የፕሬዝዳንት ፑቲን ጓደኛ በስዊዝ ባንክ ገንዘብ እንዲያስቀምጡ ‘የረዱ’ ሠራተኞች ጥፋተኛ ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጓደኛ የሆኑ ግለሰብ ከፍተኛ ገንዘብ በስዊትዘርላንድ ባንኮች ውስጥ እንዲያስቀምጡ ፈቅደዋል የተባሉ አራት የባንክ ሠራተኞች ጥፋተኛ ተባሉ።
የባንክ ሠራተኞቹ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግም ነው የተፈረደባቸው።
የሩሲያው ጋዝፕሮም ባንክ የዙሪክ ቅርንጫፍ የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚዎች ሙዚቀኛውን ሰርጌይ ሮልዱጂንን ወይም በቅጽል ስማቸው “የፑቲን የኪስ ቦርሳ”ን ረድተዋል በሚልም ነው የሰባት ወራት የእገዳ ቅጣት የተጣለባቸው።
ሰርጌይ ከ2014 እስከ 2016 ባለው ወቅት 50 ሚሊዮን ዶላር ማስቀመጣቸው ተዘግቧል።
ግለሰቡ ገንዘቡን ከየት እንዳመጡት ምንም ዓይነት ተአማኒነት ያለው ማብራሪያ አልሰጡም ተብሏል።
በስዊትዘርላንድ ሕግ መሠረት ባንኮች በሂሳቡ ባለቤት ወይም በገንዘቡ ምንጭ ላይ ጥርጣሬ ካደረባቸው ውድቅ ማድረግ ወይም መዝጋት ይጠበቅባቸዋል።
የቼሎ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች የሆኑት ሰርጌይ የፕሬዝዳንት ፑቲን የበኩር ሴት ልጅ ማሪያ የክርስትና አባት ናቸው።
ጥፋተኛ የተባሉት የባንክ ሠራተኞች ሦስቱ ሩሲያውያን ሲሆኑ አንደኛው ደግሞ የስዊትዘርላንድ ዜግነት ያላቸው ናቸው ተብሏል።
በስዊትዘርላንድ የሪፖርት እገዳዎች ምክንያት ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የተደረጉት እነዚህ ሠራተኞች፣ በአገሪቱ ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
የዙሪክ ፍርድ ቤት ዳኛ ሰርጌይ ያስቀመጡት ገንዘብ እውነተኛ ባለቤት አለመሆናቸው ከጥርጣሬ በላይ ነው ብለዋል።
ይህንን የሙዚቀኛውን የባንክ ሂሳብ የከፈቱት አራት ሠራተኞች ጥያቄዎችን ሊያቀርቡ በተገባ ነበር ተብሏል። ሰርጌይ በወቅቱ ይህ ነው የሚባል ገቢ ያልነበራቸው ሲሆን፣ የገንዘቡ ምንጭም ከየት እንደሆነ መጠይቅ ይጠበቅባቸው እንደነበርም ተጠቅሷል።
እነዚህን ማጣራቶች በተገቢው ሁኔታ ባለማካሄዳቸው የስዊትዘርላንድን ተገቢ የጥንቃቄ ሕጎች በመጣስ ጥፋተኛ ሆነው እንደተገኙም ተገልጿል።
በግለሰቦቹ ላይ የተጣለው ቅጣት ቀላል ቢሆንም ክሱ ግን ትልቅ አንድምታ እንዳለው ተነግሯል። በባንክ የተቀመጠው ገንዘብ የሰርጌይ ካልሆነ የማን ነበር የሚልም ጥያቄ አስነስቷል።
ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ በምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ የተጣለባቸው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ብዙ ሀብት እንዳላቸው እየተነገረ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም በውጭ አገራት ኢንቨስት መደረጋቸው ተገልጿል።












