፕ ፍርድቤት ከመቅረባቸው በፊት ያለውን ሌሊት በፍሎሪዳ ያሳልፋሉ።

ትራምፕ ኒው ጀርሲ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሚያሚ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው የቅንጦት ቤታቸው (ሪዞርታቸው) ነው የበረሩት።

ትራምፕ ከኒውክሌር ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ጨምሮ በርካታ ሚስጥራዊ ሰነዶችን እጃቸው ላይ በማቆየት በርካታ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ትራምፕ የፍረንጆቹ አዲስ ዓመት ከገባ በኃላ በወንጀል ሲከሰሱ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በቀጣዩ ዓመት ለሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ እያካሄዱ የሚገኙትና በፌዴራል ደረጃ ክስ የተመሰረተባቸው የመጀመሪያው የቀድሞ ፕሬዝደንት የሆኑት ትራምፕ የፈጸምኩት ያልተገባ ተግባር የለም ብለዋል።

በሌላ በኩል የሚያሚ ከንቲባ ፍራንሲስ ሱዋዝራ የትራምፕን ፍርድ ቤት ውሎ ለማስተናገድ ከተማዋ እየተዘጋጀች እንደሆነ ተናግረዋል።

እስከ 50 ሺህ ሰው ይሰበሰባል ተብሎ በታሰበበት ቀን ፖሊስ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ እንደሚሰማራ የገለጹ ቢሆነም ይሰበሳበሉ ተብሎ የሚጠበቀው ሰው ከተገመተው ዝቅ ያለ እንደሚሆን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ትራምፕ ክስ ከተመሰረተባቸው በኃላ ባለፈው ቅዳሜ ህዝብ ፊት የታዩ ሲሆን ይህ የፍርድ ቤት ጉዳይ “ሙሰኛ” በሆነው ኤፍ ቢ አይና በፍትህ መስሪያ ቤት የተደረገ “የምርጫ ጣልቃ ገብነት” ብለዋል።

ትራምፕ ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ከቅርብ አጋራቸው ዋልት ናውታ ጋር ነው። ናውታም በተመሳሳይ ክስ ነው ፍርድ ቤት የሚቀርቡት።

የትራምፕ የቅርብ አጋር ብሄራዊ የደህንነት ሰነዶችን ባልተገባ መንገድ ከመያዝ ጋር በተገናኘ ስድሰት ክሶች የቀረበባቸው ሲሆን ሁለቱም በመጀመሪያው ውሎ በተመሳሳይ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ፍርድ ቤት የዜና ተቋማት ዛሬ የሚውለውን ችሎት ፎቶ ለማንሳትና ቪዲዮ ለመቅረጽ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። ሆኖም የፍርድ ቤቱን ሁኔታ በስዕል ለማስቀረት የሚችል ባለሙያ ግን በችሎቱ ይገኛል።

ከፍርድ ቤት በኃላ ትራምፕ ቤድሚኒስትር አምርተው ለመገናኛ በዙሃን አስተያየት እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

ባለፈው ነሃሴ ወር በፍሎሪዳ በሚገኘው የትራምፕ የግል ሪዞርት ውስጥ ከ100 በላይ ሚስጥራዊ ሰነዶች መገኘቱን ተከትሎ ነበር ባለፈው ሳምንት 37 ሰዎች ላይ ክስ የተመሰረተው።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትራምፕ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ሰነዶችን እንደያዙ አንዳንዱንም በመታጠቢያ ቤት በመደበቅ መንግሥት ሰነዶቹን መልሶ እንዳያገኛቸው አሲረዋል ሲል ከሷል።

ተገኙ የተባሉት ሰነዶች አሜሪካም ሆነ ሌሎች ሀገራት ያላቸው የመከላከያና የጦር መሳሪያ አቅም እንዲሁም የውጪ ጥቃትን ተከትሎ አጻፋዊ ምላሸን መስጠት እንደሚቻል የሚያሳይ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

ትራምፕ ጠበቃቸውን እነዚህን ሰነዶች “ሰውራቸው ወይም አውድማቸው” ወይም ለመርማሪዎች እሳቸው ሰነዶቹ እንደሌላቸው ተናገር በማለት የምርመራ ሂደቱ እንዲደናቀፍ አድርገዋል የሚልም ክስ ቀርቦባቸዋል።

ይህ ድርጊት ወንጀል ሆኖ ከተገኘ ጠንከር በለ ሁኔታ ወደ እስር ቤት ሊያስልክ እንደሚችል የህግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ትራምፕ ግን የመጨረሻው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ለፕሬዝዳንትነት ለመመረጥ የማደርገውን ዘመቻ አላቋርጥም ብለዋል።