ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባሏን ገድላለች የተባለችው አሜሪካዊት ከወንጀሉ በፊት የቅንጦት ማረሚያ ቤት ስታፈላልግ ነበር ተባለ
ስለ ሃዘን በጥልቀት የሚተርክ መጽሃፍ ከመድረሷ በፊት ባሏን ገድላለች የተባለችው አሜሪካዊት ከወንጀሉ በፊት የቅንጦት ማረሚያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች ሊያስወነጅሏት የሚችሉ መረጃዎች ስትፈልግ እንደነበር ተነገረ።
እነዚህን መረጃዎች በበይነ መረብ ላይ ስትፈልግ እንደነበር የስልኳ የኢንተርኔት ታሪክ ማመላከቱን የፍርድ ቤት ሰነዶች አመላክተዋል።
ኩሪ ሪቺንስ የተባለችው የ33 ዓመቷ ግለሰብ ባለቤቷን ፌንታኒል በተሰኘው መርዝ ገድላዋለች የሚል ክስ ቀርቦባታል።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ፈጽማዋለች የተባለውን ግድያ ኩሪ “ፍጹም አላደረግኩም” ስትል አልተቀበለችውም።
ለባለቤቷ ከቮድካ ጋር የተቀላቀለ መጠጥ እንደሰጠችውና ከሰዓታት በኋላም ራሱን ስቶ ማግኘቷን ለመርማሪ ባለስልጣናቱ ተናግራለች።
ኩሪ የዋስ መብት ተክልክላለች።
ሰኞ እለት በዋለው ችሎትም ኩሪ ሪቺንስ ወንጀሉን ስለመፈጸሟ ያመላክቷሉ የተባሉ በጉግል ላይ ያደረገችው የኢንተርኔት ዳሰሳ ታሪክም በዝርዝር ቀርቧል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ ‘ለማህበረሰቡ ጠንቅ’ በማለት ከጠሯትም በኋላ በእስር እንድትቆይ ውሳኔም አስተላልፈዋል።
ግለሰቧ ግድያውን ከመፈጸሟ በፊት በኢንተርኔት ስትፈልጋቸው ነበር ከተባሉትም መካከል፦
- ሊገድል የሚችለው የፌንታይል መጠን ምን ያህል ነው?
- በአሜሪካ ውስጥ ለሃብታሞች የሚሆኑ የቅንጦት ማረሚያ ቤቶች
- የሞት የምስክር ወረቀት በመጠበቅ ላይ እያለ የህይወት መድን ይከፈላል?
- ፖሊሶች እውነት ወይም ሃሰት መናገርዎን በሚመረምረው መሳሪያ እንዲመረመሩ ሊያስገድድዎት ይችላሉ?
- ከአይፎን ላይ መረጃን በሩቅ ሆኖ እንዳይገኝ አድርጎ እንዴት መሰረዝ ይቻላል የሚሉ እንደሆኑ የክሱ ሰነዶች አመላክተዋል
ጠበቃዋ በበኩላቸው ደንበኛቸው ጉዳይዋ እንዴት እየተረመረመረ እንደሆነ ለማየት በሚል ነው እነዚህን መረጃዎች ስታይ የነበረው ካሉ በኋላ “ወንጀሉን ስለመፈጸሟ” የሚያመላክት ምንም ነገር የለም ሲሉም ተናግረዋል።
አቃብያነ ህግ በበኩላቸው የሶስት ልጆች እናት የሆነችው ኩሪ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር አንድ ሌሊት ላይ ለፖሊስ ደውላ ባለቤቷ ራሱን እንደሳተ ተናግራለች።
ባለቤቷ በአልጋ ላይ እያለ ከቮድካ ጋር የተቀላቀለ መጠጥ ሰጥታው እንደነበርና ቅዥት እያስቸገራት ከነበረው አንደኛው ልጃቸው ጋር በሌላ ክፍል መተኛቷንም ለመርማሪዎች አስረድታለች።
ሆኖም መርማሪዎች ባለቤቷ ከመጠን በላይ በሆነ ፌንታኒል ተመርዞ መሞቱን አረጋግጠዋል።