አሜሪካ ለዩክሬን በምታደርገው አዲስ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ከባድ ሮኬቶችን ልትልክ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ዩክሬን ራሷን ለመከላከል የሚያስችላትን ዘመናዊ እና ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ ሮኬቶችን ልትልክ መሆኑን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስታወቁ።
ዩክሬን የሩሲያ ኃይሎችን ከርቀት መምታት የሚያስችላት ይህ መሳሪያ እንዲሰጣት ለረዥም ጊዜ ስትጠይቅ ቆይታለች።
የጦር መሣሪያው በሩሲያ ውስጥ ያሉ ነገሮች ኢላማ ሊያደርግ ይችላል በሚል ስጋት አሜሪካ እስካሁን ድረስ የዩክሬንን ጥያቄ አልተቀበለችውም ነበር።
ይሁን እንጂ ረቡዕ ዕለት ፕሬዝደንት ባይደን፣ የጦር መሣሪያው ድጋፍ ኪዬቭ ከሩሲያ ጋር የሚኖራትን የድርድር አቅም ለማጠናከር እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ግጭቱን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።
“ዩክሬን በጦርነት ቀጠና ውስጥ ወሳኝ ኢላማዎችን ለመምታት የሚያስችላትን ይህንን ዘመናዊ የሆነ ሮኬት እና ተተኳሾች ለመስጠት የወሰነውም በዚህ ምክንያት ነው” ሲሉ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ጽፈዋል።
አዲሱ የጦር መሣሪያ ድጋፍ መካከል ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል ረዥም ርቀት መጓዝ የሚችል የሮኬት ሥርዓት እንደሚገኝበት አንድ የዋይት ሃውስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የተናገሩ ሲሆን የጦር መሳሪያ ድጋፎች ግን በአሃዝ ምን ያክል እንደሆኑ ግን በቁጥር አልገለጹም።
ይህ የሮኬት ሥርዓት ዩክሬን አሁን ላይ ካላት ከባድ የጦር መሣሪያ በተሻለ በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ኢላማ ላይ ጥቃት መፈፀም ይችላል።
ከዚህ ባሻገር ሩሲያ ካላት ሮኬቶች በተሻለ ኢላማቸውን በትክክል ይመታሉ ተብሎም ይታመናል።
ባለፈው ወር፣ የዩክሬን ጦር አዛዥ ይህን የሮኬት ሥርዓት ማግኘት የሩሲያን የሚሳኤል ጥቃት ለመከላከል ወሳኝ ነው ብለው ነበር።
አሜሪካ ዩክሬን የጦር መሣሪያዎቹን ጦርነቱ በተፋፋመበት እና የዩክሬን ከተሞችን ኢላማ ለማድረግ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የሩሲያን ከባድ መሣሪያዎች እና ኃይሎች በሚገኙበት በምስራቃዊ ዶንባስ ክልል ታሰማራለች ብላ ትጠብቃለች።
የዋይት ሃውስ ባለሥልጣናት ሮኬቱን ለዩክሬን ለመስጠት የተስማሙት መሣሪያው በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ኢላማዎችን ለመምታት እንደማይውሉ ከፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ማረጋገጫ በማግኘታቸው ነው።
ባይደን ረቡዕ ዕለት በጻፉት ጽሁፍ “ሩሲያን የሚመታ የሮኬት ሥርዓት ለዩክሬን አንልክም” ብለዋል።
አሁን አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠው ሮኬቶች ረቡዕ ዕለት በይፋ የተገለጸው 700 ሚሊዮን ዶላር ጥቅል ድጋፍ ዋነኛው ክፍል መሆኑን የዋይት ሃውስ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሄሊኮፕተሮች፣ ፀረ ታንክ መሣሪያዎች፣ ስልታዊ የሆኑ ተሽከርካሪዎች እና መለዋወጫዎችም አሜሪካ ጦርነቱ የካቲት ወር ላይ ከጀመረ አንስቶ ለዩክሬን ባደረገችው 11ኛው የጦር ድጋፍ ጥቅል ይካተታሉ ተብሏል።
ረቡዕ ዕለት ባይደን የአሜሪካ ዋና ዓላማ “ዲሞክራሲያዊ፣ ራሷን የቻለች፣ ሉዓላዊ” ዩክሬንን ማየት እንጂ ፕሬዝደንት ፑቲንን ከሥልጣን ማንሳት አሊያም ከሞስኮ ጋር የድንበር ግጭት እንዲፈጠር አይደለም ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ “ሩሲያ የሚደረገውን የሰላም ጥረት አልተቀበለችም” ሲሉ የከሰሱ ሲሆን ግጭቱን ለማስቆም ሲባል ዩክሬን የራሷን ግዛት በምላሹ እንድትሰጥ አሜሪካ ጫና እንደማታደርግ ገልጸዋል።
በዩክሬን ጥቅም ላይ እየዋለ ስላለው የኒዩክሌር ጦር መሣሪያ አደጋ አስመልክቶም ፕሬዝደንት ባይደን፤ “ይህ የሩሲያ ፍላጎት መሆኑን የሚያሳዩ እስካሁን ምንም ምልክቶችን አላየንም፤ ነገር ግን ይህንን መጠቀም ተቀባይነት የሌለው እና ከባድ መዘዝ የሚያስከትል” ነው ብለዋል።
የባይደን ጽሁፍ በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ከታተመ በኋላ የሩሲያ የጦር ባለሥልጣናት የአገሪቷ የኒዩክሌር ኃይሎች በሞስኮ አቅራቢያ ኢቫኖቮ ግዛት ልምምድ እያደረጉ መሆኑን ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዩክሬን በምስራቃዊቷ ዶንባስ ክልል ጦርነቱ ቀጥሏል።
ማክሰኞ ዕለት የሉሃንስክ ገዥ በክልሉ ከተያዙ ግዛቶች አንዷ የሆነችው ምስራቃዊቷ ከተማ ሴቬሮዶንስክ በአብዛኛው በሞስኮ ቁጥጥር ሥር መዋሏን አስታውቀዋል።
የሩሲያ ኃይሎች በአብዛኛው የሉሃንስክን ግዛት የያዙ ሲሆን ጎረቤቷን ዶኔስክ ለማያዝ ትኩረት እያደረጉ መሆናቸውም ተነግሯል።












